FILE

ዋዜማ- የመልቲሞዳል (ድብልቅ) ትራንስፖርት አገልግሎት ለመስጠት ፈቃድ ወስደው እስካሁን ሥራ ባልጀመሩ የግል ተቋማት ላይ “አስተዳዳራዊ እርምጃ እንደሚወስድ” የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን አስታወቀ።

የመልቲሞዳል ትራንስፖርት ፤ በአንድ የስምምነት ሰነድ አንድን ዕቃ በመርከብ፣ በአየር በየብስና ባቡርን በመሳሰሉ አማራጮች ከመነሻ እስከ መድረሻ ማጓጓዝ የሚያስችል አገልግሎት ነው። ይህን አሰራር  ለተገልጋዮች በብቸኝነት ሲያቀርብ የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ነበር።

ባለሥልጣኑ፤ ለበርካታ ዓመታት በመንግስት ብቻ ተይዞ የነበረውን  የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ የግል ተቋማት መሳተፍ የሚያችላቸውን ፈቃድ የሰጠው በባለው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ነበር። በወቅቱ በዘርፉ ለመሰማራት ተወዳደረው ከነበሩ 8 ድርጅቶች ውስጥ ለ ሶስቱ ፈቃድ ተሰጥቷል።

ዘርፉ ለግል ድርጅቶች ክፍት ከተደረገ በኋላ ፈቃድ ውድድሩን አሸንፈው ፈቃድ የተሰጣቸው ድርጅቶች ፓንአፍሪክ ግሎባል ሎጂስቲክስ፣ ጥቁር አባይ ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ድርጅት እና ኮስሞስ መልቲ ሞዳል ሼር ካምፓኒ ናቸው።

ድርጅቶቹ ፈቃዱን ለማግኘት ያለፉበት መመዘኛ፤ የተሟላ መሰረተልማት፣ካፒታል፣የሰው ሀብት፣ ዘርፉ ላይ ያላቸው ልምድ እንደሆነ የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂኒየር አብዱልበር ሸምሱ ተናግረዋል።

በወቅቱ ፈቃዱን የወሰዱ የግል ድርጅቶች በ 6 ወራት ውስጥ  ስራ እንዲጀምሩ ቀነ ገደብ ተሰጥቷቸው እንደነበር ያስታወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በዚህ መሰረት የተወሰኑት ስራ መጀመራቸውን ለዋዜማ ተናግረዋል። 

“ ሒደቱን ስንመለከተው እንቅስቃሴ የጀመሩ[ድርጅቶች]አሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት መጀመር  ትልቅ ስራ ነው። 6 ወር ነው የሰጠናቸው። በስድስት ወር ውስጥ አክቲቭ ሆነው ስራ ይጀምራሉ የሚለው የተወሰነ ግምገማ ለመስራት ሞክረናል። የተወሰኑት ተቋማት እንቅስቃሴ አላቸው የመጀመሪያ እቃ የሟጓጓዝ ስራ የጀመሩ አሉ። ሌሎቹ ደግሞ ገና  formation ላይ ነው ያሉት” በማለት የድርጅቶቹን የዝግጅት ሁኔታ አስረድተዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም እስካሁን ስራ ያልጀመሩት ድርጅቶች በራሳቸው ችግር ነው ወይስ በመንግስት የሚለው ከተገመገመ በኋላ “አስተዳደራዊ እርምጃ” እንደሚወሰድ ገልጸዋል። ወደ ሥራ የገቡት ደግሞ ስራቸውን እንዲቀጥሉ ከመንግሥት ድጋፍ እንደሚደረግላቸው ተናግረዋል።

“ከሌሎች ሀገራት ጋር ማለቅ ያለበት የኛ የመንግስት የቤት ስራ አለ።  በተመሳሳይ ደግሞ የነሱም [የድርጅቶቹም] ማለቅ ይኖርበታል። የመጀመሪያ ሺፕመንት ሙከራ እያደረጉ ያሉ አሉ። ማን ምን ያክል አጓጓዘ፣ ከየትኛው የጉዞ መስመር ምን አመጡ የሚለውን ስለምንገመግም፤ በራሳቸው ችግር የማይሰሩ እና ፈቃዱን ወስደው ወደ ስራ ያልገቡ ካሉ ደግሞ አስተዳደራዊ እርምጃ እንወስዳለን” በማለት አብራርተዋል። 

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን፤ ስራ ባልጀመሩ የመልቲሞዳል ትራንስፖርት አገልግሎት አቅራቢ የግል ድርጅቶች ላይ ከሚወስደው እርምጃ ጎን ለጎን  ለሌሎች ተቋማት ፈቃድ እንደሚሰጥ ገልጿል። በዚህ መሰረት በቅርቡ ለሁለት የሀገር ውስጥ ተቋማት “የመልቲሞዳል ፈቃድ” እንደሚሰጣቸው  ዋና ዳይሬክተሩ  ለዋዜማ ተናግረዋል። [ዋዜማ]