ዋዜማ ራዲዮ-በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ከፍተኛ የመንግስት ስልጣን ይዘው የሚገኙ ግለሰቦችንና ሌሎች የክልልና የፌደራል መንግስት ሰራተኞችን የትምህርት ማስረጃዎች የማጣራት ስራ ተጀመረ።
ብሄራዊ የመረጃና ደህንነት ኤጀንሲ (INSA) ከትምህርት ሚንስቴር ጋር እያደረገ ባለው ምርመራ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሀሰተኛ ሰነድ በማቅረብ ተለይተዋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ በኢትዮጵያ ክልሎችን ጨምሮ በመንግስት መስሪያ ቤቶች ውስጥ ለበርካታ ዓመታት በተጭበረበረና በሐሰት የትምህርት ማስረጃ ተቀጥረው በሚሰሩ ሰራተኞችና አመራሮች ላይ የተጀመረው የማጽዳት ዘመቻ ወደ ከፍተኛ ባለስልጣናት ከፍ ብሎ መታየቱ አንዳንድ ባለስልጣናትን እያሰቆጣ መሆኑን ዋዜማ ከምንጮች ለማወቅ ችላለች፡፡
ዘመቻው በርካታ ስመ-ጥር ባለስልጣናትን ተጠያቂ ማድረጉ ስለማይቀር ምርመራው እንዲቆም ወይም እስካሁን በተደረገው ማጣራት ላይም ከህግ ይልቅ በፖለቲካዊ ውሳኔዎች ታይቶ እንዲታለፍ አንዳንድ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጫና እያሳደሩም ይገኛሉ፡፡
በፌደራል መንግስት ስር ያሉ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛና በመካከለኛ የአመራር ደረጃዎች ያሉ ኃላፊዎች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተሹመው በመገልገል ላይ ካሉት የበርካታ ግለሰቦች ስም ዝርዝር ለኢህአዴግ ጽ/ቤትና ለጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ተልኳል ተብሏል፡፡
በዚሁ የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ባለቤት ናቸው ተብለው የተለዩት ለዓመታት ከመምሪያ ኃላፊነት እስከ ሚኒስትር ዲኤታነት እስከ ሚኒስትርነት ባሉ ማዕረጎች በኃላፊነት ተሹመው በማገለገል ላይ ያሉ መሆናቸውም ታውቋል፡፡
ከዚሁ አነጋጋሪው የሰነድ ማጭበርበር ጋር በተያያዘ የትምህርት ሚኒስቴር ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመለየት የሚያስችል የአሰራር ስርዓት ለመዘርጋት ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በጋራ እየሰራ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ ገልጸዋል፡፡
ዶ/ር ጥላዬ በፓርላማ ቀርበው ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተጠቅመው ወደ መንግስት ቢሮ የገቡ የስራ ሀላፊዎችንና ሰራተኞችን ለመቆጣጠርና ማስረጃዎቹንም ለመለየት የተጀረመው ስራ አልቆ በዚህ አመት ስራ ይጀምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡
ስራው ከጠናቀቀ በኋላ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው በስራ ላይ የተገኙትን በህግ ተጠያቂ ማድረግ እንደሚጀመርም ተነግሯል፡፡
በኦሮምያ ክልል ፐብሊክ ሰርቪስና ሰው ሀብት ልማት ቢሮ በሁለት ዙር ሲያጣራ ቆይቷል፡፡
በተደረገው የማጣራት ስራም በክልሉ ከ6,400 በላይ ሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ይዘው የተቀጠሩ ሰራተኞች ራሳቸውን አጋልጠው ይቅርታ መጠየቃቸው ይታወሳል፡፡
ሌሎች 8,300 የመንግስት ሰራተኞች ደግሞ የትምህርት ማስረጃቸው ሀሰተኛ እንደሆነ ተጠቁሞባቸው እየተጣራ መሆኑም ተሰምቷል።
በጋምቤላ ክልልም ባለፈው አመት በተደረገ ማጣራት የክልሉ የትምህርት ቢሮ ሀላፊዎችን ጨምሮ በርካታ ባለስልጣናትና ሰራተኞች በሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃ ተሹመውና ተቀጥረው እንደሚሰሩ ተደርሶባቸዋል፡፡
አሁን የትምህርት ሚኒስትር ከመረጃ መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር ጀመርኩት ያለው የሀሰተኛ የትምህርት ማስረጃን ለመቆጣጠር የሚያስችል የአሰራር ሥርዓት ሲጠናቀቅ በሁሉም የትምህርት ማሰልጠኛ ተቋማት ስራ ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