PM Abiy Ahmed and President Emanuel Macron – credit PM Office

የኢትዮጵያና የምዕራባውያን ግንኙነት በተለይም ሀገሪቱ የዕዳ ሽግሽግና ተጨማሪ ብድር ለማግኘት ያላት ዕድል በጄኔቭ እየተካሄደ ባለው የሰብዓዊ መብት ጉባዔ ውሳኔ ይወሰናል። ጉባዔው በሰሜኑ ጦርነት የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ እንዲቀጥል አልያም እንዲቋረጥ ሊወስን ይችላል። ኢትዮጵያ ምርመራው እንዲቋረጥ በሙሉ አቅሟ ጥረት እያደረገች ነው። ዋዜማ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክታለች

ዋዜማ- የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ ወዲህ ሀገሪቱ ግንኙነቷን ለማደስ ፈጣን እርምጃዎችን ብትወስድም ከምዕራባውያኑ መንግስታትና አበዳሪ ተቋማት በኩል ያለው ምላሽ አጥጋቢ አለመሆኑን ዋዜማ ሰምታለች። 

በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ሻክሮ የቆየው የኢትዮጵያና የምዕራባውያን ግንኙነት መሻሻል ካሳየ ወዲህ መንግስት አንገብጋቢ ብሎ ከያዛቸው ጉዳዮች መካከል ከለጋሾችና ከኣአበዳሪዎች ተስተጓጉለው የነበሩና አዳዲስ ድጋፎችን ማሰባሰብ ላይ ያተኮረ ነው።

እነዚህ የውጪ ድጋፎች ካልተገኙ የሀገሪቱ የውጪ ምንዛሪ በመሟጠጡ እንዲሁም ሀገሪቱ ከዚህ በፊት የተበደረችውን ዕዳ ለመክፈል አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ የዓለም የገንዘብ ድርጅት ድጋፍ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ቀውስ ቀዳሚው ትኩረት እንዲሆን አድርጎታል። 

ዋዜማ ከአበዳሪ ተቋማት፣ ከመንግስትና ከዘርፉ ሙያተኞች ባሰባሰበችው መረጃ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አንገብጋቢውን ድጋፍ ለማግኘት መራር ውሳኔ እንዲያሳልፉ የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። 

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ለኢትዮጵያ የዕዳ ሽግሽግ እንዲያደርግ ባለፈው ዓመት የቀረበለትን ጥያቄ ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ እንዲጓተት አድርጎ አሁንም ድረስ ሀገሪቱ የጠየቀችው የዕዳ ሽግሽግ ተፈፃሚ አልሆነም። ይህ መጓተት ሀገሪቱ የሚያስፈልጋትን የውጪ ምንዛሪ አሰባስባ ዕዳዋን ለመክፈል እጅ አጥሯታል። 

በሌላ በኩል ከአራት ዓመት በፊት የሀገሪቱን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ ቃል የተገባው የዓለም ባንክ፣ የዓለም የገንዘብ ድርጅት፣ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት  የተለያዩ ድጋፎች በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ በመታገዳቸው የውጪ ንግድም ከገቢ ንግድ ጋር የተመጣጠነ ባለመሆኑ ችግሩ እንዲባባስ አድርጎታል። 

ምዕራባውያኑ እጅ ላይ ወድቀናል? 

የዓለም የገንዘብ ድርጅት ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ የብር የምንዛሪ ተመንን እንድታዳክም ባቀረበው ምክረ ሀሳብ በአንድ ጊዜ 15 በመቶ ዝቅ የተደረገ ሲሆን አሁንም ብር ካለበት የምንዛሪ አቅም የበለጠ ዝቅ እንዲል የገንዘብ ድርጅቱ ፍላጎት አለው። 

የገንዘብ ሚንስትር ደዔታ እዮብ ተካልኝ መንግሥት የብር ምንዛሬን ዝቅ ለማድረግ አቅዷል ተብሎ የተሰራጨው መረጃ “መሠረተ ቢስ ነው” ሲሉ በወቅቱ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት አስተባብለዋል። 

እዮብ መንግሥት መሠረታዊ የፋይናንስ ማሻሻያ የማድረግ ፍላጎቱ እንደተጠበቀ መሆኑን ገልጸው፣ ሆኖም የመንግሥት የፋይናንስ ማሻሻያ የብር ምንዛሬ ግሽበት ስጋት ሊፈጥር አይገባውም ብለዋል። 

መንግስት የሚጠበቀውን የዕዳ ሽግሽግ ባለማግኘቱ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኳታር ያላደጉ ሀገሮች ጉባዔ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ የዕዳ ሽግሽግ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን አንስተው በምሬት ተናግረዋል። 

