• ቤተክርስቲያኒቱ ችግሩን ለመቅረፍ ውይይት መጀመሩን ለዋዜማ ተናግራለች

ዋዜማ- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ስር ባሉ የአዲስ አበባ ከተማ ሀገረ ስብከት አድባራትና ገዳማት ሥራ ለመቀጠር እንደየደረጃው ከ 3 መቶ ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር እጅ መንሻ ክፍያ እንደሚጠየቅ ዋዜማ ካነጋገረቻቸው የተለያዩ ምንጮች ሰምታለች።

በተለይም በከተማይቱ፣ ትልቅ ሀብት የሚያንቀሳቅሱና ከፍተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸው ናቸው በሚባሉ አድባራትና ገዳማት አሥተዳዳሪ፣ ጸሐፊ፣ ሂሳብ ሹም ሆኖ ለመቀጠር ከ 3 መቶ ሺሕ እስከ 1 ሚሊዮን ብር እጅ መንሻ (ጉቦ)  እንዲከፍሉ እንደሚጠየቁ ነግረውናል።

ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁና ከጉዳዩ ጋር ትሰሰር ያላቸው ምንጮች እንዳሉት፣ ሥራ ፈላጊዎች በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ከ 5 እስከ 15 ዓመታት ያህል ተምረው ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ በሚመጡበት ወቅት እንደየሥራ ዘርፉ ክፍያ ካልከፈሉ ቅጥር የማይታሰብ ነው።

አሁን ላይ በቤተክርስቲያኒቱ ያለው የቅጥር ሁኔታ በሕግና በስርዓት ማስታወቂያ ወጥቶ ሰዎች አመልክተውና ተወዳደረው ሳይሆን ገንዘብ የመክፈል አቅም ያላው የሚቀጠርበትና ሥራ የሚያገኙበት እንደሆነ እነዚሁ ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል።

ዋዜማ ካነጋገረቻቸው በርካታ ሥራ ፈላጊዎች መካከል አንዱ እንዳሉት አቋቋም፣ ድጓ እና ቅኔ የተሰኙትን የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት አጠናቀውና አስመስክረው ሥራ ፍለጋ በከተማይቱ ውስጥ ባሉ በርካታ አቢያተ ክርስቲያናት ቢያመለክቱም “እጅ መንሻ ክፍያ ካልፈጸምክ ቅጥር የለም” መባላቸውን ተናግረዋል።

ሥራ ፈላጊው የመጡት ከአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረ ብርሃን ከተማ እንደሆነ የተናገሩ ሲሆን፣በዚያ አካባቢ ባሉ ገዳማትና አድባራት ተዘዋውረው አስፈላጊውን የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት መማራቸውን አስረድተዋል።

ሆኖም ሥራ ፍለጋ ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ ነገሩ እንዳሰቡት እንዳልሆነላቸውና ሥራ ለመቀጠር 3 መቶ ሺሕ ብር ክፍያ መጠየቃቸውን ይገልጻሉ። በተለይም ከተማይቱ ውስጥ ባሉ ታላላቅ አድባራትና ገዳማት ለመቀጠር የሚጠየቀው የገንዘብ መጠን ደግሞ ለሰሚው ግራ የሚያጋባ ነው ሲሉ ትዝብታቸውን አጋርተዋል።

ከዚህ ቀደም በቤተክርስቲያኒቱ የአገልጋይ ቅጥር ሲፈጸም ቀድሞ የሚነሳው ጥያቄ ለማገልገል የሚያበቃው ምን ትምህርት ተምሯል?፣ ሥነ ምግባሩስ እንዴት ነው?፣ የሚሉ ጥያቄዎች ነበሩ ሲሉም ጠቁመዋል። አሁን ግን ጥያቄው በቀጥታ ምን ያህል የመክፈል አቅም አለው የሚል ሆኗል ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ ይገልጻሉ።

ተቀጣሪን ከቀጣሪ የሚያገናኙ ደላላዎች የጉዳዩ ዋና ተዋናዮች ሲሆኑ ሥራ ፈላጊዎቹን ካሉበት ፈልገው በሀገረ ስብከት ውስጥ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር በቀጥታ የሚያገናኟቸው ሲሆን፣ ደላሎቹም ከሚገኘው ገንዘብ ላይ ድርሻ እንዳላቸው አስረድተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ስሜ አይጠቀስ ያሉ አንድ ግለሰብ እንደተናገሩት በአዲስ አበባ ውስጥ ባለ አንድ ትልቅ ደብር በመሪጌታነት የሥራ መደብ የተቀጠሩት ከሁለት ዓመታተ በፊት መሆኑን ያስረዳሉ።

በዚያ ወቅትም አጠቃላይ የቅጥሩን ሂደት ለመጨረስ 350 ሺሕ ብር በየደረጃው ላሉ የቤተክርስቲያኒቱ አመራሮች እጅ መንሻ ክፍያ መፈጸማቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ይህ ጉዳይ አሁን የጀመረ ሳይሆን የሰነበተና ቀስ በቀስ ስር እየሰደደ መጥቶ አሁን ላይ ሕጋዊ እስኪመስል ድረስ በግልጽ የሚከናወን የአደባባይ ምስጢር ነው ።

