Newly appointed Supreme court President Dagne Melaku
Newly appointed Supreme court President Dagne Melaku
  • 109 የከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችም ዛሬ በፓርላማ ፊት ሹመታቸው ጸድቆላቸዋል

ዋዜማ ራዲዮ- ከአራት ወር በፊት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትነታቸውን በገዛ ፍቃዳቸው በለቀቁት አቶ ተገኔ ጌታነህ ምትክ አቶ ዳኜ መላኩ ዛሬ (ሀሞስ) ተሾሙ። የምክትል ፕሬዝዳንትነቱን ቦታ አቶ ፀጋዬ አስማማው ተረክበዋል።

በሀገሪቱ የዳኝነት ስርዓት የመጨረሻ እንደሆነ ለተደነገገለት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው የተመረጡት አቶ ዳኜ ከፍተኛ ትኩረት የሳቡ ፖለቲካ ቀመስ የክስ ሂደቶችን በሰብሳቢ ዳኝነትን ሲይዙ የቆዮ ናቸው። ከእነዚህም ውስጥ ከቆዮት የክስ ሂደቶች መካከል የእስክንድር ነጋ፣ የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) እና የርዕዮት ዓለሙ ይግባኞች ሲጠቀሱ አሁን በመመልከት ላይ ከሚገኙት ውስጥ ደግሞ የእነ ሀብታሙ አያሌው እና የዞን ዘጠኝ ጦማሪያን ጉዳይ ይገኝበታል።

በዳኝነት ስራ ለ28 ዓመታት ያገለገሉት አቶ ዳኜ ከደርግ ጊዜ ጀምሮ በህግ ባለሙያነት ቆይተዋል። ገዢው ፓርቲ ወደ ስልጣን ሲመጣ በቀድሞው ክልል 14 የዞን ፍርድ ቤት የወንጀል ችሎት ዳኛ ሆነው አገልግለዋል። የክልል 14 ችሎት ፈርሶ የከተማ እና ፌደራል ፍርድ ቤቶች ሲቋቋሙ ወደ ድሬዳዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተዛውረዋል።

ከዓመታት ቆይታ በኋላ ወደ አዲስ አበባ ሲመለሱ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆኑ። በ1990ዎቹ መጀመሪያ ደግሞ ለረጅም ጊዜ በዳኝነት ወደ አገለገሉበት ጠቅላይ ፍርድ ቤት መጥተዋል።

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ብቸኛ የነበረውን የወንጀል ችሎት በሰብሳቢነት ለበርካታ ዓመታት ሲመሩ ከቆዮ በኃላ የሚመለከቷቸው ጉዳዮች በዝተዋል በሚል ችሎቱ ለሁለት እንዲከፈል ተደርጓል። ከተወሰኑ ዓመታት በኃላ ግን የወንጀል ጉዳይ ተመልሶ እርሳቸው በሚመሩት አንድ ችሎት ብቻ ተጠቃልሏል።

“የሙስና፣ የሽብር ወይም ሌላ ፖለቲካዊ አንደምታ ያለው ጉዳይ ይግባኝ የሚያየው የእርሱ ችሎት ብቻ ነው” ይላሉ በጥብቅና ሙያ የተሰማሩ ባለሙያ ለዋዜማ ሲናገሩ። “እንደዚህ አይነት ጉዳዮች ካሉህ መዝገብ ቤት ሄደህ ማጣራት ሳያስፈልግህ ወደ እርሱ እንደሚመራ ግልፅ ነው።”

በመንግስት በኩል የተለየ ትኩረት ከሚሰጣቸው ጉዳዮች የይግባኝ ውሳኔዎች “ጀርባ” አቶ ዳኜ እንደነበሩ የህግ ባለሙያው ያስረዳሉ። የብዙዎቹ ውሳኔዎች “ዋነኛ አቀነባባሪ” እንደሆኑም ያክላሉ።

“በባለሙያዎችም ሆነ በተገልጋዮችም ምሬትን ያስከትሉ ውሳኔዎችን ሲስጥ እና ሲያሰጥ የነበረ ነው” ይላሉ በፍትህ ስርዓቱ ውስጥ ለረጅም ጊዜ የቆዩት ጠበቃ።