ከሁለት ሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ የመሩት የልዑካን ቡድን ወደ ፈረንሳይ አቅንቶ በቡድን ሀያ ሀገራት በፀደቀውን የዕዳ መክፈያ ጊዜ የማራዘም መርሀ ግብር ኢትዮጵያ ተጠቃሚ እንድትሆን የፈረንሳዩ አቻቸውን አጥብቀው ተማፅነዋል። 

ከዐብይ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንዳላቸው የሚነገርላቸው ኢማኑዔል ማክሮን  ኢትዮጵያ የጠየቀችው የዕዳ ማራዘሚያ ከአበዳሪዎች ወገን ይሁንታ እንደሚያገኝና ሀገራቸው ለዚህ መሳካት ድጋፍ እንደምታደረግ ቃል ገብተዋል። ፈረንሳይና ቻይና የኢትዮጵያን የዕዳ ማራዘም ጥያቄ በጋራ ሰብሳቢነት ይመሩታል። 

የሀገሪቱ አጠቃላይ የብድር ዕዳ 29 ቢሊየን ዶላር ይገመታል። መንግስት የዕዳውን መጠን በይፋ አሳውቆ አያውቅም። 

የዐብይ “የልመና” ክህሎት መፍትሄ ይዞ ይመጣ ይሆን? 

ዐብይ ቀደም ሲል በፈረንሳይ ባለፉት ቀናት ደግሞ በኳታር በነበራቸው ቆይታ ከሀገሪቱ የብድርና የዕዳ ሽግሽግ ባሻገር በጠቅላይ ሚንስትሩ መሪነት ስለሚካሄዱ ፕሮጀክቶች ለባለሀብቶችና ለመንግስታቱ ገለፃ አድርገዋል። በተለይ “ጫካ” ስለሚባለው የቤተመንግስት ግዙፍ ፕሮጀክት አበክረው ማስረዳታቸውን ለጉዳዩ ቅርብ ከሆኑ ምንጮች ተገንዝበናል። 

ፈረንሳይ የኢትዮጵያን ጦር ሀይል ለማሰልጠን ከ4 ዓመታት በፊት ቃል ገብታ የነበረ ቢሆንም በሰሜኑ ጦርነት ሳቢያ ድጋፏን መሰረዟ ይታወቃል። 

በጦርነት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት 30 ቢለየን ዶላር የሚጠጋ ድጋፍ ሀገሪቱ የሚያስፈልጋት ሲሆን ለመልሶ ግንባታ የሚሆን ድጋፍ ማግኘት አንዱ የመንግስት ትኩረት መሆኑን ከለጋሾች ጋር ውይይት እየተደረገበት መሆኑን ስምተናል። 

የኢትዮጵያ 60 በመቶ ያህል ብድር ከቻይና የተገኘ በመሆኑ ቻይና የብድር ማራዘሙን ጥያቄ እንድትቀበል ከፍተኛ የመንግስት የልዑካን ቡድን ወደ ቤጂንግ አቅንቶ የማግባባት ስራ ሰርቶ ተመልሷል። የቻይና መንግስት ምላሽ አወንታዊ መሆኑን የመንግስት ምንጮች ነግረውናል። 

ዕዳ መክፈያ ጊዜን ከማራዘም ጎን ለጎን ኢትዮጵያ በአፋጣኝ የሚያስፈልጋትን የዉጪ ምንዛሪ ለማግኘት በለውጡ ማግስት ቃል የተገባላትንና በሰሜኑ ጦርነት የተስተጓጎለ  የብድርና ድጎማ ድጋፎች እየተጠባበቀች ትገኛለች። 

ፈረንጆቹ ለምን አመነቱ? 

የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ የሰብዓዊና አንዳንድ አነስተኛ የልማት ድጋፎችን ለመቀጠል በሂደት ላይ ቢሆኑም ለኢኮኖሚ ድጎማ እንዲሆን ከዚህ ቀደም ቃል የተገባ ድጋፍ እስካሁን አልተለቀቀም። 

ከሁሉ በላይ ግን የአለም የገንዘብ ድርጅት በእንጥልጥል የተወው የ3 ቢሊየን ዶላር የኢኮኖሚ ተሀድሶ ድጋፍ አሁን እጅግ አንገብጋቢ  መሆኑን በጉዳዩ ላይ ተሳትፎ ያላቸው የዋዜማ ምንጮች ያስረዳሉ። 

የአለም የገንዘብ ድርጅትም ሆነ በአለም ባንክ በኩል የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት አግደውት የነበረውን ድጋፍ ለመቀጠል በር ከፋች ይሁን እንጂ በታሰበው ፍጥነት ድጋፉን ለመቀጠል አበዳሪዎች እንዳመነቱ ነው። 

