ዋዜማ-በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ስር የሚመራው የብሄራዊ መታወቂያ “ፋይዳ” ያላወጡ ዜጎች በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ እንደ ቅድመ ሁኔታ በመቀመጡ አገልግሎቶችን ለማግኘት እየተጉላሉ መሆኑን አዲስ አበባን ጨምሮ የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች ለዋዜማ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
ቅሬታቸውን ለዋዜማ ካቀረቡት መካከል ” ማንኛውም ፍትህ የሚፈልጉ ክሶችን በፍርድ ቤት ለማቅረብ ከሳሹ “ፋይዳ” የዲጂታል መታወቂያ ማቅረብ ግዴታ ነው በማለት ከነሀሴ ወር ጀምሮ እየተንገላቱ እንደሚገኙ እንዲሁም ጉዳዩ በጠበቃ ቢቀርብም ጠበቃው የከሳሾችን የቀበሌ ዲጂታል መታወቂያ ይዞ መቅረብ አለበት” እየተባሉ እንደሆነ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ መልኩ በአዳማ ከተማ የሚገኙ ነዋሪዎች በቀበሌ እና ማዘገጃ ቤቶች የሚሰጡ አገልግሎቶች ፣ ካርታ ለማውጣት እንዲሁም የመሬት ስም ዝውውር ለማድረግ የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ ይዞ መቅረብ እንደ ቅድመ ሁኔታ መቀመጡን የአካባቢው ነዋሪዎች ነግረውናል።
ከብሔራዊ ባንክ ባገኘነው መረጃ ደግሞ
- ከጥር 2017 አጋማሽ ጀምሮ በአዲስ አበባ አዲስ የባንክ አገልግሎት ለማግኘት ግዴታ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ያስፈልጋል
- ከሰኔ ወር 2017 መጨረሻ ጀምሮ ደግሞ በሀገሪቱ ባሉ ሁሉም ትልልቅ ከተሞች ባሉ ባንኮች አካውንት ለመክፈት ፋይዳ ግዴታ ነው
- በመላው ሀገሪቱ ያሉ ሁሉም ባንኮች ከጥር 2018 ዓ.ም ጀምሮ ፋይዳ መታወቂያን ግዴታ ያደርጋሉ
- ታሕሳስ 2019 ዓ.ም ነባር የባንክ ደንበኞችም ቢሆኑ ፋይዳ ካልያዙ አገልግሎት አያገኙም
ዋዜማ ባሰባሰበችው መረጃ መሰረት ፍርድቤቶች፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እንዲሁም የመሬት እና መሬት ነክ ጉዳዮችን ለማስፈጸም ብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ አስገዳጅ መሆኑን ተረድተናል።
አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዪ ያሉ አካባቢዎች የብሄራዊ ዲጂታል መታወቂያ አስገዳጅ የሆነበትን ምክንያት ለብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ሀላፊዎች ዋዜማ ላቀረበችው ጥያቄ በፕሮግራሙ አዋጅ መሰረት ማንኛውም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብሄራዊ መታወቂያን በአስገዳጅ ሁኔታ ወይም በቅድመ ሁኔታ እንዲኖራቸው የማስገደድ ስልጣን ባይኖረውም ከፕሮግራሙ ጋር የመግባቢያ ስምምነት የፈረሙ ተቋማት ግን እንደ ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ መብት እንዳላቸው ተደንግጓል ሲሉ ነገረውናል።
የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም ከተለያዪ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በጋራ ለመስራት የመግባቢያ ስምምነት የሚፈርመው ቴክኒካል ስራዎችን በጋራ ለመስራት እንዲያመች በሚል እንጂ አስገዳጅ አድርገው እንዲተግበሩት አይደለም ሲሉ ሀላፊዎቹ ለዋዜማ ተናግረዋል።
ነገር ግን ተቋማቱ አግልግሎታቸውን ለመስጠት በአዋጅ የተሰጣቸውን ቅድመ ሁኔታ የማስቀመጥ መብት ያላቸው በመሆኑ ፕሮግራሙ ጣልቃ አይገባም ሲሉ አክለዋል።
የሀላፊዎቹን ሀሳብ በሙሉ የምትስማማው የፕሮግራሙ የሚዲያ እና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ቃልኪዳን አብረሀም ደግሞ ተቋማቱ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጣቸው ለተጠቃሚዎች ደህንነት ከመሆኑም በላይ ዲጂታል መታወቂያ የሚገኝበት መንገድ እንደ ቀበሌ መታወቂያ የነዋሪነት ምስክር የማይጠይቅ በቀላሉ የሚሚገኝ ማረጋገጫ ስለሆነ ነዋሪዎች የሚጉላሉበት አይደለም ብለዋል።
ነዋሪዎች በቀላሉ ያገኙታል ለሚለው ምላሻቸውም የቀበሌ መታወቂያን ያስቀራል ማለት ነው ወይ? በሚል ዋዜማ ለጠየቀችው ጥያቄ እስከ አሁን ባለው ሁኔታ የቀበሌ መታወቂያ ይተካል የሚል ውሳኔ ላይ አልተደረሰም በማለት ቃልኪዳን ምላሸ ሰጥተዋል።
“ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያን ከሌሎቹ መታወቂያዎች የሚለየው አመልካቹ ኢትዮጵያዊ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ማለትም ፓስፖርት፣የቀበሌ መታወቂያ ፣የማንኛውም መስሪያቤት መታወቂያ ና ሌሎች ሰነዶች ያለው ሰው የሚሰጠው ሲሆን የባዮ ሜትሪክ መረጃ ማለትም የአይን አሻራ፣ የአስር ጣት የእጅ አሻራ፣ እና የግለሰቡ ፎቶ የሚካተትበት መሆኑን ዋዜማ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ በሚሰጥባቸው ቦታዎች መመልከት ችላለች።
አገልግሎቱ ለማግኘት አመልካቾች የብሄር ማንነታቸውን እንዲገልፁ እንደማይጠየቁ ተገንዝበናል።
ምንም አይነት ሰነዶች የሌለው ሰው “ፋይዳ” ዲጂታል መታወቂያ ያለው ሰው በምስክርነት በማቅረብ አገልግሎቱን ማግኘት ይችላል።
ኢትዮ ቴሌኮም የዲጂታል ሶሉሽን አቅራቢ ድርጅት በመሆኑ የፋይዳ ዲጂታል መታወቂያ ምዝገባ፣ በመታወቂያ ህትመትና ስርጭት፡ ማንነትን በማረጋገጥ (Authentication) ስራዎች የሚሳተፍ ሲሆን ባንኮች፣ የግል እና የመንግስት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ደግሞ ቴክኒካል ስራውን ተግባራዊ የሚያደርጉ ናቸው ተብሏል።
በ2018 ዓ. ም ማብቂያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የብሔራዊ መታወቂያ “ፋይዳ” እንዲኖራቸው እቅድ የያዘው የብሄራዊ መታወቂያ ፕሮግራም እስከ አሁን ከ4 ሚሊዮን ዜጎች በላይ መመዝገብ ችሏል።
በፈረንጆቹ አቆጣጠር 2018 የዓለም ባንክ ባወጣው ጥናት መሰረት በዓለም ዙርያ አንድ ቢሊዮን ሰዎች ማንነታቸውን ለማረጋገጥ የሚረዳ ማስረጃ የሌላቸው ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደግሞ 81 በመቶ ያህሉ የሚገኙት ከሰሃራ በታች ባለው የአፍሪካ ክፍል መሆኑን ጥናቱ ያሳያል። [ዋዜማ]