ዋዜማ ራዲዮ- የኢሚግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከዘንድሮ ጥቅምት ወር ጀምሮ ለተጠቃሚዎች በድረ-ገጽ አማካኝነት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት እና ለማደስ ቀጠሮ ማስያዝ የሚያስችል ድረ-ገጽ ይፋ አድርጎ ሲሰራ ቆይቷል። በተለይ በአሁኑ ወቅት አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ወደ ኤጀንሲው ድረ ገፅ በመግባት ቀጠሮ ለማስያዝ የሚሞክሩ አገልግሎት ፈላጊዎች በትንሹ ከሁለት ወር በፊት የሚስተናገዱበት አሰራር እንደሌለ ነው መታዘብ የሚቻለው።

ኤጀንሲው ፓስፖርት ለማግኘት መደበኛውን የወረፋ ግዜ ሳይጠበቁ እንዲስተናገዱ እና ከተቀመጠው ግዜ አስቀድሞ በአፋጣኝ አገልግሎት ለሚፈልጉ፤ አስቸኳይ ፓስፖርት ለማግኘት የተገደዱበትን ምክንያት እንዲያቀርቡ አሰራር እንዳለው በድህረ ገፁ ላይ ይጠቅሳል።

ለአስቸኳይ ህክምና፤ የትምህርት እድል ለሚያገኙ አመልካቾች እንዲሁም የዶቪ ሎተሪ እድለኞች ማስረጃቸውን እንዲያቀርቡ የሚጠይቅ አሰራር እንዳለው ያስቀምጣል። የውጭ ሀገር የመኖሪያ ፈቃድ፤እንዲሁም ከተፈቀደለት ተቋም የሚፃፍ የድጋፍ ደብዳቤ አስቸኳይ ፓስፖርት ለማውጣት የሚያስችሉ ማስረጃዎች ሆነው በጥቂቱ ተገልፀዋል።

እነዚህን ፓስፖርትን በአስቸኳይ ለማውጣት ተያይዘው የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ማግኘት ያልቻሉ እና በተለያየ ምክንያት ፓስፖርትን በፍጥነት ለማውጣት ለሚገደዱ ሰዎች ግን እስከ 30 ሺህ ብር ጉቦ እየተከፈለ በህገወጥ መንገድ ፓስፖርት እየወጣ መሆኑን ዋዜማ አረጋገጣለች።

በአሜሪካ ሀገር ለሚገኝ የትምህርት እድል ለማመልከት የፓስፖርት ቁጥር ያስፈልገው የነበረ አንድ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ ወጣት በ5 ቀናት ውስጥ ፓስፖርት ሊወጣለት እንደሚችል ነገር ግን 25 ሺህ ብር በመክፈል በደላላ በኩል እንደተገናኘ እና ፓስፖርቱን እንዳገኘ ይናገራል።

‘’ የትምህርት እድሉን የማመልከቻ ግዜ ሊጠናቀቅ ቀናት ብቻ ስለቀራቸው ምንም እንኳን ድርጊቱ ህገወጥ ቢሆንም ይህንን አማራጭ ለመከተል ተገድጃለሁ ይላል’’ ይህ ወጣት።

ሁለት የዋዜማ ሪፖርተሮችም አስቸኳይ የፓስፖርት አማራጭ እንዳለና ሰላሳ ሺህ ብር ከከፈሉ ጉዳዩ በሶስት ቀናት እንደሚያልቅላቸው በደላሎች በኩል ተነግሯቸዋል።

የዋዜማ ሪፖርተር የኢሚግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ አካባቢ በማቅናት የአሻራ ውጤት ለማቅረብ የተገኘን አንድ ባለ ጉዳይንም አነጋግሯል። አዲስ ፓስፖርት ለማውጣት ከሁለት ወር በላይ በቀጠሮ መቆየቱን የሚናገረው ይህ ወጣት አሁን የአሻራ ውጤቱን እንዲያቀርብ ተደውሎ እንደተነገረው ገልጿል።

ይሁን እንጂ መደበኛ ፓስፖርት ለማውጣት ከወራት በላይ በመጠበቅ ሂደቱን እያጠናቀቀ እንደሚገኝ በር ላይ ባገኘው አንድ ግለሰብ አማካኝነት እንዲህ አይነት አማራጭ ስለመኖሩ መስማቱን ይናገራል።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ከዚህ ቀደም ይፋ እንዳደረገው መደበኛውን ፓስፖርት ለማግኘት ከ75 ቀናት ወደ 30 ቀናት ማውረዱን ቢናገርም አሁንም መደበኛውን ፓስፖርት ለማግኘት ወራቶች መቆጠራቸው ለዚህ ህገወጥነት መነሻ መሆኑን አገልግሎት ፈላጊዎች ይናገራሉ።

የኢሚግሬሽን ዜግነትና የወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ እንዲህ አይነቱን ችግር በቀላሉ እንደማይመለከተውና በማስረጃ ከቀረበለት እርምጃ እንደሚወስድ አሳውቆናል። ህብረተሰቡ ማናቸውንም አገልግሎት ከመስሪያ ቤቱ ውጪ ባሉ ደላሎች ለማስፈፀም እንዳይሞክርና ገንዘብም እንዳይከፍል መክሯል።

ይህን ዘገባ እያጠናቀርን ባለበት የአንድ ሳምንት ጊዜ የተወሰኑ ደላሎችና የመስሪያ ቤቱ ሰራተኞች ላይ በይፋ ያልተብራራ እርምጃ መወሰዱን ስምተናል። መስሪያ ቤቱ አስፈላጊ በሆነ ወቅት መግለጫ ይሰጣል ተብለናል። [ዋዜማ ራዲዮ]