ዋዜማ- ባለፉት ዓመታት በመቶ ቢሊየን የሚቆጠር ገንዘብ ከብሄራዊ ባንክ የወሰደው መንግስት ከዚህ በኋላ እንደፈለገ የሚበደርበትን አሰራር የሚከለክል አዲስ ረቂቅ አዋጅ ለተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ።

ዋዜማ የተመለከተችው ረቂቅ አዋጅ እንዳሰፈረው መንግስት የከፋ ችግር ካልገጠመው በቀር ከብሄራዊ ባንክ ያለገደብ የሚበደርበት አሰራር ከዚህ በኋላ በህግ የተከለከለ ይሆናል።

ይህ ድንጋጌ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ማቋቋሚያ አዋጅን ለማሻሻል በቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ተካቶ የቀረበ ሲሆን በረቂቅ አዋጁ ክፍል አምስት በብሔራዊ ባንክ እና በመንግስት መካከል የሚኖረውን ግንኙነት ባተተበት ምእራፍ ውስጥ ተካቷል።

“በአዋጁ በግልጽ ካልተፈቀደ በስተቀር ብሔራዊ ባንክ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ለፌዴራል ; ለክልል ; ለማንኛውም የታችኛው የመንግስት የአስተዳደር እርከን ፣ የከተማ አስተዳደር ወይም የመንግስት ተቋም ብድር መስጠት አይችልም ” ይላል።

የፌዴራል መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ሲወስድ የቆየው ቀጥተኛ ብድር (Direct advance)በሚባል የሚታወቀው የብድር አይነት የገንዘብ ህትመትን በማበረታታት ለሀገሪቱ የዋጋ ንረት መባባስ ከዋነኞቹ ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳል።

በአዋጁ ማብራሪያ ላይ እንደተጠቆመው በመንግስት ከብሄራዊ ባንክ ጋር ያለው የብድር ግንኙነት በግልጽ ተደንግጎ አለመቀመጡ ችግር መፍጠሩን ያነሳል። ከ1995 ዓ.ም አንስቶ እስከ 2000 ዓ.ም ድረስ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ በሚወስደው የብድር መጠን እና የአከፋፈል ሁኔታ እንዲሁም ወለዱ በሚሰላበት አግባብ ላይ ግልጽ ድንጋጌ እንደነበር የጠቀሰው የአዋጁ ማብራሪያ ፣ ነገር ግን እነዚህ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ ብድር የሚወስድበትና የሚከፍልበትን እንዲሁም ወለድ የሚሰላበት ድንጋጌ ከ2000 ዓ.ም ወዲህ እንዲወጡ መደረጉንም አንስቷል።

ብዙዎች እነዚህ ገደቦች መነሳታቸው መንግስት በተለይም የፌዴራል መንግስት ከብሄራዊ ባንክ ያለ መጠን እና ያለ መክፈያ ጊዜ ገደብ እንዲበደር እንዳደረገው እና ከብሔራዊ ባንክ የሚወሰድ ብድር ደግሞ ሌሎች ባንኮች እንደሚያደርጉት ከገበያ የተሰበሰበ ሳይሆን በኢኮኖሚ ውስጥ ያልነበረ እና ከምርት ጋር የማይገናኝ በመሆኑ የዋጋ ንረት እንዲባባስ መንገድን ከፍቷል ።

የፌዴራል መንግስት ከብሔራዊ ባንክ በዚህ መንገድ በመቶ ቢሊየን ብሮች ተበድሮ ወደ ገበያ ማስገባቱ እና እነዚህ ብድሮችም አለመመለሳቸውን ለጉዳይ ቅርብ የሆኑ ምንጮች ያስረዳሉ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባለፈው አመት ሀምሌ ወር ላይ ባወጣው መመሪያ የፌዴራል መንግስት በ2016 ዓ.ም ከብሔራዊ ባንክ መበደር የሚችለው በ2015 ዓ.ም የተበደረውን አንድ ሶስተኛውን ብቻ እንዲሆን ገድቦት ቆይቷል።አሁን በማእከላዊ ባንኩ ረቂቅ አዋጅ ላይ ብድርን ለመንግስት መስጠት እንደማይችል አስቀምጧል።

ሆኖም ለፓርላማው የቀረበው ረቂቅ አዋጅ መንግስት ከብሔራዊ ባንክ የሚበደርበትን መንገድ ሙሉ ለሙሉ አልዘጋውም። በዚህም ብሔራዊ ባንክ በጥሬ ገንዘብ ፍሰት ላይ የተመሰረተ ጊዜያዊ የኦቨር ድራፍት አገልግሎት (የመንግስት ሂሳብ እየታየ በአንድ አመት ውስጥ የሚከፍለው የአጭር ጊዜ ጊዜ ብድር ) እንደሚሰጠው ይጠቅሳል። ይህም ግን ሁለት ገደቦች ተጥለውበታል። አንዱ በዚህ መልኩ የሚሰጠው ብድር የፌዴራል መንግስት ያለፉት ሶስት አመታት ገቢው አማካዩ ተወስዶ ፣ የአማካዩ 15 በመቶ መሆኑ እና ፣ መንግስት በቀጣይ አመት ተመሳሳይ የኦቨር ድራፍት ብድር መውሰድ ከፈለገ ቀድሞ የወሰደውን ብድር የግድ መመለስ እንዳለበትም ግዴታ ተቀምጧል። በገንዘብ ፖሊሲ ተመን ላይ ተመስርቶ የሚመሰለ ወለድም ይታሰብበታል።

መንግስት ከተቀመጠለት በላይ ብድር መጠየቅ የሚችለውም ከአቅም በላይ የሆነ ችግር ሲያጋጥም ; ማለትም ያልጠበቀ የማህበረሰብ ጤና ችግር ፣ የተፈጥሮ አደጋ ፣ ድርቅ ወይንም አጠቃላይ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ወይንም በፌዴራል መንግስት ገቢ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ የውጭ ኢኮኖሚ ለውጦች ሲኖሩ መሆኑም ተጠቅሷል።

ረቂቅ አዋጁም ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ በትላንትናው እለት ተመርቷል። [ዋዜማ]