ዋዜማ- ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ንግድ ባንኮች በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ላይ እንዳይሰማሩ ያደረገው በ2009 ዓ.ም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ወጥቶ የነበረው መመሪያ በአዲስ መመሪያ ተተክቶ ንግድ ባንኮች በተለያዩ ዘርፎች ላይ በተገደበ ሁኔታ እንዲሰማሩ ተፈቀደ ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከሀምሌ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ባወጣው መመሪያ ንግድ ባንኮች ሊሰማሩባቸው የሚችሏቸውን ዘርፎች ዘርዝሯል።

በዚህም አንድ ባንክ በአንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ ውስጥ ብቻ አክስዮን ሊኖረው እንደሚችል : ነገር ግን ባንኩ በኢንሹራንስ ኩባንያው ውስጥ የሚኖረው ድርሻ ከኢንሹራንስ ኩባንያው አጠቃላይ ካፒታል ከ5 በመቶ መብለጥ እንደሌለበትም መመሪያው ያስቀምጣል። ሆኖም ራሳቸው ባንኮቹ ግን የኢንሹራንስ አገልግሎት መስጠት አይችሉም ተብሏል።

እንዲሁም ንግድ ባንኮች እንደ ኢንቨስተመንት ባንክ ባሉ የካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭ ካምፓኒዎች ውስጥ ሙሉ ድርሻ ኖሯቸው በባለቤትነት እንዲይዙም ተፈቅዷል። ይህም በካፒታል ገበያ አዋጁ መሰረት የሚፈጸም እንደሆነም ያብራራል።

የኢንቨስትመንት ባንኮች በብዛት በካፒታል ገበያ ላይ ለሚሳተፉ አካላትን የማማከር : ኩባንያዎችም ሆኑ ጀማሪ ነጋዴዎች መንቀሳቀሻ ገንዘብን ሲፈልጉ በካፒታል ገበያ ውስጥ ገንዘብ የማፈላለግ ስራን ይሰራሉ ፤አገናኝ ሆነው ያገለግላሉ።

ባንኮች በካፒታል ገበያ ውስጥ እንዲሳተፉ መፈቀዱም ጅምር ላይ ላለው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ጥሩ መነቃቃትን ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል። ሆኖም ባንኮች ከካፒታል ገበያ አገልግሎት ሰጭ ስራዎች ውስጥ የተቋማት የብድር ቁመና ደረጃ ሰጭ( credit rating agency)  ኩባንያዎቸ ውስጥ ድርሻ እንዲኖራቸው አልተፈቀደም።ባንኮች ራሳቸው በነዚህ ተቋማት ቁመናቸው የሚገመገም በመሆኑ የጥቅም ግጭት እንዳይኖር በማሰብ ነው ገደቡ የተቀመጠው።

አዲሱ መመሪያ በተጨማሪ ባንኮች ፤ የባንክ እና የኢንሹራንስ አገልግሎት በማይሰጥ አንድ ኩባንያ ውስጥ  እስከ 10 በመቶ ድርሻ ሊኖራቸው እንደሚችል ደንግጓል። ሆኖም ባንኮች ከዘርፋቸው ውጭ በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ውስጥ ሲሰማሩ የሚያፈሱት ገንዘብ ከአጠቃላይ ካፒታላቸው ከ15 በመቶ ሊበልጥ እንደማችልም መመሪያው ተቀምጧል። ባንኮች ከብሄራዊ ባንክ ፍቃድ ውጭ ከአጠቃላይ ካፒታላቸው ከ10 በመቶ በላይ የሆነ ገንዘብ በሪልስቴት ንግድ ዘርፍ ባለቤት መሆን እንደማይችሉም መመሪያው ያዛል።

አዲሱ መመሪያ ለበርካታ ጊዜያት ዝግ የሆኑ ስራዎች ለባንኮች ክፍት ያደረገ ሲሆን በተለይ ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፏን ለውጭ ለመክፈት እየተዘጋጀች ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ባንኮች በትርፍም ሆነ በካፒታል እንዲጠናከሩ ሊረዳቸው እንደሚችል ታምኖበታል። [ዋዜማ]