Negele Borana village road

ዋዜማ- በኦሮሚያ ክልል አዲስ በተዋቀረው ምስራቅ ቦረና ዞን ጎሮ ዶላ ወረዳ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን ትምህርት ቤቶች ሙሉ ለሙሉ ትምህርት አለመስጠታቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

    ከዞኑ እንደ አዲስ መዋቅር ጋር ተያይዞ በተማሪዎቹ በተደረገ አድማ ምክንያት፣ በወረዳው ስር ካሉ ሰማኒያ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ ለቀጣዩ 2017ዓ.ም. የትምህርት ዘመን አንድም ትምህርት ቤት የተማሪ ምዝገባ አለማድረጉንም ዋዜማ ሰምታለች። 

በዚህም ምክንያት 60 ሺሕ ገደማ የሚሆኑ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታቸው ውጪ ሆነው ከርመዋል። 

ከእነዚሁ ተማሪዎች መካከል የተወሰኑት መልቀቂያ ወስደው አጎራባች ወደ ሆኑት ዋደራ፣ አዶላ፣ ሻኪሶ፣ ቦሬ ወረዳዎች እንዲሁም ወደ ነጌሌ ቦረና ከተማ ሄደው ትምህርታቸውን መከታተላቸውን ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች ገልጸዋል።

 በምዝገባ ወቅት ተማሪዎቹ እንዲመዘገቡ እና ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ በመንግሥት፣ በአገር ሽማግሌዎች እና በሃይማኖት አባቶች ጭምር ከፍተኛ ጫና ሲደረግ እንደነበር ያስታወሱ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ግን ጥያቄው መልስ እስካላገኘ ድረስ አንማርም በሚለው በአቋማቸው ፀንተዋል ተብሏል።

 በዚሁ ምክንያት ተማሪዎቹ በ 2016 ዓ.ም. የተሰጡት አገር አቀፍ እና ክልላዊ ፈተናዎች እንዳለፋቸውም አስረድተዋል። በመንግሥት በኩል ከተማሪ ቤተሰቦች፣ ከመምህራን እንዲሁም በየደረጃው ካለው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ተከታታይ ውይይት ሲደረግ የነበረ ቢሆንም ምንም ለውጥ አለመምጣቱን ያብራራሉ። 

ተማሪዎቹ ጎሮ ዶላ ወረዳ ቀድሞ ወደነበረችበት ምስራቅ ጉጂ ዞን ስር እስካልተካለለች ድረስ፣ ለቀጣዩ  የትምህርት ዘመንም ምዝገባ አናደርግም የሚል አቋም መያዛቸውን አክለዋል።

  የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት (ጨፌ ኦሮሚያ) መጋቢት 20 ቀን 2015 ዓ.ም. ሃያ አንደኛ የክልሉ ዞን በማድረግ አዲስ ያዋቀረውን የምስራቅ ቦረና ዞን አደረጃጀት ይፋ ካደረገበት ቀን ጀምሮ፣ በዞኑ ስር ካሉ 18 ወረዳዎች አንዷ የሆነችው ጎሮ ዶላ ወረዳ፣ “በምስራቅ ቦረና ዞን ስር መካለል አንፈልግም” ያሉ የወረዳዋ ተማሪዎች ያለማቋረጥ የተቃውሞ ስልፍ ሲያደርጉ መሰንበታቸው ይታወሳል። ሰልፉ ውጤት አላመጣም ብለው ያመኑት ተማሪዎች፣ ትምህርት ወደማቆም አድማ መግባታቸውን ምንጮች ተናግረዋል።

   የጎሮ ዶላ ወረዳ እንደ ወረዳ ከተዋቀረችበት 1994 ዓ.ም. ጀምሮ በምሥራቅ ጉጂ ዞን ስር ስትተዳደር እንደነበርና ነጌሌ ቦረና ደግሞ የዞኑ ዋና ከተማ ነበረች ፡፡ እንዲሁም አደረጃጀቱ ወረዳዋ ከጉጂ ዞን እንዲሁም ከዋና ከተማዋ ከነጌሌ ቦረና ስታገኝ የነበረውን ተቋማዊ አገልግሎት ሙሉ ለሙሉ የሚያቋርጥ ነው በሚል ቅሬታ፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ተቃውሞውን ሲያሰማ ነበር፡፡ 

ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ በወረዳው አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ አንድ ግለሰብ ለዋዜማ እንደገለጹት፣ በዚሁ ተደጋጋሚ ተቃውሞ ምክንያት የመንግሥት መስሪያ ቤቶች በየመሃሉ ሥራ ሲያቆሙ እንደነበርና የንግድ እና የትራንስፖርት እንቅስቃሴም ሲቆራረጥ መቆየቱን ተናግረዋል። ምንም እንኳን ወረዳዋ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ስትተዳደር ብትቆይም፣ በየጊዜው “ማን እንደጠራው የማይታወቅ” ሰልፍ ይደረግ እንደነበር፣ ለዚህም ሲባል የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ሰልፉን ለመበተን በሚወስዱት እርምጃ በሰዎች ላይ ሞት እና የአካል ጉዳት ሲደርስ መቆየቱንም አስታውሰዋል። 

ጎሮ ዶላ ወረዳ ቀድሞ ከተካለለችበት ምሥራቅ ጉጂ ዞን 190 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ስትገኝ፣ ከአዲሱ አደረጃጀት ምሥራቅ ቦረና ዞን ደግሞ በ 20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች።

በተጨማሪም በዞኑ አጎራባች በሆኑት ሊበን እና ጉሚ ኤልደሎ ወረዳዎች በ 2016 ዓ.ም የመማር ማስተማር ሂደት በበርካታ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተስተጓጉሎ እንደነበር ዋዜማ ከአካባቢው ነዋሪዎች ሰምታለች።

በሁለቱ ወረዳዎች በመንግሥት ወታደሮችና ራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እያለ በሚጠራው ታጣቂ ቡድን መካከል በሚደረጉ ተከታታይ ውጊያዎች ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲቆራረጥ እንደነበር ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

ውስን ተማሪዎችም ትምህርታቸውን ላለማቋረጥ መልቀቂያ ወስደው ወደ ነጌሌ ቦረና ከተማ ሄደው ትምህርታቸውን ለመቀጠል መገደዳቸውን ዋዜማ ተረድታለች።

ዋዜማ በጉዳዩ ላይ የምስራቅ ቦረና ዞን ዋና አሥተዳዳሪ የሆኑትን ጃርሶ ሁሴንን ለማነጋገር በእጅ ስልካቸው በተጋጋሚ የደወለች ሲሆን ስልካቸው ባለመነሳቱ ለጊዜው ሃሳባቸውን ማካተት አልተቻለም። [ዋዜማ]