- ምዕራባውያን ኢትዮዽያ የበቀል ጥቃት ከመወስድ እንድትቆጠብ እያግባቡ ነው
- የኢትዮዽያ የስለላ ቡድን ተሰማርቷል
- ደቡብ ሱዳን ማናቸውም ወታደራዊ ጣልቃገብነት አልቀበልም ብላለች
- አስካሁን የተካሄደ ይህ ነው የሚባል ወታደራዊ ዘመቻ የለም
(ዋዜማ) የደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር አንድ ምዕራፍ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የጥምር መንግስት ምስረታ አጣብቂኝ ውስጥ በወደቀበት በዚህ ጊዜ ኢትዮዽያ የበቀል ወታደራዊ እርምጃ ለመውሰድ ብትሞክር ክፍለ አህጉሩን ወደ አዲስ ቀውስ ሊያመራው ይችላል በሚል ምዕራባውያን ስጋታቸውን እየገለፁ ነው።
የኢትዮዽያን ጥቃት ተከትሎ የደቡብ ሱዳን የጎሳ ጦርነት ከዚህ ቀደም ከነበረውም ተባብሶ ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት ያደረባቸው ምዕራባውያን ኢትዮዽያን እያሳሰቡ መሆኑ ተሰምቷል። ኢትዮዽያ ራሷው አደራዳሪ የሆነችበትን የሰላም ጥረት እንዳታፈርሰው ለማሳሰብ የአውሮፓና የዩናይትድ ስቴትስ ዲፕሎማቶች ጫና ለማድረግ እየሞከሩ ነው።
“በህዝብ ጫና እየተደረገበት ያለው የኢትዮዽያ መንግስት ለዓመታት ጦርነት ባደቀቀው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ላይ ጥቃት ቢፈፅም ራሱ በአደራዳሪነት ጭምር የተሳተፈበትን የእስካሁኑን ጥረት ያፈርሰዋል። ያን ያደርጋሉ ብዬ አልጠብቅም” ይላሉ በኣአደራዳሪነት የሚሳተፉ የምዕራብ ዲፕሎማት።
“ሁለቱ መንግስታት በቅርበት ተነጋግረው ወንጀለኞቹ የሚያዙበትንና የሚቀጡበትን መንገድ እንዲፈልጉ ሀሳብ ስጥተናቸዋል” ዲፕሎማቱ የኢትዮዽያ መንግስት ባለስልጣናትን መነጋገራቸውን በመጥቀስ።
ሰፊ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነትም ሆነ ጭፍን ወታደራዊ እርምጃ በቋፍ ያለውን የደቡብ ሱዳን ቀውስ ያባብሰዋል ወደ ኢትዮዽያም እንዲዛመት በማድረግ ችግሩ አዲስ መልክ ይይዛል የሚል ስጋት አላቸው ዲፕሎማቱ።
የኢትዮዽያ መንግስት በበኩሉ የደቡብ ሱዳን መንግስት ተባባሪ ከሆነ የጋምቤላ ጥቃት ያደረሱት ታጣቂዎች ላይ የተመጠነ የአፀፋ ቅጣት ማድረስ ይቻላል ባይ ነው። የደቡብ ሱዳን መንግስት ግን ምንም አይነት ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት አልፈልግም በሚል የደቡብ ሱዳን ድንበርን አቋርጠው የገቡትን የኢትዮጵያ ወታደሮች እንዲወጡ አድርጓል።
የቅርብ የኢትዮዽያ ምንጮች እንደገለፁት ግን ኢትዮዽያ በቁጥር አነስተኛ የሆነ ስውር የክትትል ቡድን በአካባቢው አሰማርታ መረጃ እያሰባሰበች ነው። የጋምቤላው ጥቃት የጎሳ ግጭትን ሽፋን በማድረግ የደቡብ ሱዳን አማፅያን መሪ ሪክ ማሻርን ለመግደል የተቀነባበረ መሆኑን የሚጠቁሙ መረጃዎች እየወጡ ነው።LINK http://wazemaradio.com/?p=2076
