- በቻይና ከተሰራውና በዓለም የጤና ድርጅት ተቀባይነት ካለው መሳሪያ ጋር ተመሳሳይ ቢሆንም ወደ ገበያ እንዳይወጣ ተደርጎ ቆይቷል።
ዋዜማ – በአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲትዩትና በአሜሪካው ኦሪገን ሄልዝ ኤንድ ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ ትብብር የተሠራው Enzyme-Linked Immunosorbent Assay (ELISA) የተሰኘ የኮቪድ 19 መመርመሪያ መሳሪያ (ኪት) በዋጋ ቅናሽ ውጤቱን ለመለካትም ቀላል እንደሆነ፣ ዋዜማ እጅ የገባው፣ ኢንስቲይዩቱ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የፖሊሲ ምክረ ሀሳብ ሰነድ ይጠቁማል።
በፖሊሲ ምክረ ሀሳብ ሰነዱ፤ በጤና ሚኒስቴር በኩል ይህን የመርመርያ መሳሪያ ሀገር ውስጥ ለሚደረጉ የኮቪድ 19 ምርመራዎች ከመጠቀም ባሻገር፤ ለሌሎች አፍሪካ ሀገራትም በመሸጥ የውጪ ምንዛሬ ማግኘት እንደሚቻል ያብራራል።
ዋዜማ በጉዳዩ ላይ ማብራርያ የጠየቀቻቸው፣ የአርማወር ሐንሰን የምርምር ኢንስቲቱዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ዓለምሰገድ አብዲሳ፣ የኮቪድ 19 መመርመርያ ግኝቱ፣ በቅርብ ጊዜ የተጀመረው “ኢትዮጵያ ታልማ “ የሚል ንቅናቄ አካል እንደሆነ ያስረዳሉ።
የኮቪድ 19 መመርመሪያ መሳሪያው ለምን እንደተሠራ ሲያብራሩም፤ “ሁሉንም ነገር ገዝተን አንችለውምና የመመርመሪያው መሣርያው ዓላማም ኢዚሁ አምርተን ጥቅም ላይ ማዋል ነው” ይላሉ።
የመመርመርያ መሳርያው በዋጋ ርካሽ፣ ቴክኖሎጂውም ቀላል እንደሆነ የሚገልፁት ደግሞ በኢንስትቲዩቱ ከፍተኛ ተመራማሪና የኮቪድ 19 መመርመርያ መሳሪያውን የሠሩት የሳይንትስቶች ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ ገለኖ ናቸው።
“ከውጭ እንግዛ ከተባለ፤ ገበያ ላይ ያለው ‘ዋንታ’ የሚባል ቻይኖች የሠሩትና የዓለም ጤና ድርጅት ያፀደቀው ተመሳሳይ ምርት አለ፣ 80 ሰው ለመመርመር የሚያገለግለው መሳርያ (ኪት) 700 የአሜሪካ ዶላር አካባቢ ይፈጃል። እኛ የሠራነው በሰው 2 የአሜሪካ ዶላር [ለ80 ሰው 160 የአሜሪካ ዶላር ማለት ነው] ይፈጃል” ብለዋል።
የመርመርያ መሳርያው ተገቢውን እውቅና አግኝቶ ሥራ ላይ እንዲውል፣ አስረጂ ሰነዶች ለኢትዮጵያ ምግብና መድሐኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን መግባቱንና ፈቃድ መገኘቱን የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለምሰገድ ይገልፃሉ።
በሌላ በኩል፤ የሳይንቲስቶቹ ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ፣ “የተሰጠው አውቶራዜሽን (ፈቃድ) ገደብ ተጥሎበታል። ይህም እንዳንሸጠው ያግደናል” ይላሉ።
የመመርመሪያ ማሽኑ፤ “በእኛ ጥቅም ላይ ውሏል። ሌሎች የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ወስደው እየተጠቀሙበት ነው” የሚሉት፣ የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር አለምሰገድ፣ አክለውም፣ ለገበያ እንዳይውል ያገደው የኢንስቲትዩቱ የቀድሞ መዋቅር እንደሆነ ይጠቅሳሉ። የአሁኑ መዋቅር ያንን እንደሚፈቅድላቸውም ያብራራሉ።
የምርምር ሳይንቲስቶቹ ቡድን መሪ የሆኑት ዶ/ር ተስፋዬ በበኩላቸው፤ “ኮሜርሻል ፓርትነር (የንግድ አጋር) እያፈላለግን ነው” ይላሉ።
ኢንስትቲዩቱ የተለያዩ የጤና ምርምሮችን ሲያደርግ እንደቆየ የሚገልፁት፤ በኢንስቲትዩቱ የእውቀትና አስተዳደር ተጠባባቂ ዳይሬክተርና ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር አክሊሉ ዓለሙ በበኩላቸው፤ “እስካሁን ምርምሮቻችን እስከ ሕትመት ብቻ ነበር የሚሄዱት። አሁን ግን፤ ፖሊሲዎችንና ድርጊቶችን መቀየር አለባቸው የሚል አቅጣጫ አስቀምጠን እየተንቀሳቀስን ነው” ይላሉ።
ዶ/ር አክሊሉ የኢንስቲትዩቱ ምርምሮች በጤና ፖሊሲ ላይ ያመጣውን ተፅዕኖ ሲያስረዱ፤ “ምንም እንኳን የአቅም ውስንነት ቢኖርብንም፣ የእኛ ምርምሮች የሚያመጧቸው ውጤቶች አሉ።” ብለው እንደ ምሳሌም ስጋ ደዌና ቲቢ(ሳንባ ነቀርሳ) ላይ የሠራናችው ምርምሮች ለጤና ሚኒስቴር ግብዓት እንደሆኑ ይገልፃሉ።
የምርምር ተቋሙ ከ 52 ዓመታት በፊት በኖርዌይና ሲውዲን መንግስታት ድጋፍ የተቋቋመ ነው። [ዋዜማ ]