እጅግ ከባድ የሚባለውን የቤተክርስቲያኒቱን ትምህርት ለበርካታ ዓመታት የተማሩና እውቀቱ ያላቸው ሰዎች የተጠየቁትን ክፍያ መፈጸም ባለመቻላቸው በአዲስ አበባ ከተማ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሉ በርካቶች ናቸው ።

ከእነዚህ መካከል በከተማይቱ አደባባዮች ላይ ሎተሪ የሚያዞሩ፣ በጥበቃ ሥራ የሚተዳዳሩ፣የቀን ሥራ የሚሰሩ በየአቢያተክርስቲያናቱ ደጅ እየጠኑ ያሉ ሰዎች ቁጥራቸው ብዙ ነው።

ስራ ፈላጊዎቹ ከአመታት ትምህርትና ልምድ በኋላ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡት በክልሎችና በገጠር ያሉ አድባራት አዲስ ሰራተኛ ለመቅጠር የሚያስችል አቅምና ፍላጎት ስለሌላቸው መሆኑንም ይናገራሉ። 

ይህን ጉዳይ ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጀምሮ፣የሀገረ ስብከቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ፣የየመምሪያው የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በየደረጃው ያሉ ሰዎች የሚያውቁትና ተደጋጋሚ አቤቱታ የቀረበበት ነው ሲሉ ጉቦ ተጠይቀናል ያሉት ግለሰቦች አስረድተውናል።

ሆኖም ግን ይህን ችግር ለመፍታትና እንደዚህ አይነት አሰራር ለማስቆም አንዳችም ጥረት ሲደረግ ተመልክተው እንደማያውቁ ያስረዳሉ።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸው አንድ ሌላ ግለሰብ ደግሞ በስብከተ ወንጌል የሥራ ዘርፍ ለመቀጠር አመልክተው 4 መቶ ሺሕ ብር ክፍያ መጠየቃቸውን አውስተዋል።

ሆኖም ይህን ያህል ገንዘብ የመክፈል አቅሙ ስለሌላቸው እንደተውት ገልጸዋል።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የአዲስ አበባ አገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ የሆኑትን ሊቀ ማእምራን የማነ ዘመንፈስቅዱስን ጠይቃለች።

“ከሠራተኛ ቅጥር ጋር ተያይዞ እንደዚህ አይነት ችግሮች የሉም ማለት አይቻልም”  ብለዋል ዋና ሥራ አስኪያጁ።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በዚህ ሰዓት ሙሉ ለሙሉ የሠራተኛ ቅጥር መፈጸም አቁሟል ሲሉ አክለዋል።

ከዚሁ ችግር ጋር ተያይዞ፣ እሳቸውን ጨምሮ ከጠቅላይ ቤተ ክህነት እንዲሁም ከአዲስ አበባ አገር ስብከት የተወጣጡ አባላትን ያካተተ ኮሚቴ መቋቋሙን ለዋዜማ ገልጸዋል።

ችግሩን ለመቅረፍም ከዚህ በኋላ አድባራት ራሳቸው ማስታወቂያ አውጥተው ሰራተኞችን አወዳድረው ቅጥር እንዲፈጽሙ ለማድረግ የሚያስችል አሰራር እንዲፈጠር ውይይት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከሥራ ቅጥር ጋር ተያይዞ ቅሬታ ከሚያነሱ ሰዎች ጋርም የሚመለከታቸው የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት፣ ውይይት መካሄዱን ሊቀ ማእምራን የማነ ገልጸዋል።

በሌላ በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት የተማሩ በሙሉ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ አድባራትና ገዳማት ሥራ ለመቀጠር ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ከተማይቱ በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚፈልሱ ጠቁመዋል።

ይህ ደግሞ አሁን ለሚነሳው ችግር እንዲጋለጡ ትልቁን ሚና እንደሚጫወት ሥራ አስኪያጁ አብራርተዋል።

በተጨማሪም ሥራ አስኪያጁ ከሦስት ወራት በፊት ከቤተክርስቲያኒቱ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የአዲስ አበባን አገረ ስብከት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በሥራ አስኪያጅነት የመምራት እድል እንደነበራቸው ተናግረዋል።

በዚህ ወቅት ወደዚሁ ኃላፊነት ድጋሚ ሲመጡ ተቋሙ በብዙ መልኩ ተዳክሞና የተለያዩ የአሰራር ችግሮች አጋጥመውት እንዳስተዋሉ አንስተዋል።

ከነዚህም መካከል በአገረ ስብከቱ አላስፈላጊ የሆነ የሠራተኛ ቅጥር ተከናውኖ መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

እሳቸው ወደ አገረ ስብከቱ በሥራ አስኪያጅነት ሲመጡ፣ ከ 1 መቶ በላይ ፣በአለቅነት፣ በሂሳብ ሹምና በፀሀፊነት ጭምር የተመደቡ ትርፍ ሰራተኞች ደሞዝ ይከፈላቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት “የአዲስ አበባ አገረ ስብከት የታወከ፣ጩኽት የበዛበትና መረጋጋት የተሳነው ነው” 

“ወደ ኃላፊነት ስመጣ እንደ ተቋም ፈርሶ ነው ያገኘሁት” ሲሉ ተደምጠዋል። [ዋዜማ]