Condomዋዜማ ራዲዮ- በኢትዮጵያ የሚከፋፈለው ኮንዶም የጥራት ደረጃ አጠያያቂነት ሲያወዛግብ ቆይቷል። ከጥቂት ዓመታት በፊት የደራሲ ዳግማዊ ቡሽ “ኮንዶም ኤድስን ይከላከላል?” የተሰኘ መጽሐፍ ያስነሳው ክርክርና ሙግት ይታወሳል፡፡ ከሠሞኑ ደግሞ ሲደባበስና ሲሸፋፈን የቆየው ችግር ዕርቃን ወጥቷል፤ ጥራታቸውን ያልጠበቁ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኮንዶሞች በአንድ የሕንድ ኩባንያ አማካይነት ወደ ሃገር ውስጥ ገብተው አገልግሎት መስጠት የሌለባቸው ኮንዶሞች መሠራጨታቸው ታውቋል፡፡ ዜናው የፈጠረው ሥጋት እንደዋዛ አይታለፍም፤ አንድምታውም ለፍቺ ያዳግታል፡፡

የዳንኤል ድርሻን ዘገባ መዝገቡ ሀይሉ በድምፅ ያገኙታል፣ ያድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ


በአስደንጋጭ ሁኔታ እየተስፋፋ የነበረውን ኤች.አይ.ቪ ኤድስን በመቆጣጠሩ ረገድ የኮንዶም ሚና ቀላል አልነበረም። ከፌደራል ኤችአይቪ ኤድስ መቆጣጠሪያና መከላከያ ጽቤት በተገኘ መረጃ ከ7 ዓመት በፊት 70 ሚሊዮን የነበረው የኮንዶም ሥርጭት እ.አ.አ በ2015 ዓ.ም ወደ 203 ሚሊዮን ጨምሯል፡፡ አደጋው ግን ሲቀንስ አልታየም፡፡

“ከ2000 እስከ 2014 ከሠሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት የኤችአይቪ ኢንፌክሽን በ41 ከመቶ ቢቀንስም ከዓለም 66 ከመቶ የሚኾነው አዲስ ተጠቂ የሚገኘው በዚሁ አካባቢ ነው”። ሲል ሂደቱን ያስረዳው UNAIDS በ2014 ብቻ ከሠሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ አገራት 1.4 ሚሊዮን አዲስ የኤችአይቪ ኢንፌክሽን መመዝገቡን አስታውቋል፡፡

ባለፈው ወር በአዳማ ከተማ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በተሰጠ ሥልጠና ላይ ሲገለጽ እንደሰማነው በኢትዮጵያ የኤችአይቪ ቫይረስ በደማቸው እንደሚገኝ የሚያውቁ የቫይረሱ አዲስ ተጠቂዎች ብዛት 24 ሺህ ይደርሳል፡፡ የተጠቂዎች አጠቃላይ ብዛት ደግሞ 740 ሺህ እንደሚደርስ ተጠቁሟል።

እንደ ኢትዮጵያ ያሉ አገራት እስከ 2030 ዓ.ም ድረስ ከኤች.አይ.ቪ ኤድስ ነጻ ለመሆን ዕቅድ ሠንቀዋል ቢባልም የበሽታው ሥርጭት እያደር ሲጨምር ይስተዋላል፡፡ ከ3 ዓመት በኋላ የቫይረሱ ክትባት ይጀመራል የሚባለው “ጭላንጭል” ሳይደምቅ ጥራት የጎደላቸው ኮንዶሞች ሥርጭት ጉዳይ መከሰቱ አሰቃቂ ሆኗል፡፡ ወደ ሃገር ውስጥ የገቡትን ደረጃቸውን ያልጠበቁ ኮንዶሞች ግዢ የፈፀመው መንግስታዊው ተቋም የመድሃኒት ፈንድ እና አቅርቦት ባለሥልጣን ሲሆን፣ አቅራቢው ደግሞ HLL Life Care Ltd. የተሠኘ የሕንድ ኩባንያ ነው፡፡

ግዢውን የመድሃኒት ፈንድ ቢያከናውነውም የጥራት ምርመራ የሚያካሂደው “የምግብ፣ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳዳርና ቁጥጥር ባለሥልጣን” የሚባለው ሌላኛው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ነው፡፡ ወደ ሃገር የሚገቡትን የሕክምና መገልገያዎች ጥራት፣ ግምገማ እና ምዝገባ የሚያደርገውና የማስወገድም ሆነ ደረጃ የማውጣት ሥልጣን ያለው ይኸው ተቋም ነው፡፡