አበዳሪዎችንም ሆነ ምዕራባውያንን ለማማለል የኢትዮጵያ መንግስት የኢትዮቴሌኮምን የተወሰነ ድርሻ ለውጪ ባለሀብቶች ለመክፈት እንዲሁም የውጪ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የጀመረውን ማሻሻያ እያፋጠነ ነው። 

የአለም የገንዘብ ድርጅት ብድር ለተጫናቸው ሌሎች የአፍሪቃ ሀገራት የብድር ሽግሽግ ካደረገላቸው መንፈቅ አልፏል። እንደ ግብፅና ኬንያ ያሉ ሀገራት ደግሞ ተጨማሪ ብድር ተፈቅዶላቸዋል። 

የኢትዮጵያን ጥያቄ ለመመልከት በተለምዶ የሚላከው የአለም የገንዘብ ድርጅት የግምገማ ቡድንም ወደ አዲስ አበባ የሚመጣበትን ቀጠሮ ሁለት ጊዜ ያህል አራዝሟል። 

የዕዳ ማሸጋሸጉንም ሆነ ተጨማሪ ብድር የማግኘቱ ነገር ለኢትዮጵያ አንገብጋቢ መሆኑን የተገነዘቡት አበዳሪዎች  የብር ከዶላር አንፃር ያለው የምንዛሪ መጠን የበለጠ እንዲዳከም ይፈልጋሉ። መንግስት ተጨማሪ ድርጅቶችን ወደ ግል እንዲያዞር (ለገበያ እንዲያቀርብ) ፍላጎት አላቸው። 

ሀገሪቱ መጠነ ሰፊ የታክስ ማሻሻያ እንድታደርግና የሚሰበሰበው የታክስ መጠን ከእጥፍ በላይ እንዲጨምር አበዳሪዎች ግፊት እያደረጉ ነው። 

ከአበዳሪና ለጋሾች የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መቀበል  ሊያስከትል ስለሚችለው አደጋ በመንግስት በኩል ሙሉ ግንዛቤ የተያዘ ሲሆን በተለያየ ጊዜም ክርክር እንደተደረገበትም ምንጮቻችን ነግረውናል። 

የጄኔቫው ትንቅንቅ

በጄኔቭ እየተካሄደ ያለው የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክርቤት ጉባዔ በዚህ ሳምንት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል። ይህ ውሳኔ የኢትዮጵያ መንግስት ከምዕራባውያን ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የሚወስን ይሆናል። 

ምክር ቤቱ በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈፀሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ ግኝቱን ለምክር ቤቱ እንዲያቀርብ አጣሪ ኮምሽን ከአንድ አመት በፊት አቋቁሟል። 

ይህ ኮምሽን ጉዳት ወደ ደረሰባቸው አካባቢዎች በተለይም ወደ ትግራይ ሄዶ ምርመራ ለማድረግ በኢትዮጵያ መንግስት ተከልክያለሁ ሲል ቆይቷል። 

የኢትዮጵያ መንግስት በበኩሉ ኮምሽኑ አደርገዋለሁ የሚለውን ምርመራ እንዲያቋርጥና እንዲፈርስ ፍላጎት አለው። ይህን ፍላጎቱን የሚገልፅ ምክረ ሀሳብ ለምክር ቤቱ አንዳንድ አባላት ማደሉንና በይፋ አጀንዳ አድርጎ እንደሚያቀርበው ይጠበቃል። 

አፍሪቃውያን ሀገራት በአለማቀፍ መድረክ በስብዓዊ መብት ጥሰት ሽፋን በድሀ ሀገሮች ላይ የመንግስት ግልበጣ ይደረጋል፣ ይህም ፍትሐዊ አካሄድ አይደለም ሲሉ ይቃወማሉ። 

አሁን ኢትዮጵያ የሰሜኑ ጦርነት ምርመራ እንዲቌረጥ እያደረገች ያለው ጥረት ሰሚ ጆሮ ካገኘ እጅግ አደገኛ ልማድ ሊሆንና ሌሎች ሀገራትም መስል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ሲሉ ከ70 በላይ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ተቃውሞ አቅርበዋል። 

አሜሪካና አውሮፓ በሰሜኑ ጦርነት የተፈፀሙ ወንጀሎች ተጣርተው  አጥፊዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ፍላጎት እንዳላቸው በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል። ኢትዮጵያ ምርመራው እንዲቋረጥ እንቅስቃሴ መጀመሯ እንደተሰማ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች አጀንዳው ተቀባይነት እንዳይኖረው ግፊት እያደረጉ መሆኑ ተሰምቷል። ሩሲያ (በዩክሬይን)ና ቻይናን   የመሳሰሉት ሀገራት እንደኢትዮጵያ ሁሉ  የሶስተኛ ወገን አጣሪ በሀገራቸው ጉዳይ እንዳይሰማራ የሚቃወሙ ሀገራት ናቸው። [ዋዜማ]