የጋምቤላው ጥቃት በደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርና የአማፅያኑ መሪ ሪክ ማሻር መካከል ያለውን አለመተማመን አስፍቶታል።
“በጋምቤላ የደረሰው ጥቃት የመጀመሪያ ኢላማ ነበሩ” የተባለላቸው የደቡብ ሱዳን አማጽያን መሪ ሬክ ማሻር ወደ ሀገራቸው መናገሻ ከተማ ጁባ ሊያደርጉት የነበረውን ጉዞ ላልተወሰነ ጊዜ አስተላለፉ፡፡ ማሻር ከውሳኔው ላይ የደረሱት የእርሳቸው የቅርብ ሰዎች ወደ ጁባ ይዘዋቸው ሊገቡ ባሰቧቸው ከባድ መሳሪያዎች ላይ ከደቡብ ሱዳን መንግስት ጋር ስምምነት ላይ መድረስ ባለመቻሉ ነው፡፡
ማሻር ወደ ጁባ ሊያቀኑ የነበረው ሶስት ዓመት ያስቆጠረውን የደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት ለመፍታት ከተደረጉ ተደጋጋሚ ድርድሮች በኋላ ተደረሰ በተባለ ስምምነት መሰረት ቀድሞውኑም የነበራቸውን የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታ ለመረከብ ነበር፡፡ የአማጽያኑን መሪ ወደ ስልጣን ለመመለስ የመጀመሪያ ቀን የተቆረጠው ለባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ሚያዝያ 4 ነበር፡፡ በማሻር ጥያቄ ወደ ሰኞ ሚያዝያ 10 እንዲሸጋገር ተደርጓል፡፡
ከጁባ ጉዟቸው በፊት ፓጋክ በተሰኘ በኢትዮጵያ ድንበር አቅራቢያ በሚገኝ ቦታ ባለው ወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያቸው ለምክክር ጎራ ብለው ነበር፡፡ በፓጋክ ከከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮቻቸው ጋር በምክክር ላይ ባሉበት ወቅት ነበር በኪሎሜትሮች ርቅት ላይ የሚገኙት የኢትዮጵያ ሶስት ወረዳዎች በሀገራቸው ሰዎች ተጠቅተው 208 ኢትዮጵያውያን የተገደሉት እና 108 ህጻናት ታግተው የተወሰዱት፡፡
ከግድያው ሁለት ቀን በኋላ ሰኞ በጋምቤላ አውሮፕላን ጣቢያ ተገኝተው ወደ ጁባ ይበርራሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ማሻር የውሃ ሽታ ሆነው ቀሩ፡፡ የአማጽያኑ ቃል አቃባይ “የሎጀስቲክ ምክንያቶችን” በመጥቀስ የማሻር ጉዞ ለዛሬ መተላለፉን አሳውቀው ነበር፡፡ “የሎጀስቲክ ምክንያቶች” ተብለው በደፈናው የተጠቀሱት አንዴ የማሻር ጠባቂዎች ከሚታጠቋቸው መሳሪያዎች ፍቃድ መታጣት ጋር ሌላ ጊዜ የአማጽያኑ “ቺፍ ኦፍ ስታፍ” ሊያጓጉዟቸው ያሰቧቸው የመሳሪያ ዓይነቶች ተቀባይነት አለማግኘት ጋር ሲያያዝ ታይቷል፡፡