ተቋሙ ከውጪ ከሚገባው ጥቅል እሽግ ኮንዶም ናሙና ወስዶ የቁመት፣ የስፋት፣ የመለጠጥ፣ የጥንካሬ፣ የማለለስለሻ ቅባት ጥራት፣ እንዲሁም አስተሻሸጉን እና የጥቃቅን ቀዳዳዎች መኖር አለመኖርን ይመረምራል፡፡ ከተገዛው እሽግ በዘፈቀደ የናሙና ምርጫ ባካሄደው ምርመራም በብዙ የኮንዶም ናሙናዎች ላይ ቀዳዳ መገኘቱን አረጋግጧል፡፡

ጥራትን በተመለከተ ምርመራውን ያካሄደው “የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን” የዓለም ጤና ድርጅትን ደንብና ሥርዓት እንደሚከተል ነው የሚገለጸው፡፡ ለምርመራ የሚወስደው የናሙና መጠን እንደየ እሽጉ ሊለያይ ይችላል፡፡ በአንድ እሽግ ውስጥ ከ50 ሺሕ እስከ 150 ሺህ ኮንዶሞች ቢኖሩ ለምርመራ ናሙናነት የሚወሰደው ብዛት ከ1‚444 እስከ 3‚444 ሊደርስ ይችላል፡፡ በዚህ የናሙና ምርጫ መሰረት ከተወደው ናሙና ውስጥ ከ361 በላይ የሚሆነው ኮንዶም ቀዳዳ ተገኝቶበታል ተብሏል፡፡

ግዢውን ያከናወነው የመድሃኒት ፈንድ ባለስልጣን ከሕንዱ ኩባንያ ስለተረከበው የኮንዶም ብዛትም ሆነ ስለሌሎች ተጋዳኝ ጉዳዮች ምላሽ ለመስጠ ፈቃደኝነት እንደጎደለው የዘገበው አዲስ ፎርቹን ጋዜጣ ያናገራቸው የፈንዱ ምክትል ዳይሬክተር አቶ የማነብርሃን ታደሰ “ጉዳዩ ገና በእንጥልጥል ላይ ስለሆነ ለአደባባይ የሚበቃና የሚገለጽ ዝርዝር የለንም” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ ምርመራውን ያካሄደው ድርጅት የኤፍ.ኤም.ሃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ምክትል ኃላፊ አቶ ቢቂላ ባይሳ ግን “ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ለምርመራ ወደ ላቦራቶሪያችን በሚመጡ ኮንዶሞች ላይ የሚገጥመን ዋናው ችግር የቀዳዳ መገኘት ነው” ሲሉ ዋነኛውን የችግሩን ምክንያት ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ የሚሰራጨው ኮንዶም እንደ ዋጋው ሁኔታ በሶስት ዓይነት መንገድ ለተጠቃሚው ይዳረሳል፡፡ በአንጻራዊነት ውድ በሚባል ዋጋ የሚሸጡ፣ ቀደም ሲል ዲኬቲ ያከፋፍላቸው እንደነበሩት አይነት የሚደጎሙ እና በነጻ የሚሰራጩ ናቸው፡፡ ከውዶቹ ኮንዶሞች ውጪ ያሉት የድጎማና የነጻ ሥርጭት ኮንዶሞች ዋጋ እንደ ዩኤስኤአይዲ እና ፔፕፋር ካሉ ለጋሾች በሚገኝ ርዳታ ይሸፈናል፡፡ የነጻ ኮንዶሞች በአብዛኛው በመንግስት ጤና ተቋማት ሲከፋፈሉ፣ በቡና ቤት ለሚሰሩ ሴቶችም ይታደላሉ፡፡

እ.ኤ.አ በ2009 ዓ.ም የአገሪቱን የኮንዶም ገበያ 70 ከመቶ ይሸፍን የነበረው “ዲኬቲ” አሁን ከ30 % በላይ መድረስ አልቻለም፡፡ ባለፈው ዓመት ብቻ ከሚያሰራጨው 60 ሚሊየን ኮንዶም ውስጥ 40 ሚሊየን ሚሆነው በአዲስ አበባ መጋዘኑ ውስጥ ሳይሸጥ ተከማችቶ ነው የተገኘው፡፡ በተመሳሳይ ዓመት የመድሃኒት ፈንድ የሚባለው የመንግስት ተቋም ብቻውን 60 ሚሊየን ኮንዶሞች ገዝቶ ማስገባቱን ምንጮች ጠቁመዋል፡፡

ይሕ በኮንዶም ግዢና ሥርጭት ውስጥ ያለውን የሙስና ችግር አመላካች መሆኑን የሚገልጹም አሉ፡፡ በጥራት ጉድለት አቤቱታ ቀርቦባቸው ለአስፈጻሚው የቀረቡ ጉዳዮች እልባት ሳያገኙ ለዓመታት ያለ መፍትሔ መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ለዚህም ይመስላል ብዙዎች “በሕይወት ላይ ቁማር በሚጣጣሉት” የዚህ ድርጊት ፈጻሚዎች ላይ ፈጣን ርምጃ ይወሰዳል ብለው የማያምኑት፡፡