ሌላ የህግ ባለሙያ በበኩላቸው ከአቶ ዳኜ ውሳኔዎች ጀርባ “እንዳላስቀይም ዓይነት ጥንቃቄ አለ” ይላሉ።

“ፍርዱን አትገምተውም። የራሱ አይነት አካሄድ አለው” ይላሉ የህግ ባለሙያው። “ጭብጡን እና በችሎት የተነሳውን ክርክር ይዞ አይደለም ውሳኔ የሚሰጠው።”

አቶ ዳኜ በጸባያቸው “ተጋፊ”፣ “ከስራ ባልደረቦቻቸው ጋር የማይግባቡ” እንደዚሁም “ሱሰኛ” እንደሆኑ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። በክልል 14 ዳኛ በነበሩ ጊዜ በችሎት ውስጥ አብረዋቸው ከሚያስችሉ ዳኞች ጋር መደባደባቸውን ያስታውሳሉ።

የአቶ ዳኜ የፕሬዝዳንትነት ሹመት ለዋዜማ አስተያየታቸውን በሰጡ ባለሙያዎች ዘንድ ተተችቷል። ሹመቱን ያጸደቀው በገዢው ፓርቲ አባላት እና አጋሮቹ የተሞላው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤትም እንደ ባለፈው ማክሰኞ ውሎው አይሁን እንጂ በፕሬዝዳንቱ ላይ ለየት ያለ ድምፅ አስተናግዷል። ድምፀ ተአቅቧቸውን በስተመጨረሻ ያስመዘገቡ የፓርላማ አባል አቶ ዳኜን “ብቃት የላቸውም” ሲሉ ወርፈዋቸዋል።

በአንድ ወቅት ከአቶ ዳኜ ጋር አብረው የሰሩ የህግ ባለሙያም ዳኛው “ለኃላፊነት ቦታ የማይመጥኑ” እንደሆኑ ይቀበላሉ። የአቶ ዳኜን መሾም “መቼም አስቤው አላውቅም” ሲሉ ሀዘን የተቀላቀለበት ገረሜታቸውን ይገልጻሉ።

“ተቋሙ የሚገመገመው በፕሬዝዳንቱ ሁኔታ ነው” ይላሉ ባለሙያው። “የዳኜ መሾም መንግስት ለተቋሙ የሰጠውን ቦታ ነው የሚያሳየው።”

የህግ ባለሙያዎቹ “ረጅም ጊዜ ማገልገል ብቻውን የፕሬዝዳንትነት መምረጫ መስፈርት ሊሆን አይገባውም” ይላሉ። ተሿሚው ፕሬዝዳንት ከኃላፊነት ይልቅ “ለጡረታ የቀረቡ” ናቸው ሲሉ ይተቻሉ።

ለጡረታ ወራት የቀራቸው እና የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አቶ ተገኔን ተክተው የኃላፊነቱን ስራ ሲያከናውኑ የቆዩት ምክትላቸው አቶ መድህን ኪሮስ ግን በዛሬው የፓርላማ ውሎ ተሰናብተዋል። እርሳቸውን የተኳቸው አቶ ፀጋዬ አስማማው በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ብዙም የቆዩ አይደሉም።

Tsegaye Asmamaw newly appointed Deputy President of the Supreme Court
Tsegaye Asmamaw newly appointed Deputy President of the Supreme Court

በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ከመምጣታቸው በፊት የትግራይ ክልል ፍትህ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል። ህወሃትን ወክለው ፓርላማ በመግባት በፍትህ እና አስተዳደር ቋሚ ኮሚቴ ውስጥ በሰብሳቢነት አገልግለዋል።

ለዳኝነት አካሉ እንግዳ ናቸው የሚባሉት አቶ ፀጋዬ በሙስናም ክፉኛ ይታማሉ። በጠቅላይ ፍርድ ቤት የዳኝነት ቆይታቸው “ፋይል ይዘው መቅረት የሚያዘወትሩ” እና “በአየር ላይ ተደጋጋሚ ቀጠሮ” በመስጠት ጠበቆችን ያማረሩ እንደነበሩ ይነገርላቸዋል።

በኃላፊነት ደረጃ ከተሾሙት ሁለቱ ዳኞች በተጨማሪ በፌደራል ዳኞች አስተዳደር ጠቋሚነት እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት 109 የከፍተኛ እና የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዳኞችም ዛሬ በፓርላማ ፊት ሹመታቸው ጸድቆላቸዋል።