Screen shot of the leaked Exam paper (SM)
Screen shot of the leaked Exam paper (SM)
  • የፈተና ወረቀቱ የተሰረቀበትን ቦታና ተሳታፊ ግለሰቦችን ለመለየት ሁለት አስቸኳይ ስብሰባዎች ተደረገዋል

(ዋዜማ)-ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ በመላው ኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ የሚደግፉ አስተባባሪዎች እና አራማጆች ጉዳዩን ወደ ሌላ ምዕራፍ የሚያሸጋግር እርምጃ በዛሬው ዕለት ወስደዋል፡፡ በዛሬው ዕለት ተጀምሮ የነበረው እና ለቀጣዮቹ ሶስት ቀናት እንዲካሄድ መርሃ ግብር ወጥቶለት የነበረውን የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ፈተና በሀገር አቀፍ ደረጃ እንዲቋረጥ ማድረግ ችለዋል፡፡ አስተባባሪዎቹ ከፈተናው ዕለት አንድ ቀን አስቀድመው በ”ፌስ ቡክ” ይፋ ያደረጉት የእንግሊዘኛ ፈተና እና ምላሹ ለፈተናው መቋረጥ ሰበብ እንደሆነ ትምህርት ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ ገልጿል፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ለዋዜማ እንደገለጹት አስተባባሪዎቹ ፈተናዎቹን እና መልሶቹ በእጃቸው ያስገቡት ከፈተናው ሶስት ሳምንት በፊት ነበር፡፡ “በመላው ኦሮሚያ የሚገኙ ተማሪዎች ለወራት በዘለቀው ተቃውሞ ምክንያት በትምህርት ገበታቸው ላይ መገኘት ባለመቻላቸው በሌሎች ክልሎች ካሉ ተማሪዎች እኩል ፈተና ላይ ሊቀመጡ አይገባም” የሚል መከራከሪያ ያነገቡት አስተባባሪዎች ወደ ዛሬው እርምጃ ከመግባታቸው በፊት ሌሎች አማራጮችን መሞከራቸውን ያስረዳሉ፡፡

ይህ ጉዳይ በቀጥታ ይመለከተዋል ካሉት ከኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ጋር ለመነጋገር መሞከራቸውን የሚገልጹት አስተባባሪዎች በመጀመሪያ ተቀባይነት አግኝተው እንደነበር ይናገራሉ፡፡ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ከፌደራል ትምህርት ሚኒስቴር ጋር ከተነጋገረ በኋላ ግን የተደረሰበት ስምምነት መፍረሱን ያስታውሳሉ፡፡

ትምህርት ሚኒስቴር ፈተናው ለሌላ ጊዜ የሚተላለፈው አስተባባሪዎቹ እንደጠየቁት በክልል ደረጃ ሳይሆን በተወሰኑ ቦታዎች ብቻ እንደሚሆን ከሳምንታት በፊት በይፋ አሳውቋል፡፡ በዚህም መሰረት በኦሮሚያ በሚገኙ 23 ትምህርት ቤቶች የ10ኛ ክፍል ፈተና ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ ሲደረግ ዛሬ ተጀምሮ ለነበረው የ12ኛ ክፍል ፈተና ደግሞ 12 ትምህርት ቤቶች ይሁንታ አግኝተው ነበር፡፡

በዚህ የተከፉት አስተባባሪዎች የተማሪዎች እና ወላጆችን ጥያቄ ያነገቡ የሀገር ሽማግሌዎች በጉዳዩ ላይ ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ያደርጋሉ፡፡ ይህም ግን የሚፈለገውን ውጤት አላመጣም፡፡ በዚህ ተስፋ ያልቆረጡት አስተባባሪዎች ከሁለት ሳምንት በፊት የስልክ ዘመቻ ይጀምራሉ፡፡ ጉዳዩ ይመለከታቸዋል የተባሉ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ባለስልጣናትን ስልክ በማህበራዊ ድረ-ገጾች በማውጣት የተቃውሞው ደጋፊዎች እየደወሉ ግፊት እንዲያሳድሩ ያደርጋሉ፡፡

