ዋዜማ ራዲዮ-በኢትዮጵያ ባለፉት አራት አመታት በተለይም የመንግስት ለውጥ ከተደረገ ወዲህ የወጭና ገቢ ኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎች ቁጥርና የግብይት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን የጉምሩክ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡
የኮንትሮባንድ መጨመር ጋር ተያይዞ እየታየ የመጣው ችግር በተለይም ለየት ባለ መልኩ የተዋናኞች አደረጃጀት እጅግ አደገኛ፣ አሳሳቢና ውስበስብ እየሆነ በመምጣቱ ሁሉም የመንግስት መዋቅር ከችግሩ ጋር ተመጣጣኝ መልስ ለመስጠት በሚያሰችል መልኩ ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባ የጉምሩክ ኮሚሽነር አቶ ደበሎ ቃበታ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽነሩ ኮንትሮባድ ንግድ ዝውውር ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት ማንነትና ምንነት ለመረዳት በሚያዳግት መልኩ እየተንቀሳቀሱ ወደ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሶማሌያና ወደ ኬንያ አካባቢ ያሉ መተላለፊያዎች ላይ ችግሩ መባባሱን የገለጡት ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም የገቢዎች ሚንስትር የአስር ወራት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ለህዝብ ተወካዮች ምክርቤት ባቀረበበት መድረክ ነው፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ከኮንትሮባንድ አዘዋዋሪዎች ጋር ተመጣጣኝ የሆነ አደረጃጀት እንዲዘረጋ የጠየቁት ኮሚሽነሩ መንግስት በተለያየ መልኩ የጸረ ኮንትሮንድ ግብረ ሃይል አቋቁሞ የስምሪት አቅሙን ቢያሰድግም የኮንትሮባድ አዘዋዋሪዎች መሳሪያ ታጥቀው ጠንካራ መኪኖቸን በመያዝ የሚታዩት ክስተቶች ተራ እንዳልሆኑ ግንዛቤ ሊያዝ ይገባል ሲሉ ኮሚሽነሩ አሳስበዋል፡፡
የችግሩ አሳሰቢነት ከፍተኛ መሆኑንና ለዚህም በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግስት አስተዳድር አካላት ዝግጁነትና ጠንካራ አመራር እንደሚያስፈልግ የገለጹት ኮሚሽነሩ አልፎ አልፎ በመንግስት ተሸከርካሪዎች፣ በቀይ መስቀልና በጸጥታ አካላት ተሸከርካሪዎች ጭምር በመታገዝ የኮንትሮባንድ ዝውውሩ መባባሱን አክለው ገልጸዋል፡፡
ለአብትም ባለፉት አስር ወራት ብቻ የወጭና ገቢ ኮንትሮባንድን ለመከላከል በተደረገ ስራ 3.5 ቢሊዮን ብር የሚገመት የገቢ ኮንትሮ ባንድ ዕቃዎች እንዲሁም ግማሽ ቢሊዮን የሚጠጋ የወጭ ኮንትሮባንድ ዕቃዎች በድምሩ 4.4 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የኮንተሮባንድ ሸቀጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን የገቢዎች ሚንስተሩ አቶ ላቀ አያሌው ገልጸዋል፡፡
ከ2013 ዓ.ም ጋር ሲነጻጸር የገቢ ኮንትሮባንድ በ54 በመቶ ማደጉንና የወጭ ኮንትሮባንድ ደግሞ በ 20 በመቶ መቀነሱን አክለው ተናግረዋል፡፡
በንግድ ማጭበርበርና በኮንትሮባንድ ስራዎች በተለይም በኢንተሌጀንስ ስራዎች 850 ሚሊዮን ብር፣ በድንገተኛ ፍተሻ 690 ሚሊዮንብር፣ በገቢ ኮንትሮባንድ 3.5 ቢሊዮን ብር በወጭ ኮንትሮባንድ 490 ሚሊዮን ብር፣ ከድህረ ዕቃ አወጣጥ ኦዲት 7.7 ቢሊዮን ብር፣ ከቀረጥ ነጻ አጠቃቀምን በመቆጣጠር 488 ሚሊዮን ብር፣በመደበኛ ሰነድ ፍተሸ 25 ቢሊዮን ብር በአጠቃላይ ባለፉት አስር ወራት 39 ቢሊዪን ብር ማዳን መቻሉንና የወጭና ገቢ ኮንትሮባንድ መጠን በአማካኝ በ 41 በመቶ ማደጉን አቶ ላቀ አስረድተዋል፡፡
በበጀት አመቱ 10 ወራት ውስጥ ከአገር ውስጥ ገቢ 168.7 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ከውጭ ንግድና ቀረጥና ታክስ 118 ቢሊዮን ብር በድምሩ 282.5 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡንና 82 ቢሊዮን ብር የሚገመቱ ሸቀጦች ከቀረጥ ነጻ ወደ አገር ውስጥ መግባታቸውም በሪፖርቱ ተመልክቷል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]