ዋዜማ- ላለፉት በርካታ አመታት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ከመንግስታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድረው ያልከፈሉት 900 ቢሊየን የሚሆን ብርን የገንዘብ ሚኒስቴር እንዲወርስ መወሰኑን ዋዜማ ከሁነኛ ምንጮቿ ሰምታለች።
ውሳኔውም የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሰኔ 7 ቀን 2016 ዓ/ም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን መዋቅራዊ ሪፎርምን እና የባንኩን ካፒታል ለማሳደግ ካሳለፈው ውሳኔ ጋር መጽደቁንም ሰምተናል።
የገንዘብ ሚኒስቴር እዳውን እንዲወስድ የተወሰነውም የልማት ድርጅቶቹ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገንዘቡን ሲበደሩ በገንዘብ ሚኒስቴር ዋስትና ሰጭነት በመሆኑ ነው ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስቴር እዳቸውን እንዲወርስ ከተወሰናቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ፣ ስኳር ኮርፖሬሽን ፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕን ጨምሮ ቀድሞ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ውስጥ የተካተቱ ተቋማት ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ሀይል ብቻውን ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተበድሮ ያልከፈለው ከ300 ቢሊየን ብር በላይ እዳ እንደነበረበት የሚታወስ ነው። ከዚህ ቀደም እዳ ውስጥ የተዘፈቁ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን እዳ የሚያስተዳደር፣ የመንግስት የእዳ እና ንብረት አስተዳደር ኮርፖሬሽን ተቋቁሞ ወደ ስራ ገብቶ እንደነበር የሚታወስ ነው።
አሁን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባስተላለፈው ውሳኔ መሰረት የገንዘብ ሚኒስቴር በልማት ድርጅቶች ለንግድ ባንክ ያልተከፈለ 900 ቢሊየን ብር ወስዶ በተከፋፈሉ ጊዜያት ወደ ቦንድ ቀይሮ ለገበያ በማቅረብ ፣ ከቦንዱ ሽያጭ የሚገኝ ገንዘብን በየጊዜው ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እንደ እዳ መመለሻ ገንዘብን እየሰጠ ባንኩን የማጠናከር ስራ ይሰራል ተብሏል።
የገንዘብ ሚኒስቴር የወሰደውን እዳ ወደ በረጅም ጊዜ የሚከፈል ቦንድ አድርጎ ለገበያ ያቀርበዋል። ዋዜማ እንደሰማችው ከሆነም ሚኒስቴሩ ለገበያ የሚያቀርበው ቦንድ የ10 አመት የመክፈያ ጊዜ ያለው (ማለትም ቦንዱን የሚገዙት አካላት ገንዘቡ የሚመለስላቸው በአስር አመት) ሲሆን ቦንዱን ለሚገዙ የዘጠኝ በመቶ ወለድ የሚከፈል እንደሆነም ነው መረዳት የቻልነው።
የገንዘብ ሚኒስቴር ብድሮችን ወደ ረጅም ጊዜ ቦንድ የመቀየር ሁኔታ በተለይ ለበጀት መሙያ ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ የተበደረው ገንዘብ ላይ በስፋት ይታያል። በቅርቡም ከብሄራዊ ባንክ በህትመት ተበድሮት የነበረው ብድር ወደ ረጅም ጊዜ ቦንድ እንደተቀረ የሚታወስ ነው። [ዋዜማ]