• ሌሎች የፋኖ፣ የሸኔና የትግራይ ጦር አባል ናቸው የተባሉ በድምሩ 900 ያህል ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል

ዋዜማ- የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ባለፉት ሁለት ወራት ውስጥ ብቻ 224 “የሻዕቢያ መንግሥት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች” ናቸው ያላቸውን ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ዋዜማ ከፀጥታና ደህንነት ምንጮች ስምታለች።

ቢሮው፣ ወደ ከተማዋ የገቡ “የትግራይ ተዋጊ ኃይሎች”፣ “የፋኖ” እና “የሸኔ” አባላትንም መያዙን ገልጿል። የሰላምና ጸጥታ አስተዳደር ቢሮ ይህን ያስታወቀው ማክሰኞ መጋቢት 23 ከማዕከልና ከወረዳ ከተወጣጡ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ አመራሮች ጋር ባደረገው ውይይት ላይ ነው።

በከንቲባ ጽህፈት ቤት አዳራሽ የተካሄደው ስብሰባ፣ በከተማ አስተዳደሩ የሰላምና ጸጥታ ዘርፍ የሦስተኛ ሩብ ዓመት ዕቅድ አፈጻጸምን የተመለከተ ነበር።

ለመገናኛ ብዙሃን ዝግ ሆኖ የተካሔደው ውይይት፣ የከተማዋ ወቅታዊ የሰላም እና ጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ የቢሮው ኃላፊ ሊዲያ ግርማ እና ሌሎች አመራሮች ማብራሪያ አቅርበውበታል።

ውይይቱ ባብዛኛው ያተኮረው፤ የቢሮው የጸጥታ ሥራዎች ዘርፍ ምክትል ኃላፊ ተስፋዬ ደንድር፤ “ወቅታዊ የከተማችን የጸጥታ ሁኔታና የአመራሩ ሚና” በሚል ርዕስ ባቀረቡት የአፈጻጸም ግምገማ ጽሁፍና የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ወራት “በጽንፈኛ ኃይሎች” ላይ ያደረገውን “ክትትል” እና “የወሰዳቸውን ርምጃዎች” በተመለከተ ለተሳታፊዎች በሠጡት ማብራሪያ ነበር።

ምክትል ኃላፊው፤ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ውስጥ “አስተማማኝ ሰላም” መኖሩን ቢጠቅሱም፤ በአዲስ አበባ “የተለያዩ ፍላጎት ያላቸው የሽብር እና የጽንፍ ኃይሎች እኩይ ዓላማቸውን ለማሳካት እንቅስቃሴ የሚያደርጉባት” ከተማ ናት በማለት ተናግረዋል።

ተስፋዬ፤ ለከተማዋ ሰላም እና ጸጥታ ስጋት እንደሆኑ ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል “ጽንፈኛ” እና “የሽብር ኃይል” ብለው በጠሯቸው አካላት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል።

“በሃይማኖቶች መካከል ያለው ሁኔታ” እንዲሁም “በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ የተለያዩ ፍላጎቶችም” ተስፋዬ በስጋት ምንጭነት የጠቀሷቸው ሌላኛዎቹ ጉዳዮች ናቸው። በእነዚህ የስጋት ምንጮች ላይ “በተጠንቀቅ ቆሞ” መስራት እንደሚያስፈልግ ከከተማዋ የተለያዩ መዋቅሮች ለመጡት አመራሮች አስገንዝበዋል።

ምክትል ኃላፊው፣ የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት ሁለት ወራት ባደረገው “ክትትል እና ቁጥጥር” የተለያዩ ቡድኖች አባላት ናቸው የተባሉና “ጽንፈኛ ሲሉ የጠሯቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው በቁጥጥር ስር ውለዋል ብለው ከዘረዘሯቸው ግለሰቦች መካከል 356ቱ “የፋኖ አባላት” ናቸው። የከተማዋ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ በብዙ ክፍለ ከተማዎች ላይ የሚያዙ “ወንጀለኞች” ከፋኖ ኃይሎች ጋር ግንኙት እንዳላቸውና የቡድኑ የመረጃ ምንጭ ሆነው ሰርገው የገቡ አካላት ናቸው” ሲሉ ከስሰዋል።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው ተስፋዬ ባቀረቡት ዝርዝር ውስጥ፣ በቁጥር ብዛት በሁለተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጡት “የሻዕቢያ መንግሥት ተልዕኮ አስፈጻሚዎች” ተብለው የተጠቀሱ 224 ተጠርጣሪዎች ናቸው።