ሌሎች ወገኖች ደግሞ የአማጽያኑ “ቺፍ ኦፍ ስታፍ” ጀነራል ሳይመን ጋትዌች ወደ ጁባ መግባት በራሱ እግድ እንደተጣለበት ያስረዳሉ፡፡ ጀነራል ሳይመን ጋትዌች በእርስ በእርሱ ግጭት ወቅት በነበራቸው ድርሻ ምክንያት የተባበሩት መንግስታት እ.ኤ.አ በሰኔ 2015 የጉዞ እና ሌሎችም እግዶች ካስተላለፈባቸው ሶስት የአማጽያኑ ወታደራዊ አመራሮች መካከል አንዱ ናቸው፡፡
ጀነራሉ ከማሻር አስቀድሞ ጁባ እንዲገቡ የታሰበ ቢሆንም እርሳቸውን እንዲወስድ የተዘጋጀው “ቻርተርድ” አውሮፕላን እንኳ ከካርቱም አለመንቀሳቀሱን ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ ማሻር እንዲጓጓዙበት የታሰበው አውሮፕላን ሰኞም ሆነ ማክሰኞ በጋምቤላ አውሮፕላን ጣቢያ በተጠንቀቅ ዝግጁ ሆኖ ይጠባበቅ እንደነበር ምንጮች ጨምረው አስረድተዋል፡፡
ጀነራሉን ጨምሮ ከአማጽያኑ መሪ ጋር ወደ ጁባ ሊያመሩ ሲጠባበቁ የነበሩ ወደ መቶ የሚጠጉ ደቡብ ሱዳናውያን ሁለቱንም ቀናት በአውሮፕላን ጣቢያው ቢታዩም ማሻር ግን በወታደራዊ ማዘዣ ጣቢያቸው ፓጋክ መቆየትን መርጠዋል፡፡ የደቡብ ሱዳን መንግስት ማክሰኞ ከሰዓት ላይ ባወጣው ሶስት ገጽ መግለጫ ላይ ለአማጽያኑ መሪ ወደ ጁባ አለመምጣት ተጠያቂው ራሳቸው ማሻር እንደሆኑ አስታውቋል፡፡ እንደውም ማሻርን “ቃሉን አላከበረም” ሲል ይወርፋቸዋል፡፡
ማሻር እንደ “ጸረ-ታንክ እና በጨረር የሚመሩ ሚሳኤሎች”አይነት ከባድ መሳሪያዎችን ይዘው ለመምጣት ማሰባቸውን መንግስት እንደተረዳ የሚያብራራው መግለጫው ይህ ሁለቱ ወገኖች የደረሱበትን ስምምነት እንደሚጻረር ያስረዳል፡፡ እ.ኤ.አ በህዳር 2015 በአዲስ አበባ በተደረሰው ስምምነት መሰረት አማጽያኑ ወደ ጁባ ይዘው እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ኃይል 1410 ብቻ እንደሆነ መግለጫው ያስታውሳል፡፡
ከእነዚህ ውስጥ 1370 ያህሉ ከታጠቋቸው የነፍስ ወከፍ መሳሪያዎች፣ ቀላል ማሺን ገኖች (አውቶማቲክ ጠመንጃ) እና አር ፒ ጂዎች ጋር ተፈቅዶላቸው ወደ ጁባ ከገቡ መሰንበታቸውን ይገልጻል፡፡ ምክትል ፕሬዝዳንቱን ለመጠበቅ የተመደቡ ናቸው የተባሉ 350 ወታደሮችም ከእነ መሳሪያቸው በጁባ እንደሚገኙ የሚተነትነው መግለጫው ማሻር ይዘው መምጣት የሚችሉት ከተመደበው ቁጥር የጎደሉትን 40 ወታደሮች ብቻ እንደሆነም ይጠቁማል፡፡
“[ማሻር] ማንኛውም ዓይነት ተጨማሪ የታጠቁ ኃይሎች ወይም መሳሪያዎች በጁባ አይስፈልጉትም” ይላል ጠንከር ያለው የደቡብ ሱዳን መንግስት መግለጫ፡፡ “የደቡብ ሱዳን ሪፖብሊክ መንግስት ወደ ጁባ የሚመጣን ተጨማሪ መሳሪያንም ሆነ ትርፍ ኃይል አይቀበልም፡፡”
የደቡብ ሱዳንን ቀውስ ለመፍታት “የመጀመሪያ እርምጃ” ተደርጎ ሲወሰድ የነበረው የሬክ ማሻር ወደ ስልጣን መመለስ እንደተለመደው በሁለቱም ወገን ባለው “የውሃ ቅዳ ውሃ መልስ” ፖለቲካ ላልተወሰነ ጊዜ ተገፍቷል፡፡