ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ አለማግኘታችን በእጅጉ አሳስቦናል ሲሉ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አርሶ አደሮች ተናገሩ። 

በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በተለይም በምዕራብ ሸዋ፣ በአርሲና ባሌ አካባቢ ያሉ አርሶ አደሮችም በተመሳሳይ ማዳበሪያ ለማግኘት ተቸግረናል ሲሉ አቤቱታቸውን እያቀረቡ ይገኛሉ።

የኦሮሚያ ክልል መንግስት በበኩሉ፣ ብልሹ አሰራርና ስርቆት የማዳበሪያ ስርጭቱ ላይ እንቅፋት እንደፈጠረ አምኖ ከፍተኛ መጠን ያለው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ማከፋፈሉን ነግሮናል። 

በምዕራብ ሸዋ ዞን ጉደር ከተማ አካባቢ፣ ኩታዬ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች “ወቅቱ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች የሚከፋፈልበት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እያገኘን አይደለም፤ በዚህም ምክንያት የግብርና ሥራ ወቅት እያለፈብን ነው” ሲሉ ችግራቸውን ለዋዜማ አጋርተዋል።

አርሶ አደሮቹ፣ “ዘንድሮ ዝናብ በወቅቱ ዘንቦ አርሰን መሬቱን አለስልሰን የነበረ ቢሆንም፣ ማዳበሪያ በበቂ ሁኔታ ባለማግኘታችን ምክንያት በሚፈለገው ልክ የግብርና ሥራችንን መከወን አልቻልንም” ባይ ናቸው። 

“በአካባቢው ያለው የመንግሥት መዋቅር በየጊዜው በወቅቱ እናከፋፍላችኋለን ቢሉም፣ ከንግግር በዘለለ የሰሩት ስራ አጥጋቢ አይደለም” ሲሉም አክለዋል።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ሌሎች አርሶ አደሮች በበኩላቸው፣ “የታችኞቹ የመንግሥት መዋቅሮች፣ የአልፎ አልፎ የሚገኘውን ማዳበሪያ እንኳን መንግሥት ከተመነው ዋጋ በላይ በኩንታል ከ 5 መቶ እስከ 7 መቶ ብር ጭማሪ እያደረጉበት ነው የሚሸጡልን ሲሉ ተናግረዋል።

መሬቱ ከማዳበሪያ ጋር በእጅጉ በመላመዱ የተነሳ ያለ ማዳበሪያ ብንዘራ እንኳን ከኪሳራ ውጪ ምንም ምርት መሰብሰብ አንችልም ሲሉም አስረድተዋል። እነሱ ባሉበት አካባቢ እንደ ጤፍ፣ ባቄላ፣ አተር እና በቆሎ የመሳሰሉ አዝርዕቶች በሰፊው እንደሚመረቱ የሚገልጹት አርሶ አደሮቹ፣ ማዳበሪያ በጊዜ ካላገኘን ለከርሞ የምንሰበሰበው ምርት አይኖረንም ብለዋል።

አርሶ አደሮች ከማዳበሪያ ስርጭት ጋር ተያይዞ በዋናነት የሚያነሱት ችግር፣ በመንግሥት በኩል ከመሬት ዓመታዊ ግብር ጋር ተያይዘው አብረው የሚመጡ የተለያዩ አይነት የግብር አይነቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል። 

ከነዚህ ክፍያዎች መካከል የጤና ኢንሹራንስ፣ የመንገድ፣ የስፖርት፣ የሴቶች ሊግ፣ የሰላምና ጸጥታ እና ሌሎችም ስያሜ ያላቸው የተለያዩ ክፍያዎች ተደምረው እንደሚመጡ ገልጸዋል። 

ይህ ክፍያ አንድ ላይ ሲደመር ከአርሶ አደሩ የመክፈል አቅም በላይ እንደሚሆንና፣ ክፍያውን ከፍለው ጨርሰው የከፈሉበትን ደረሰኝ እስካላሳዩ ድረስ ያለውንም ማዳበሪያ መውሰድ እንደማይችሉ ያነጋገርናቸው አርሶ አደሮች ነግረውናል። 

