ዋዜማ- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ለሚያካሂደው የተማሪዎች ምገባ ለአንድ ተማሪ በቀን 23 ብር የነበረውን የምግብ በጀት ዘንድሮ ወደ 32 ብር ከፍ ማድረጉን ዋዜማ ተረድታለች።
አስተዳደሩ የዋጋ ማሻሻያ ያደረገው በወቅቱ ባለው የግብዓት ዋጋ መጨመር ምክንያት እንደሆነ ጠቅሷል።
በተጨማሪም በዚህ ዓመት በተማሪዎች የምግብ ዝርዝር (ሜኑ) ላይም መጠነኛ ማሻሻያ የተደረገ ሲሆን፣ በሳምንት አንድ ቀን ቁርስ ሰዓት እንቁላል ፍርፍር ይቀርባል። በሌሎቹ ቀናት ባብዛኛው ባለፈው ዓመት የነበሩት ከአትክልት እና ከእንጀራ የተዘጋጁ ምግቦች ይቀጥላሉ።
ዋዜማ በተመለከተችው የዘንድሮ ዓመት የተማሪዎች የምገባ ዝርዝር ውስጥ ስጋ ነክ ምግብ አልተካተተም።
ዋዜማ በተማሪዎች ምገባ በሃላፊነት ላይ ከሚሰሩ ምንጮቿ ባገኘችው መረጃ፣ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በመመሪያ የተደነገገ ለተማሪዎች መቅረብ ያለበት የምግብ መጠን እንዲቀንስ ሲደርግ፣ የምግብ ዝርዝሩም በአግባቡ አይተገበርም። ይህም ለብልሹ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን ዋዜማ ተረድታለች።
የተማሪዎችን ምገባ ለማከናወን የተዘጋጀው መመሪያ ለመዋዕለ ህጻናት እና ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች በቁርስ እና ምሳ ሰዓት መቅረብ ያለበትን የዳቦ እንዲሁም የእንጀራ መጠን በግራም ያስቀምጣል።
በዚህ መመሪያ መሰረት የሥራ ዕድል የሚፈጥርላቸው እናቶች የገቢ ምንጭ የሌላቸው ወይም ልጃቸውን የመንግሥት ትምህርት ቤት ውስጥ የሚያስተምሩ መሆን አለባቸው።
ከተማ አስተዳደሩ በስሩ ባሉ መደበኛ የመንግስት ትምህርት ቤቶች በቀን ለሚማሩ መዋዕለ ህጻናት እና የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ቁርስ እና ምሳ ምግብ ያቀርባል።
በተጨማሪም በየትምህርት ከትምህርት ቤት ሲመለሱ መመገብ ለሚቸገሩ ልጆችን በመለየት እራት እንዲቋጠርላቸው ይደረጋል።
ከአንደኛ ወደ ኹለተኛ ደረጃ ከተሸጋገሩ በኋላም፣ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግር ያለባቸው ተማሪዎች ተመርጠው በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የመንግሥት የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አቅንተው ቁርስ እና ምሳ መመገብ ይችላሉ። ይህ ግን በአግባቡ ተግባራዊ እየተደረገ እንዳልሆነ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጭ ገልጸዋል።
በ2012 ዓ.ም የተጀመረው የተማሪዎች ምገባ የተማሪዎችን የመድገም እና የማቋረጥ ምጣኔ በመቀነስ ረገድ ገንቢ አስተዋጾ ማድረጉ ይገለጻል።
ባለፈው ዓመት ከ800 ሺሕ በላይ የመዋዕለ ሕጻናት እና የአንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ተመጋቢ እንደነበሩ እና ከ17 ሺሕ በላይ እናቶችም የሥራ ዕድል እንዳገኙ ተገንዝበናል።
የግል ትምህርት ቤቶች የሚጠይቁትን ከፍተኛ የመማሪያ ክፍያ ተከትሎም ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከግል ትምህርት ቤቶች ወደ መንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚዛወሩ ተማሪዎች ቁጥር በርካታ መሆኑን ተረድተናል። [ዋዜማ]