በመንግስት በኩል ለዘመቻው የተሰጠው ምላሽ ተመሳሳይ ነበር፡፡ ይህንን ያገናዘቡት አስተባባሪዎች የፈተናው ቀን ሲቃረብ ሁለት ዕቅዶች ይነድፋሉ፡፡ የመጀመሪያው ሀገር አቀፍ የሆነ ተቃውሞ በመጥራት ፈተናውን ማደናቀፍ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ፈተናዎቹን አስቀድሞ በኢንተርኔት መልቀቅ እንደነበር ምንጮች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ ፈተናዎቹን አስቀድመው ያገኙት አስተባባሪዎች ተቃውሞ መጥራት ሳያስፈልጋቸው የፈተናውን መቃረብ መጠበቅ ያዙ፡፡

በዚህ መሀል ግን ለኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ እና ለትምህርት ሚኒስቴር “የመጨረሻ ዕድል” መስጠታቸውን ይናገራሉ፡፡ አስተባባሪዎቹ በእጃቸው የገቡትን ፈተናዎች ለሁለቱም ተቋማት በመላክ በኦሮሚያ የፈተናውን ወቅት እንዲያዛውሩ በድጋሚ መጠየቃቸውን ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ሁሉ በኋላ በትላንትናው ምሽት በመጀመሪያ ይሰጥ የነበረውን የእንግሊዘኛ ፈተና በ”ፌስ ቡክ” አማካኝነት ይፋ ለማድረግ መገደዳቸውን ያብራራሉ፡፡  

መንግስት በበኩሉ ፈተናው ተሰረቀ የተባለው ከእውነት የራቀ እንደሆነ እና ተማሪዎች ተረጋግተው በፈተና ቦታ እንዲገኙ በትላንትናው ዕለት አስታውቆ ነበር፡፡ የፈተና ወረቀቱ የተሰረቀበትን ቦታና ተሳታፊ ግለሰቦችን ለመለየት ሁለት አስቸኳይ ስብሰባዎች ተደረገዋል ፡፡ ፈተናው መቋረጡን መንግስት በይፋ ካስታወቀ በኋላ ግን ዛሬ ሁለት አስቸኳይ ስብሰባዎች ተደርገው የፈተና ወረቀቱ ተሰርቆ የወጣበትን ቦታና ተሳታፊ ግለሰቦችን ለመለየት በሚቻልበት መንገድ ላይ ውይይት ተደርጓል። የመንግስት የፀጥታ ሀላፊዎችን ያካተተው ይህ ስብሰባ በድጋሚ ነገ ተገናኝቶ ምክክሩን እንደሚቀጥል የዋዜማ ምንጮች ተናግረዋል። አዲስ ፈተና ማዘጋጀትና አዲስ የፈተና መርሀ ግብር ማውጣት በሚቻልበት መንገድ ላይም ተመሳሳይ ስብሰባ መደረጉን ለመረዳት ችለናል። 

ዛሬ ጠዋቱን ወደ ፈተና ጣቢያ የተመሙ ተማሪዎች በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ሆነው ነበር፡፡ ፈተናውን ከሚያስፈጽመው የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናናፈተናዎች ኤጀንሲ እና በበላይነት ከሚመራው ትምህርት ሚኒስቴር በቅርበት ርቀት የሚገኘው የዳግማዊ ምኒልክ የከፍተኛ ትምህርት መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች ረፋዱ ላይ ተመሳሳይ ስሜት ያንጸባርቁ ነበር፡፡

መንግስት ዘመም የሆነው ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ወደ አራት ሰዓት ግድም በ”ሰበር ዜና”ው ፈተናው መቋረጡን ቢያውጅም የዳግማዊ ምኒልክ ተማሪዎች ፈተና ላይ ነበሩ፡፡ ፈተናቸውን ጨርሰው ሲወጡ እንኳ ከሰዓት ለሌላ ፈተና እንደሚመለሱ ነበር የሚያውቁት፡፡ በአንጻሩ “ቦሌ ሆምስ” አካባቢ የሚገኘው የቦሌ ኮሚዩኒቲ ተማሪዎች ፈተናቸውን ሰርተው ካጠናቀቁ በኋላ “ፈተናው እንደተቋረጠ እና ጉዳዩን በሚዲያ ተከታተሉ” እንደተባሉ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡

