ዋዜማ- በአዲስ አበባ ከተማ በመንገድ ዳር የሚገኙ የንግድ ወይም አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ከምሽት 12 እስከ ንጋት 12 ድረስ “የውጭ” እና “የውስጥ መብራት” ካላበሩ እንዲሁም በምሽት ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን የሚያሳይ በመብራት የሚሰራ ምልክት ካላስቀመጡ እስከ 10 ሺህ ብር የሚደርስ ቅጣት ሊያስቀጣቸው የሚችል ደንብ የከተማዋ አስተዳደር ተግባራዊ ማድረግ ጀምሯል።

ደንቡ፣ በመንገድ ዳር የሚገኙ ማናቸውም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የንግድ መደብሮች እንዲሁም መኖሪያ ቤቶች በሕንጻቸው የፊተኛው ገጽ መብራት ወይም የፋሳድ ላይት መብራት የማስገባት ግዴታ ጥሎባቸዋል።

አገልግሎት ሰጪዎች በምሽት የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ የወጣውን ደንብ የከተማዋ ካቢኔ ያጸደቀው ባለፈው የካቲት ወር ነበር። አስተዳደሩ ደንቡን ካወጣባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ ከተማዋ የደረሰችበት ኢኮኖሚያዊና ማኀበራዊ ለውጥ መሆኑ ተገልጿል።

የአብዛኛው ማኀበረሰብ የሥራ ባህል እና ፍላጎት በመለወጡ፣ የንግድ ሥራዎችንና አገልግሎቶችን በምሽት የመከወን ተግባር ወጥነትና ቀጣይነቱን ለማረጋገጥ ደንቡ እንደወጣ አስተዳደሩ ተናግሯል። የከተማዋን ተወዳዳሪነት እውን ለማድረግ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ቀን ከሚሰጡት አገልግሎት በተጨማሪ በምሽትም አገልግሎት የሚሰጡበት ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ደንቡ የወጣበት ሌላኛው ምክንያት ነው።

በምሽት የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ የወጣው ደንብ ተፈጻሚ በሚሆንባቸው ተቋማት ላይ የተለያዩ ግዴታዎችን ተጥለዋል። በዚህ መሰረት በከተማዋ “መንገድ ዳር” የንግድ ሥራ የሚሰራ ማንኛውም የንግድ ተቋም፤ በቀኑ ክፍለ ጊዜ የሚያካሄደው የንግድ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ ዘወትር ማታ ከምሽቱ 12 ሰዓት እስከ ምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል ድረስ የመቆየት ግዴታ አለበት።

የንግድ ተቋሙ በምሽት ክፍለ ጊዜ የመግቢያ በሩን ዘግቶ አገልግሎት የሚሰጥ ከሆነ ደሞ፤ ክፍት መሆኑን የሚያሳይ በመብራት ወይም በኤሌክትሪክ የሚሰራ ምልክት በግልጽ በሚታይ ቦታ ላይ ማስቀመጥ እንደሚኖርበት በደንቡ ላይ ተደንግጓል።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ተቋማቱ ያስገቡትን የውጭም ሆነ የውስጥ መብራት፣ ከምሽቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋቱ 12 ሰዓት ድረስ ማብራት አለባቸው ተብሏል። በመንገድ ዳር የሚገኙ መኖሪያ ቤቶች ግን በተመሳሳይ የሰዓት ገደብ ውስጥ እንዲያበሩ የሚገደዱት የውጭ መብራት ብቻ እንደሆነ በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

በአዲስ አበባ የሚገኙ የንግድ ቤቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት እስከ ንጋት ድረስ “የሚያበሯቸው ስታንዳርዳቸውን የጠበቁ መብራቶች ሠላምና ፀጥታ ለማረጋገጥ አጋዥ መሆናቸው ተገልጿል። መብራቶቹ “የአካባቢውን ውበት ይበልጥ የሚያደምቁ እና ኀብረተሰቡ ለመዝናናትና እረፍት ለማድረግ የሚያዘወትራቸው ተመራጭ ቦታዎች እንዲሆኑ ለማድረግ እስከ ንጋት ድረስ መጥፋት እንደሌለባቸው ደንቡ ያስገነዝባል።

በደንቡ ላይ የተጠቀሱት መንገድ ዳር የሚገኙ የአገልግሎት ሰጪ ወይም የንግድ ተቋማት የተጣለባቸውን ግዴታ ካልተገበሩ አሊያም የተደነገጉትን ክልከላዎች ከተላለፉ፣ “ከማስጠንቀቂያ” ጀምሮ የንግድ ሥራ ፍቃዳቸውን እስከማገድ የሚደርስ ርምጃዎችን የከተማዋ የንግድ ቢሮ እንደሚወሰድ ዋዜማ መረዳት ችላለች።

ደንቡ ላይ ከተዘረዘረው የቅጣት ሰንጠረዥ ውስጥ ከፍተኛው ቅጣት 10 ሺህ ብር ሲሆን፣ ዝቅተኛው ደሞ 5 ሺህ ብር ነው።

ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን ሊያስቀጣ የሚችለው ጥፋት ከምሽቱ 3 ሰዓት ተኩል በፊት የንግድ ተቋሙን መዝጋት እንደሆነ በደንቡ ላይ ሰፍሯል።

የሕንጻዎቹ የፊተኛው ገጽ “መብራት ወይም የፋሳድ ላይት ያለመስቀል አሊያም ያለማብራት፣ ቅጣቱ 5 ሺህ ነው።

በተጨማሪ ተቋማቱ እስከ ከምሽት 12 ሰዓት እስከ ንጋት 12 ሰዓት ድረስ የውጭ እና የውስጥ መብራት ካላበሩ የሚከፍሉት የቅጣት ገንዘብ 7 ሺህ ብር ነው።

በምሽት የንግድ እና የትራንስፖርት አገልግሎቶች እንዲሰጡ ለማድረግ የወጣው ደንብ፣ ከምሽቱ 4 ሰዓት በፊት የትራንስፖርት አገልግሎት ማቋረጥ ወይም የስምሪትን መስመር ማቆራረጥ 5 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተቀምጦለታል። በገንዘብ ቅጣት ሰንጠረዡ ላይ፤ ከታሪፍ በላይ ተሳፋሪውን ማስከፈልም በተመሳሳይ 5 ሺህ ብር እንደሚያስቀጣ ተደንግጓል። [ዋዜማ]