• በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ለማቋቋም ዓለም አቀፍ ተቋማት የተካተቱበት ኮሚቴ ተቋቋመ

ዋዜማ- የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን፣ በኢትዮጵያ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ተፈናቃዮችን ቁጥር አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ)፣ ከሰሞኑ ያወጣውን ሪፖርት መቃወሙን ዋዜማ ተረድታለች። በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚኖሩ ተፈናቃይ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን መሆኑን ለዋዜማ የገለፀው ኮሚሽኑ፣ የኦቻው ሪፖርት የቆየ ነው ሲል በሕዝብ ግንኙነቱ በኩል አጣጥሎታል።  

   የኮሚሽኑ ከፍተኛ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አታለለ አቡሃይ፣ ‘የኦቻ ሪፖርት የቆየ እና ትክክለኛ ጥናት ላይ ያልተመሰረተ ነው’ ከማለታቸው ባለፈ፤ ‘ትክክለኛ የተፈናቃዮች ቁጥር ከ3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የማይበልጥ’ መሆኑን ለዋዜማ ነግረዋታል። ኮሚሽኑ፣ በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) እስከ ፈረንጆች ሰኔ 30 ቀን 2024 ድረስ፣ በግጭት እና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ  በመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች ቁጥር 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን መሆኑ አስታውቆ ነበር። ቢሮው፣ ለረጅም ጊዜ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙት በኦሮሚያ፣ ሶማሌ እና ትግራይ ክልሎች እንደሆነ ገልጾ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ተፈናቃዮች ከአንድ ዓመት በላይ፤ ከ23 በመቶ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከኹለት እስከ አራት ዓመት፤ እንዲሁም 11 በመቶዎቹ ለአምስት ዓመት ያህል ከቀያቸው የተፈናቀሉ መሆናቸውንም ነው በሪፖርቱ አስነብቦ ነበር። 

   ‘በአገሪቱ ያሉትን ተፈናቃዮች ቁጥር ለማወቅ በዓመት ኹለት ጊዜ ጥናት ይደረጋል’ ሲሉ ለዋዜማ የነገሯት አታለለ፣ ‘በመኸር ጊዜ የተደረገው ጥናት የሚያሳየው፣ አጠቃላይ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን መሆናቸውን ነው’ ብለዋል። በበልግ ወራት የሚደረገው ጥናት እየተሰራ መሆኑንም ገልፀው፣ ጥናቱ ሲያልቅም አሁን ያለው የተፈናቃዮች ቁጥር ከወራት በፊት ከነበረው እንደሚቀንስ አመልክተዋል። 

ከደብረ ብርሃን መጠለያ ጣቢያዎች 4 ሺሕ ገደማ ተፈናቃዮች ወደመጡበት መመለሳቸውን በመጥቀስ፣ በተለያዩ ቦታዎች የነበሩ ተፈናቃዮች ወደመጡበት በመመለሳቸው፣ ‘አጠቃላይ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚኖሩ ተፈናቃዮች ቁጥር መቀነሱ አይቀሬ ነው’ ሲሉም፣ የሪፖርታቸውን መከራከሪያ ነግረውናል። ባለሙያው፣ መንግሥት ክልሎች የራሳቸውን ተፈናቃዮች በራሳቸው አቅም ማቋቋም አለባቸው በሚል ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት፣ የአዲስ አበባ እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ሌሎች አራት ክልሎች በውስጣቸው ያሉ ተፈናቃዮችን ለማቋቋም ከፌደራል በጀት ከመቀበል መውጣታቸውንም ነግረውናል።  ሆኖም ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ የሚታይባቸው የአማራ፣ የኦሮሚያ እና የትግራይ ክልሎች፣ ‘ከፌደራል መንግሥቱ ጥላ ስር በአጭር ጊዜ አይወጡም’ ብለዋል። ባለሙያው በክልሎች ምን ያህል ተፈናቃዮች እንዳሉ፣ እንዲሁም በአገሪቱ ያሉ የሰብዓዊ ዕርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር ከመግለፅ ግን ተቆጥበዋል። 

    በተመሳሳይ ርዕሰ-ጉዳይ ለዋዜማ ጥያቄ ምላሽ የሰጠው የአማራ ክልል አደጋ መከላከል እና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን በበኩሉ፣ ለዋዜማ በጽሁፍ በላከው መረጃ፣ በክልሉ በኹሉም ዞኖች በጊዜያዊ መጠለያዎች እና ከማኅበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ 621 ሺ 797 ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል። ኮሚሽኑ፣ በዓመቱ ውስጥ ከተፈናቃዮች መካከል ምን ያህሎቹ ወደ ቦታቸው እንደተመለሱ ግን በቀጣይ እንደሚገለጽ አሳውቋል። 

    በክልሉ በዘጠኝ ዞኖች ውስጥ በሚገኙ 43 ወረዳዎች እና 429 ቀበሌዎች ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በድርቅ መጎዳታቸውን የገለጸው ኮሚሽኑ፣ የፌደራሉ መንግሥት 1 ነጥብ 96 ሚሊዮን የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታ ፈላጊዎች እና 556 ሺ 239 ተፈናቃዮች፣ በድምሩ ከ2 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች የዕለት ምግብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በፌደራል መንግሥቱ መረጋገጡን ገልጿል። የፌደራል መንግሥት ለክልሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው አካላት ያደረገው ድጋፍ 68 በመቶ መሆኑንም ኮሚሽኑ አመልክቷል። ኮሚሽኑ፣ በክልሉ ለረዥም ጊዜ በመጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚያስችል የዕቅድ ሰነድ መዘጋጀቱንም የገለጸ ሲሆን፣ ሰነዱ ጸድቆ ወደ ትግበራ ከመገባቱ በፊት፣ በሚመለከታቸው አካላት ውይይት እየተደረገበት ነው ብሏል። 

ተፈናቃይ እና ተመላሾችን በዘላቂነት ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ከተመድ የልማት ፕሮግራም (ዩኤንዲፒ)፣ ከኦቻ፣ ከክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ እና ከሌሎች አጋር አካላት የተወጣጣ የባለሙያዎች ቡድን መቋቋሙንም ዋዜማ ተረድታለች።    በዚህም የተፈናቃዮችን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ወደ ቀያቸዉ መመለስ የሚፈልጉ እንዲመለሱ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፤ አካባቢያቸዉ ላይ ሰርተው ራሳቸውን ለመቻል የሚፈልጉ እና መሬት ተፈልጎ ማልማት የሚፈልጉትን በመለየት በዘላቂነት ለማቋቋም መታሰቡንም፣ ዋዜማ ኮሚሽኑ ከላከው መረጃ መገንዘብ ችላለች። [ዋዜማ]