በኮኮበ ጽብሃ  ትምህርት ቤት የነበረው ትዕይንት ግን ለየት ይላል፡፡ ፈተናው ተሰረዘ ስለመባሉ ጭምጭምታ የሰሙ ተማሪዎች ስለጉዳዩ ለማጣራት በትምህርት ቤታቸው ቅጽር ግቢ በር ላይ ተሰብስበው ጥያቄ ሲያቀርቡ በፖሊስ እንዲበተኑ መደረጉን የዓይን እማኞች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ በዳግማዊ ምኒልክ ትምህርት ቤት ደጃፍ ላይም በርካታ የፌደራል እና የአዲስ አበባ ፖሊሶች ጥበቃ ሲያደርጉ ውለዋል፡፡

“ጠዋት ወደ ፈተናው ስንገባ ፖሊሶቹ በጥብቅ ነበር የፈተሹን ይላል” አንድ ተፈታኝ፡፡ “ካልሲያችን እንኳ አልቀራቸውም” ይላል በእጁ ወደጫማው እያመለከተ፡፡

ፖሊሶቹ ፍተሻውን ቢያጠናክሩም ተማሪዎች ከአንድ ቀን በፊት በ”ፌስ ቡክ” ተለቀቀ የተባለውን መልስ ደብቀው ከመግባት አላገዳቸውም፡፡ በፌስ ቡክ ከተለቁቁት ጋር ተመሳሳይ ኮድ ያላቸው ፈተናዎች የደረሳቸው ተፈታኞች ደብቀው ያስገቡትን መልስ በመገልበጥ በፍጥነት እንዳጠናቀቁ ተማሪዎች

“አጠገቤ የነበረው ተማሪ ጥያቄዎቹን እንኳ አያነብም ነበር፡፡ ፈተናውን የጨረሰው በ30 ደቂቃ ውስጥ ነበር” ይላል ለፈተናው የተመደበውን ሁለት ሰዓት አጠናቅቆ የወጣ የዳግማዊ ምኒልክ ተማሪ፡፡

አራት ኪሎ ወደ አምስት ሰዓት ግድም አካባቢው የተለያዩ ዩኒፎርም በለበሱ ተማሪዎች ተሞልቶ ነበር፡፡ ሁሉም እጅ ላይ የተሸበለለ ነጭ ወረቀት ይታያል፡፡ አብዛኞቹ ላይ የወትሮው ከፈተና በኋላ ያለ ስሜት አይነበብም፡፡ እዚህም እዚያም እጅብ ብለው ቆመው ብጣሽ ወረቀት አሊያም የሞባይል ስልክ ላይ  አተኩረው ይወያያሉ፡፡ አንዳንዶቹ ጥያቄዎቹን በ”ፌስ ቡክ” ወጣ ከተባለው ጋር ያመሳክራሉ፣ ሌሎቹ መልስ ብቻ የተጻፈበትን ወረቀት ይዘው ከራሳቸው ምላሽ ጋር ያስተያያሉ፡፡ ሁሉም ላይ መደናገር ይነበባል፡፡

አብዛኞቹ ተፈታኞች “ተሰርቆ በፌስ ቡክ ወጣ” ስለተባለው ፈተና ሰምተዋል፡፡ ሁሉም ግን ማን ይህን እንዳደረገው እና ለምን ተብሎ እንደተደረገ ግንዛቤው የላቸውም፡፡ ፈተናው መቋረጡን ግን የወደዱት አይመስልም፡፡ “በድጋሚ ፈተና ወቅት ከብዶ እና ጠንክሮ ይመጣብናል” የሚል ስጋት ይዟቸዋል፡፡ “ልፋታችን ከንቱ ቀረ!” በሚል የሚቆጩም ታይተዋል፡፡ ፈተናው መቋረጡን የሰሙ ተፈታኞች ሲያለቅሱ መገናኛ አካባቢ እንዳስተዋሉ አንዲት የአይን እማኝ ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