ሌሎች 201 ያህሉ መንግስት “ሸኔ” እያለ የሚጠራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት አባላት ሲሆኑ፣ 106 ያህል ደሞ የትግራይ ታጣቂ ኃይል አባላት ናቸው ተብሏል። ተጠርጣሪዎቹ ግለሰቦች በከተማዋ ውስጥ ምን ዓይነት ድርጊት ሲፈጽሙ እንደነበር ግን ኃላፊዎቹ በዝርዝር አልጠቀሱም።

ሆኖም፤ “የኤርትራ መንግሥትን ጨምሮ ሁሉም ኃይሎች በተለያየ ስልት የመንግስት አገልግሎቶችን ለማስተጓጎል ፊት ለፊት መጋፈጥ ባይችሉ እንኳን፣ መንግሥትን ከሕዝብ በሚነጥሉ የተለያዩ አጀንዳዎች እንዲሁም በንጥቂያና ዝርፊያ ላይ ተሠማርተዋል” ሲሉ ከስሰዋል።

ምክትል ኃላፊው፤ “887 ግለሰብ ሲባል ቀንደኛ ቀንደኛውን ነው የያዝነው። አንዳንዶቹ በውጊያ ላይ የነበሩና ማንነታቸውን ቀይረው የመጡ ናቸው” በማለትም በቁጥጥር ስር ስለዋሉት ግለሰቦች አብራርተዋል።

ሃላፊው አያይዘውም፤ “ከዚህ የምንወስደው ትምህርት አለ፤ አንድ ግለሰብ ሰፈር በሙሉ መበጥበጥ ይችላል። 887 ግለሰብ ማለት እድል ቢያገኙ እዚህ ከተማ ላይ ምን ሊፈጠር እንደሚችል ማሰብ ነው” በማለት የአስተዳደሩን የስጋት ደረጃ አስረድተዋል።

የከተማዋ ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው፤ “በበርካታ ክፍለ ከተማዎች ላይ ተደጋጋሚ ወንጀል እና የተደራጀ ዝርፊያ ውስጥ ሙለ በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ የጽንፈኛ ኃይሎች አባላት የተገኙበት ሁኔታ አለ። ይሄ ለኛ ትልቅ ደወል ነው” በማለት የተስፋዬን ስጋት አጠናክረዋል።

በተያዘው የመጋቢት ወር ብቻ በከተማዋ “በወንጀል ምክንያት 36 ገደማ ሰዎች መሞታቸውን” የቢሮ ኃላፊዋ ተናግረዋል። ሊዲያ፤ “በቀጣይ መታረም አለባቸው” ያሏቸውን ጉዳዮች ጠቅሰው በውይይቱ ለተሳተፉ የሰላም እና ጸጥታ ዘርፍ አመራሮች መመሪያዎች ሰጥተዋል።

የቢሮ ኃላፊዋ ከሰጧቸው መመሪያዎች አንዱ፤ ሰነድ አልባ የኤርትራ ዜጎችን የተመለከተው ይገኝበታል። ከሁሉም በላይ ሰነድ አልባ ከሆኑ ኤርትራዊያን እና ከትግራይ የቀድሞ ተዋጊዎች ግማሾቹ በተቀናጀ መልኩ ዝርፊያ ላይ የገቡ ናቸው ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ፤ ይህን ጉዳይ “በደንብ ማየት ያስፈልጋል” ሲሉ ለተሰብሳቢዎቹ በአጽንዖት አሳስበዋል።

የከተማ አስተዳደሩ በሚመለምላቸው “የሰላም ሠራዊት” አባላት ውስጥ “ሰርገው የገቡ የፋኖ እና የሸኔ አባላት” እንደተያዙም ሊዲያ አክለው ተናግረዋል። የከተማ አስተዳደሩ መዋቅሮች ይህንን ምልመላ ሲያካሂዱ “በየጊዜው የሂደቱን ጤናማነት” እንዲፈትሹም ሊዲያ አሳስበዋል።

በውይይቱ ላይ “የጽንፈኛ እና የሽብር ኃይሎችን ወቅታዊ ስልት የተረዳ ብቁ አመራር እየሰጡ ቀድሞ በማምከን” ላይ የታዩ ክፍተቶች ሊሻሻሉ እንደሚገባም ተገልጧል። [ዋዜማ]