• ከኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ በሚደርሱ የንብረት ጉዳቶች፣ የአሽከርካሪዎች ቅጣት ወደ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች እየመጣ መቸገራቸውን ሀላፊዎቹ ተናግረዋል
Photo credit- Fortune Addis

ዋዜማ- በ 5 እጥፍ ጭማሪ የተደረገበት አዲሱ የሶስተኛ ወገን የተሸከርካሪ መድን ፖሊሲ ከነሀሴ 16 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ በማድረግ በሰው ላይ የሚደርስ የሞት እና የአካል ጉዳት በፊት ከነበረው 40ሺ ብር የካሳ ክፍያ ወደ 250 ሺ ብር ከፍ እንዲል ተደርጓል። 

በተጨማሪም በንብረት ላይ ለሚደርስ ኪሳራ በፊት 100 ሺ ብር የነበረውን አሁን 200ሺ ብር እንዲሁም ለአስቸኳይ የህክምና አገልግሎት 15ሺ ብር  እንዲሆን ተወስኗል።

ዋዜማ የተመለከተችው  አዲሱ “በሶስተኛ ወገን የተሽከርካሪ አደጋ የመድን ፖሊሲ የአረቦን ተመን እና የካሳ መጠን ክፍያ ደንብ” እንደሚገልጸው ከዚህ በፊት ይከፈል የነበረው አረቦን (premium) ክፍያ ከ500 ብር ጀምሮ የነበረ ሲሆን በአዲሱ የፕሪሚየም ክፍያ ዝቅተኛው  “1600 CC ኮድ 2” መኪና ከሆነ 2641 ብር ጀምሮ ፤ ባለ 400 ኩንታል ከባድ የጭነት መኪና 12ሺ 728 ብር ተደርጓል።

በተጨማሪም የህዝብ አገልግሎት ኮድ 3 ሚኒባስ 11ሺ 292 ብር እና አውቶቡሶች በአይነታቸው በመለየት ከ7ሺ እስከ 11ሺ 500 ብር ፕሪሚየም እንደሚከፈል በሰነዱ ተቀምጧል።

በስራ ላይ የነበረዉና የሚኒስትሮች ምክርቤት በአዋጅ ቁጥር 799/2002 የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ  ወገን መድን ዋስትና የአርቦን መጠንና የመድን ፈንድ ታሪፍን በተመለከተ ያስተላለፈው ዉሳኔ በአዲሱ ደንብ ተሽሯል።

የተሻሻለውን ደንብ ሲያዘጋጁ የነበሩት የመንገድ ደህንነት እና የመድን ፈንድ አገልግሎት ኬኒያ ከሚገኘው ACTSERV actuarial የተባለ ኩባንያ ጋር በመሆን የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እድገት፣ እየደረሰ ያለውን የጉዳት መጠንና በርካታ ጉዳዮችን በማጥናት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ነጻነት ለሜሳ ለዋዜማ ተናግረዋል።

አቶ ለሜሳ አክለውም የተሻሻለው የሶስተኛ ወገን ፖሊሲ በይበልጥ የሚጠቅመው ጉዳት ለሚያጋጥመው ህብረተሰብ ቢሆንም አሽከርካሪዎችንም የሚጠቅም ነው ብለዋል።

” አሽከርካሪዎች የሚከፍሉት አረቦን በአንድ ጊዜ በ5 እጥፍ በማሳደግ ብሩ ከፍ የተደረገበት ዋና ምክንያት ለጉዳት የሚከፈለው የካሳ ክፍያ አነስተኛ በመሆኑ ነው። የደንቡን ተፈጻሚነት ቀስ በቀስ እንዲሆን ያለተደረገበት ምክንያት ደግሞ አሽከርካሪዎች ጉዳት ሲያደርሱ የሚጠየቁት የገንዘብ መጠን እጅግ ከፍተኛ እየሆነ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መክፈል ከሚጠበቅባቸው ክፍያ በላይ እየተጠየቁ በመሆኑ ነው” ብለዋል።

በተጨማሪም በንብረት ላይ የሚደርስ ጉዳት በሚኖርበት ጊዜ ንብረት የወደመበት ሰው የኢንሹራንስ ኩባንያ የሚከፍሉት 100 ሺ ብር  በቂ ባለመሆኑ ፍርድቤት ድረስ በመሄድ የአሽከርካሪውን ንብረት በማሳገድ ለአሽከርካሪዎች እንግልት እየፈጠረ መሆኑን ሀላፊው አስረድተዋል።

በአዲሱ ጭማሪ ግን ቢያንስ የተሻለ የካሳ ክፍያ ስለሆነ  አሽከርካሪዎች የአረቦን ክፍያ ጭማሪ ላይ ቅሬታ ከማቅረብ የካሳ ክፍያውን መጨመሩ ሊያስደስታቸው ይገባል ሲሉ አቶ ነጻነት ተናግረዋል።

ዋዜማ ያነጋገራቻቸው ሌላ የኢንሹራንስ ባለሙያ በተመሳሳይ አዲሱ ተመን ለህብረተሰቡ እንደሚጠቅም በመግለጽ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ መታየት ያለበት ጉዳይ በኮሪደር ልማት ምክንያት ተሽከርካሪዎች የሚቀጡት ቅጣት በተዘዋዋሪ ወደ ኢንሹራንስ ኩባንያ እየመጣ ነው።

በኮሪደር ልማት ምክንያት አሽከርካሪው ላይ የሚደርሰውን ቅጣት በተመለከተ ዋዜማ የአቶ ነጻነትን ምላሽ የጠየቀች  ሲሆን፣ በምላሻቸውም ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውድመት ሲኖር ለወደመው ንብረት ካሳ ለመክፈል የተቋቋሙ እንጂ የአሽከርካሪዎችን ደንብ ጥሰት ቅጣት የሚከፍሉ አይደሉም ብለዋል። 

ነገር ግን ጉዳቱ የሚደርሰው በእጽዋት፣ በመብራት ምሰሶና በመሳሰሉት ላይ ከሆነ በፍትሐ ብሄር ህግ አሽከርካሪው ያደረሰውን የንብረት ጉዳት ክፍያ ተመን በማስላት የሚከፍለበት መንገድ መኖሩን ተናግረዋል። [ዋዜማ]