ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ በመጪው ሳምንት በፓርላማ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፓርላማ አባላት ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጡና አዲስ ያዋቀሩትን ካቢኔም ይፋ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

ሹም ሽሩ ያስፈለገው 28 የነበሩት የሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ወደ 20 ዝቅ እንዲሉ በማድረግ እንዲሁም አዳዲስ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች እንዲዋቀሩ በመደረጉ ነው። አንዳንድ የሚኒስቴር መስሪያቤቶች ደግሞ ይቀላቀላሉ።

የዋዜማ ምንጮቹ እንደገለጹት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ በሳምንቱ ሁለት ጊዜ ወደ ፓርላማ ይመጣሉ። ማክስኞ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ ሪፖርት ያቀርባሉ ጥያቄዎች ይመልሳሉ። ሐሙስ ደግሞ የካቢኔ ሚንስትሮቻቸውን ያስሾማሉ።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ በማከስኞው ስብሰባ በዋነኛ አጀንዳነት በተያዘላቸው መሰረት ባለፈው ሳምንት በአምስተኛው የፓርላማ ዘመን 4ኛ ዓመት የስራ ዘመን መክፈቻ ቀን ለሁለቱ የጋራ ምክርቤቶች ርዕሰ-ብሔሩ ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ባቀረቡት የመክፈቻ ንግግር ውስጥ የተዘረዘሩ ጉዳዮችን በተመለከተ ማብራሪያ እንደሚሰጡ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ የምክር ቤቱ አባላት በአገሪቱ በስፋት እየተከሰቱ በሚታዩት ብሔር ተኮር ግጭቶችና፣ በዜጎች ላይ እየደረስ ባለው መፈናቀሎችና ተያያዥ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ጥያቄ ለማቅረብ በጽህፈት ቤቱ በኩል በርካታ ጥያቄዎችን ማቅረባቸውን ዋዜማ ከምንጮቹ ለማወቅ ችላለች፡፡

በተመሳሳይም ለሐሙሱ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስተሩ የፌደራል መንግሥትን አስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር ለመወሰን ተዘጋጅቶ ረቡዕ መሰከረም30፣ 2011 ዓ.ም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የጸደቀውን ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ከምክርቤቱ ለሚነሱላቸው ጥያቄዎች ማብራሪያ ይሰጣሉም ተብሏል፡፡

ምክር ቤቱም እንደሚያጸድቀው የሚጠበቀው የዚሁ የአስፈጻሚ አካላትን ስልጣንና ተግባር እንደገና ለመወሰን የቀረበው ርቂቅ አዋጅን በተመለከተ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት በሰጠው መግለጫ ያስፈለገበትን ሶስት ምክንቶች መግለጹም ይታወሳል፡፡

እነሱም ወደኋላ የቀሩናያ ልተጠናቀቁ የ2ኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ሥራዎችን በቀሪው ጊዜ አካክሶ ለመፈጸም የሚያስችል አደረጃጀት በማስፈለጉ፤ በሀገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ የሚያስችል አደረጃጀትን መከተል በማስፈለጉ እንዲሁም የአስፈጻሚ አካላትን ቁጥር ቀልጣፋ፣ ወጪ ቆጣቢና ውጤታማ ለማድረግ በማስፈለጉ የሚሉት ናቸው፡፡

በምክር ቤቱም ውሳኔ የካቢኔ አባላት ቁጥር ከ28 ወደ 20 እንዲቀንስ ተደርጓል፤ ዋና ዋናዎቹ ለውጦችም ውስጥ የንግድ ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ተዋህደው – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር   ሲሆን የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እና የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ተዋህደው – የኢኖቬሽንና የቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የሚሉት ይገኙበታል፡፡
እንዲሁም የከተማ ልማት ሚኒስቴር እና የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር ተዋህደው – የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስቴር እንዲሆን ሲወሰን ሌሎች ተጠሪ ተቋማትም በተመሳሳይ ሁኔታ እንዲዋሃዱ ውሳኔ የተሰጠባቸው ይገኛሉ::

ሌላው ቁልፍ ውሳኔ በአገር ውስጥ ሰላም እና የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን በሕዝቡ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፖለቲካ ማህበረሰብ በጋራ መገንባት ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ “የሰላም ሚኒስቴር” እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
ከትምህርት ሚንስቴር ሁሉንም ዩኒቨርሲቲዎች እና የቴክኒክና ሙያ ተቋማትን በመውሰድ እንዲሁም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚንስቴር ስር የሚገኙት ሁለቱን ዩኒቨርሲቲዎች በመጨመር “የከፍተኛ ትምህርትና የሳይንስ ሚንስቴር” ተብሎ እንዲደራጅ ተወስኗል::

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን የገቢዎች ሚኒስቴር እና ለሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ተጠሪ የሆነ የጉምሩክ ኮሚሽን በመሆን ሁለት ተቋማት ሆነው እንዲደራጁ ተወስኗል፡፡
በአዲሱ አደረጃጀት የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ሚንስቴር ቀርቶ በቀጣይነት የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ለማስተዳደር መሰረታዊ ሚናቸው ንግድ የሆኑትን በመለየት የመንግስትን የባለቤትነት ሚና በተገቢው ሁኔታ የሚያስተዳደር “የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲ” በገንዘብ ሚኒስቴር ሥር እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡ ይህም የመንግሥት ቁልፍ ሚና የሆነው ሬጉሌሽን (ቁጥጥር) በልማት ድርጅቶች ላይ ካለው የባለቤትነት ሚና ተለይቶ እንዲታይ እንደሚያግዝ ታምኖበታል፡፡
ረቂቅ አዋጁ ሌሎች መለስትኛ ለውጦችንም የያዘ ሲሆን: በሐሙሱ መደበኛ ስብሰባ ምክር ቤቱ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል::