ለተጋላጮች 22 ቢሊየን ብር ከፍያለሁ – መንግስት
ዋዜማ- የአለም የገንዘብ ድርጅት በኢትዮጵያ ለኢኮኖሚ ጫና ለተጋለጡ ዜጎች የሚደረገው ድጎማ በቂ አይደለም ሲል በቅርብ ሪፖርቱ ላይ ተችቷል። የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ደግሞ መንግስት የድጎማ ስርዓቱን ከተረጂነት ስነ ልቦና ለማላቀቅ በመሞከሩ እንጂ ድጋፉ ለዜጎች እየቀረበ ነው ሲሉ ለዋዜማ በሰጡት ምላሽ ተናግረዋል።
የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም(አይኤምኤፍ) ለኢትዮጵያ በፈቀደው የተራዘመ የብድር አገልግሎት ዙርያ ሲያደርገው የነበረውን ሁለተኛ ዙር ግምገማ ማጠናቀቁ የሚታወስ ነው። ይህም ለኢትዮጵያ በገንዘብ ተቋሙ ተፈቅዶ ከነበረው አጠቃላይ 3.4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር ውስጥ 248 ሚሊየን የአሜሪካ ዶላር ብድር እንዲለቀቅላት አስችሏል።
የኢትዮጵያ መንግስት “የተሟላ” ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ መተግበር ጀምሬያለሁ ካለ ከባለፈው አመት ሀምሌ ወር መጨረሻ በኋላ ያገኘውን ብድር 1.6 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር አድርሶታል።አይ ኤም ኤፍ ባጠናቀቀው የሁለተኛ ዙር ግምገማ ሪፖርቱ ላይ ኢትዮጵያ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ካደረገ በኋላ ያሉ የአፈጻጸም ሁኔታዎችን አካቷል።
ሆኖም የገንዘብ ተቋሙ በሪፖርቱ መንግስት እየተገበረ ባለው መርሀ ግብር ላይ ቀጥታ የገንዘብ ድጋፍ ለሚደረግላቸው የሴፍቲ ኔት ተጠቃሚዎች የሚደረገው ክፍያ ከታሰበው በታች መሆኑን አንስቷል። የገንዘብ ተቋሙ በዚህኛው ዙር ሪፖርቱ ብቻ ሳይሆን ቀደም ባለ ሪፖርቱም ላይ የኢትዮጵያ መንግስት እየተገበረ ባለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ተጋላጭ ለሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎች የሚደረገው ድጋፍ የተጠበቀውን ያክል አይደለም ብሎ ነበር።
ኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ውስጥ ስትገባ በተለይ የምንዛሬ ተመኑ የሚያመጣውን ተጽእኖ ይበልጥ ለኢኮኖሚያዊ ጉዳት ተጋላጭ ለሚሆኑ ዜጎች የሴፍቲ ኔት መርሀ ግብር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ በጽሁፍ የወጣው የሀምሌ 21 ቀን 2016 አ.ም መግለጫ ያትታል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በቀደመውም ሆነ በአሁኑ ጊዜ በአንጻሩ የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸውን ዜጎች በገጠር በተፋሰስ ልማትና በአፈር ጥበቃ ፣ በከተሞች ደግሞ በጽዳትና በማስዋብ ስራዎች ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ክፍያ ይፈጸምላቸዋል። በገጠርም ሆነ በከተማ በነዚህ ስራዎች ላይ መሰማራት ለማይችሉ ደግሞ ቀጥተኛ የሆነ የገንዘብ ድጋፍ ይደረጋል።
በዚህ መርሀ ግብር ውስጥ በሚሊየን የሚቆጠሩ ዜጎች ተካተው አሉ። ሆኖም በእንዲህ አይነት የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎች ሀገሪቱ የብር የውጭ ምንዛሬ ተመንን በገበያ እንዲወሰን ስታደርግ እና ተያያዥ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን ስትፈጽም ለተጨማሪ የኢኮኖሚ ችግር ይበልጥ ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ስለታመነ ኢትዮጵያ ለማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ትግበራው ለድጎማ ከምታውለው ገንዘብ ውስጥ 60 ቢሊየን ብር ለዚሁ የሴፍቲ ኔት እንዲውል በሚል የተመደበው።
ከዚሁ መርሀ ግብር ጋር በተያያዘ ለተጋላጭ ዜጎች የሚደረግ የገንዘብ ክፍያ ጋር የሚነሳው ትችት ላይ መልስ እንዲሰጡ ዋዜማ የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋን(ዶ/ር) ጠይቃለች። “የኢትዮጵያ መንግስት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ጋር በተያያዘ ለዚህ አመት 400 ቢሊየን ብር የሚጠጋ ብርን ለተለያዩ ዘርፎች ድጎማ መድቧል ፣ ለነዳጅ 100 ቢሊየን(ከዚህ ውስጠ 72 ቢሊየን ብሩ ጥቅም ላይ ውሏል) ፣ ለማዳበርያ 87 ቢሊየን ፣ ለመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪ 91 ቢሊየን ፣ ለዘይትና መድሀኒት ምርቶችም ድጎማው የተመደበ ሲሆን ፣ በሴፍቲኔት ለሚታቀፉ ዜጎች ደግሞ 60 ቢሊየን ብር ተመድቧል” ብለውናል ሚኒስትሯ።
“አሁን ተግባራዊ እየተደረገ ባለው መርሀ ግብር ላይ ቀድሞም ተጠቃሚ የነበሩ ሚሊየኖች የተካተቱ ሲሆን ፣ አሁን ላይ የሴፍቲኔት መርሀ ግብር ውስጥ ለመግባት ከጫፍ የደረሰ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ የደረሱ ዜጎችን አካተናል ” ብለውናል።
ሆኖም በመርሀ ግብሩ የታቀፉ ዜጎች በሚሊየን ይቆጠራሉ ከማለት ውጭ በትክክል ቁጥራቸው ስንት እንደሆነ አልገለጹልንም። ነገር ግን በአይ ኤም ኤፍ እንደተነሳው ሳይሆን ለዚህ አመት ለኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች ከተያዘው 60 ቢሊየን ብር ውስጥ ባለፉት አምስት ወራት 22 ቢሊየን ብሩ ለተጠቃሚዎች ተላልፏል ብለዋል የፕላንና ልማት ሚኒስትሯ ፍጹም።
ታድያ መንግስት ይህን ያክል ገንዘብ ካወጣ ለኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ ከሆኑ ዜጎች ጋር በተያያዘ የሚነሳው አስተያየት ከምን የመነጨ ነው? በሚል ለሚኒስትሯ ላነሳነው ጥያቄ ምላሽን ሲሰጡ ” ኢትዮጵያ ቀድሞ ልማታዊ ሴፍቲ ኔትን ስትተገብር ከሀገራትና ከአለም አቀፍ ተቋማት አድናቆትን ታግኝ እንጂ እንደ መንግስት ይህ መርሀ ግብር ጥገኝነትን የማበረታታት አዝማሚያም ስላለው ፣ ግዴታ የሚሆንበት ሁኔታ ስላለ እንጂ ብዙም የምንደግፈው አይደለም” ይላሉ።
“መርሀ ግብሩንም የምንተገብረው በተቻለ መጠን ዜጎች ራሳቸውን ችለው ከተረጂነት በሚወጡበት መልኩ ነው ፣ አሁን የሚነሳው አስተያየትም መንግስት መርሀ ግብሩን ከሚተገብርበት መንገድ ጋር በተያያዘ ካለ የአቅጣጫ ልዩነት እንጂ የኢኮኖሚ ችግር ተጋላጭ ለሆኑ ዜጎች ድጋፍ ስላልተደገ አይደለም ” ብለውናል ሚኒስትሯ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ መንግስት የኢትዮጵያ ብር የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ካደረገ በሁዋላ የኢትዮጵያ አመታዊ ምርት የዋጋ ንረትን ሰሌት ውስጥ ባላስገባ መልኩ ሲሰላ ከ207 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወደ 100 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዝቅ ማለቱ በገንዘብ ሚኒስቴር የአመታዊ የእዳ ሰነድ መጽሄት ላይ ተጠቅሷል።ይህም የሆነው በምንዛሬ ተመን ለውጡ ሳቢያ ነው። የሀገሪቱ የውጭ እዳም ከ28 ቢሊየን ዶላር ወደ 31 ቢሊየን ዶላር እድገትን አሳይቷል። የኢትዮጵያ አመታዊ ምርት ወደ 100 ቢሊየን ዶላ ከመውረዱ ጋር ተዳምሮ የሀገሪቱ የውጭ እዳ ከአመታዊ አጠቃላይ ምርት አንጻር ያለውን ድርሻ ከ30 በመቶ በላይ አድርሶታል። [ዋዜማ]