በሌላ በኩል ማዳበሪያ የማከፋፈልን የሥራ ኃላፊነት እንደ ከዚህ ቀደሙ በግብርና ቢሮ በኩል መሆኑ ቀርቶ በኅብረት ሥራ ማኅበራት ስር እንዲሆን መደረጉ ችግሩን ውስብስብ አድርጎታልም ባይ ናቸው። ማዳበሪያ ወደ ማከማቻ መጋዘኖች በብዛት ሲገባ በተደጋጋሚ ማስተዋላቸውን የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ ከመጋዘኑ ወጥቶ ለአርሶ አደሩ በተፈለገው ሰዓት የማከፋፈል ችግር ግን የበዛ ነው ብለውናል።

በዚህ ወቅት መንግሥት የተመነው የአንድ ኩንታል ማዳበሪያ ዋጋ 3 ሺህ 800 ብር ቢሆንም ባለሃብቶች ከኅብረት ሥራ ማኅበራት፣ከወረዳና ከቀበሌ አመራሮች ጋር በመመሳጠር አንዱን ኩንታል እስከ 8 ሺህ ብር በመሸጥ ላይ ይገኛሉ ብለዋል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲን ያነጋገረች ሲሆን፣ ለአርሶ አደሩ ማዳበሪያ በማከፋፈል ሂደት ላይ ትልቅ ፈተና የሆነው በወረዳና ቀበሌዎች ላይ ያለ ሕገወጥ የማዳበሪያ ሽያጭና ብልሹ አሰራር ነው በማለት ኤጀንሲው ገልጿል። 

የኤጀንሲው የግብዓት አቅርቦትና ስርጭት ቡድን መሪ ሚጀና ረጋሳ ለዋዜማ እንደገለጹት፣ ያለውን ሕገወጥ ሽያጭና ብልሹ አሰራር ለመከላከል የማዳበሪያ ግብይት ስርዓትን በዲጂታል መንገድ ብቻ እንዲሆንና ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ የራቀ ለማድረግ ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። 

በዚህም በዘንድሮ ዓመት በዲጂታል የግብይት ስርዓት የ5 ቢሊዮን ብር የማዳበሪያ ሽያጭ ተፈጽሟል ሲሉ ለዋዜማ ነግረዋታል። ይህም ሆኖ በአርሲ እና ምስራቅ ሸዋ ዞኖች አንዳንድ አካባቢዎች ላይ ሕገወጥ የማዳበሪያ ሽያጭና ስርቆት መኖሩን ይጠቅሳሉ። 

በተጨማሪም ማዳበሪያው ማከማቻ መጋዘኖች ላይ ተጓጉዞ ከደረሰ በኋላ ሳይራገፍ ለቀናት በመኪና ላይ መቆየቱ፣ “አርሶ አደሩ እጅ በተፈለገው ሰዓት እንዳይደርስ እንቅፋት ሆኗል” ሲሉ ችግር ነው ። 

“በዘንድሮ ዓመት እንደ ክልል 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የማዳበሪያ ፍላጎት ቢኖርም እስካሁን እጃችን የደረሰው 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ነው ያሉት” ሚጀና፣ “በፍላጎትና አቅርቦት መካከል የ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ክፍተት” አለ ብለውናል። 

“የተቀበልነውን 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንደ ታጠቅ፣አዳማ፣ጅማና ነቀምትን በመሳሰሉ ግዙፍ ማከማቻዎች አስገብተናል” ሲሉ ቡድን መሪው ሰራን ያሉትን ይጠቅሳሉ። 

እንደርሳቸው ንግግር፣ ከ 6 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ መካከል 3 ነጥብ 6 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ ተከፋፍሎ አርሶ አደሩ እጅ ደርሷል። ቀሪው እንደ ክልሉ ባሉ ኅብረት ሥራ ማኅበራት አማካኝነት እየተከፋፈለ መሆኑንም ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ “አቅደን የነበረውን 8 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንዳናገኝ ያደረገው፣ በጅቡቲ ወደብ ተራግፎ የነበረው ማዳበሪያ ተከስቶ በነበረው ጎርፍ ምክንያት በታቀደው ሰዓት ተጓጉዞ አለመድረሱ ነው” ብለዋል።

 በክልሉ አንዳንድ አካባቢዎች ያለው የጸጥታ ሁኔታም ማዳበሪያውን ለአርሶ አደሩ በሚፈለገው ልክ ለማድረስ ችግር ከሆኑ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ ነው ባይ ናቸው። ይህም ሆኖ ያሉ ችግሮችን በመቅረፍ ማዳበሪያው ለአርሶ አደሩ ለማድረስ ጥረት እየተደረገ ነው ሲሉ ቡድን መሪው ሁኔታውን ለዋዜማ አስረድተዋል። [ዋዜማ]