የኢትዮጵያ መንግስት በኦሞ ወንዝ ላይ ያስገነባው በአፍሪካ በዓይነቱ ለየት ያለ እንደሆነ የሚነገርለትና በሙሉ አቅሙ ማምረት ሲጀምር አንድ ሺህ ስምንት መቶ ሰባ ሜጋ ዋት እንደሚያመነጭ የሚጠበቀው ግልገል ጊቤ ሶስት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት የሙከራ ጊዜውን አልፎ መደበኛ ሥራውን ከጀመረ አንድ ወር አስቆጥሯል፡፡ የጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔ ጉዳዮች አማካሪ ሚኒስትር የሆኑት የቀድሞው የውሃ፣ መስኖና ኃይል ሚንስትር አለማየሁ ተገኑ ግልገል ጊቤ ሦስት የሃገሪቱን የኃይል አቅም በሁለት መቶ ሰላሳ አራት በመቶ እንደሚያሳድግ በቅርብ ገልጸዋል፡
ሆኖም ፕሮጀክቱ ይፋ ከተደረገበት ወቅት አንስቶ የአካባቢ ጥበቃ ባለሙያዎች ግዙፍ ከባቢያዊ ቀውስ እንደሚያስከትል፣ በተለይም በዩኔስኮ ዓለም ዓቀፍ ቅርስነት በተመዘገበው ቱርካና ሃይቅ ላይ ከባድ አደጋ እንደሚደቅንና በጠቅላላው በኦሞ ወንዝ ታችኛው ተፋሰስ የሚኖሩ ሕዝቦችን ሕልውናም አደጋ ላይ እንደሚጥል ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ በተለይ ሰሞኑን የሙከራ ጊዜውን ጨርሶ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ተከትሎ ይኸው የአካባባቢ መብት ተቆርቋሪዎች የተቃውሞ ድምጽ እየተሰማ ነው፡
(ዳንኤል ድርሻ የሚከተለውን ዘገባ አዘጋጅቷል መሰሉ ንጉስ ታቀርበዋለች፣ አድምጡት)
ሃይል ማመንጫው ከሚያመነጨው ግማሽ ያሕሉን ኃይል ለሃገር ውስጥ የሚያውለው ግልገል ጊቤ ቀሪውን ደግሞ ለኬንያ፣ ለሱዳንና ለጅቡቲ ለመሸጥ ማቀዱን የኢትዮጵያ መንግስት አስቀድሞ ነበር ያሳወቀው፡፡ በተለይ ለኬንያ ሊሸጥ የታቀደው አምስት መቶ ሜጋ ዋት በመሆኑ ከሌሎች ጎረቤት ሀገሮች ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል፡፡ ይሕም አካባቢያዊ የኃይልና ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማጠንከር እንደሚረዳ መንግስት ከመግለጽ የተቆጠበበት ወቅት የለም፡፡
ሆኖም ለጊዜውም ቢሆን የኦሞ ወንዝ ፍሰት አቅጣጫ በመቀየሩ፣ በዩኔስኮ በሰው ልጅ መገኛነት በዓለም ዓቀፍ ቅርስነት በተመዘገበው ቱርካና ሃይቅና በተፋሰሱ ዙሪያ በሚኖሩ የኢትዮጵያና ኬንያ አርብቶ አደር ህዝቦች ህልውና ላይ ከባድ አደጋ ይደቅናል በማለት የአካባቢ መብት ተቆርቋሪዎች ድምጻቸውን በማሰማት ላይ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የታችኛው ኦሞ ሸለቆ ላይ የሚገነቡ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶች የቱርካና ሐይቅን የውሃ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እያሟጠጠ መምጣቱንና የሕዝቦችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች በመታየት ላይ መሆናቸውን የሚገልጹት እንደ ሂዩማን ራይትስ ዎች የመሳሰሉ አካላት ግን “ ጊዜ የለንም ወይም ምንም ጊዜ አልቀረንም” በሚለው ማሳሰቢያቸው ገፍተውበታል፡፡
