ዋዜማ- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ፓርኮች በፌደራልና በከተማ አስተዳደሩ ስር ተለይተው እንዲተዳደሩ የሚስችል አዲስ ደንብ ስራ ላይ ውሏል። ለዚህም እንዲረዳ ሁለት ኮርፖሬሽኖች ተቋቁመዋል።
በፌደራል ደረጃ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር ከሀምሌ 30 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ የተቋቋመው የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ሲሆን እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የተቋቋመው የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችና ፓርኮች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ይባላል።
ዋዜማ የተመለከተችው የአንድነት ፓርኮች ኮርፖሬሽን ማቋቋሚያ ደንብ እንደሚገለጸው 5 የፓርክ አገልግሎት ላይ የተሰማሩ ተቋማት ማለትም አንድነት ፓርክ፣ የአንድነት የመኪና ማቆሚያ ህንጻ፣ ሳይንስ ሙዚየም፣ ወዳጅነት አደባባይ አንድ እና ሁለት በአንድ ተቋም እንዲተዳደሩ ተደርጓል።
ኮርፖሬሽኑ የፌደራል የመንግስት የልማት ድርጅት በመሆን የተቋቋመ በመሆኑ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ይቆጣጠረዋል።
በጠቅላይ ሚኒሰትር አብይ አህመድ ተፈርሞ በነጋሪት ጋዜጣ የታተመው ሰነድ እንደሚገልጸው ከሆነ ለኮርፖሬሽኑ ማቋቋሚያ የተፈቀደው ካፒታል 28 ቢሊየን ብር ሲሆን 22.14 ቢሊየን ብር በጥሬ ገንዘብና በዓይነት መከፈሉን ይገልጻል።
የተወሰነ የጊዜ ቆይታ የሚኖረው ኮርፖሬሽኑ ካለው ጠቅላላ ንብረት በላይ በዕዳ ተጠያቂ እንደማይሆን ተጠቅሷል፡፡
በተመሳሳይ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስር የህዝብ መዝናኛ ቦታዎችና ፓርኮች አስተዳደር ኮርፖሬሽን ታህሳስ ወር 2016 ዓ.ም 10 ፓርኮችን በጋራ በመያዝ መቋቋሙን፣ የኮርፖሬሽኑ የኢኮ ቱሪዝምና ደንበኞች አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ መዝገቡ ይስማው ለዋዜማ ተናግረዋል።
በአንድ የተቋቋሙት 10 ፓርኮች በፊት በየራሳቸው የሚተዳደሩ የነበሩ ሲሆን እንጦጦ ፓርክ፣ አዲስ ፓርክ፣ 6 ኪሎ ፓርክ (አንበሳ ግቢ)፣ ኢትዮ ኩባ ወዳጅነት ፓርክ፣ የኮሪያ ዘማቾች ፓርክ፣ ሐምሌ 19 ፓርክ ፣ ብሄረጽጌ፣ ከንቲባ ወልደጻዲቅ ፓርክ፣ አፍሪካ ፓርክ፣ አምባሳደር እና ልደታ ፓርክ ናቸው።
እነዚህ 10 ፓርኮች ከተቋቋሙበት ወር ጀምሮ በ2016 የበጀት አመት 63 ሚሊዮን 591 ሺ ብር መገኘቱን ይህም የእቅዱን 89 በመቶ ማሳካት መቻሉን አቶ መዝገቡ ተናግረዋል።
በከተማ አስተዳደሩ ስር የተቋቋመው ይህ ኮርፖሬሽን ሶስት ዘርፎች ያሉት ሲሆን ኢኮ ቱሪዝም (የደንበኞች አገልግሎት ፣ጉብኝትና ሁነቶች የሚያካሂድ)፣”የእንሰሳትና እጽዋት ዘርፍ” ደግሞ (Zoo service)ና ችግኝ ማልማት ሲሆን ሶስተኛው “የምህንድስና ዘርፍ አገልግሎት” የተባለው ፓርኮችን በደረጃቸው እድሳት ማድረግና የአደባባይ ኮሪደር ስራ ዘርፎች በመባል የተዋቀሩ ናቸው። [ዋዜማ]