በአንፃሩ የግልገል ጊቤ ሶስትን የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥና ለመግዛት የተዘጋጁት የኢትዮጵያና የኬንያ መንግስታት ስለ ፕሮጀክቱ ጠቀሜታ እንጂ ጉዳት ሲናገሩ አይሰሙም፡፡
ከሰሞኑ ግብጽን የጎበኙት አዲሱ የኢትዮጵያ መስኖና ኃይል ሚኒስትር ሞቱማ መቃሳም በካይሮ ቆይታቸው “አል ሞኒተር” ከተሰኘው የሃገሪቱ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም ግልገል ጊቤ ሶስትን በተመለከተ የተለመደውን የመንግስታቸውን አቋም ነው ያንጸባረቁት፡፡
አበዳሪዎችና ለጋሾች ፕሮጀክቱን ለመደገፍ ባለመፍቀዳቸው በገንዘብ እጥረት ሥራው ሲጓተት የቆየው ግልግል ጊቤ ባለፈው ሐምሌ የሙከራ የኃይል ማመንጨት ሥራ መጀመሩ በይፋ ተገልጾ የነበረ ቢሆንም እስካለፈው ጥቅምት ወር ድረስ ግን ኃይልን በመደበኛነት ማመንጨት ሳይጀምር መቆየቱን የመረጃ ምንጮች ያገልፃሉ፡፡ አሁንም ሙሉ በሙሉ ሥራው ተጠናቅቆ አስሩም ሃይል አመንጪ ተርባይኖች በቀጣዮቹ ስድስት ወራት ተጠናቀው ኃይል ያመነጫሉ የሚለው ግምት አጠራጣሪ መሆኑን አንዳንድ የዘርፉ ባለሙያዎች በመግለፅ ላይ ናቸው፡፡
ግድቡ ከወዲሁ በቱርካና ሐይቅ ላይ ከፍ ያለ ተጽዐኖ ማሳደሩን የገለጸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ተቋም ሂዩማን ራይትስ ዎች ከሰሞኑ ባወጣው ባለ ዘጠና ስድስት ገጽ ሪፖርት የአየር ንብረት ለውጥ ከአካባቢው የልማት እንቅስቃሴ ጋር ተዳምሮ የቱርካና ነዋሪዎችን ሕይወት ለምስቅልቅል በመዳረግ ላይ መሆኑን ተንትኗል፡፡
የሂዩማን ራይትስ ዎች ዳይሬክተር ጀምስ አሞስ እንዳሉት ̋የቱርካና ሐይቅ በመድረቅ ሥጋት ውስጥ ይገኛል፤ የባለሃገሬው የሐይቁ አካባቢ ነዋሪዎችም ጤና እና ሕልውና በቋፍ ላይ ይገኛል፡በታችኛው ኦሞ ወንዝ ሸለቆ የሚካሄዱ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችና እና ለስኳር ፋብሪካዎች መስኖ ተብለው የተመሰረቱ የሸንኮራ አገዳ እርሻዎች የቱርካና ሐይቅን የውሀ መጠን በእጅጉ እንደቀነሱም ሪፖርቱ ያብራራል፡፡
ከዚህም ባሻገር በአካባቢው የአየር ሙቀት ጭማሪው በአስደንጋጭ ሁኔታ መጨመሩ ከብቶች የሚሰማሩበትን የግጦሽ መሬት ቦታ ማሳጣቱ ከላይ ከተጠቀሱ ችግሮች ጋር ተዳምረው በነዋሪዎች ዘንድ ወደፊት ግጭት እንዲፈጠር የማድረግ ዕድሉ የሠፋ መሆኑን የሰብዐዊ መብቱ ተሟጋቹ ቡድን በሪፖርቱ አብራርቷል፡፡