Gondar City
Gondar City

ዋዜማ ራዲዮ-በጎንደር ትናንት የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ በፌደራሉ መንግስት፣ የትግራይና የአማራ ክልል መንግስታት እንዲሁም የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያቤት መካከል ከፍተኛ አለመግባባት ተከስቷል። የትግራይ ክልል በአንድ ብሄር  ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተከፍቷል ሲል ከሷል። የአማራ ክልል የሀገሪቱ የደህንነት መስሪያቤት ምንም መረጃ ሳይነግረን በክልሉ ትርምስ እንዲፈጠር አድርጓል እያለ ነው። የፌደራሉ መንግስት (የጠቅላይ ሚንስትሩ ፅህፈት ቤት) በበኩሉ ጉዳዩ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ድርድር ማድረግና “ፀረ ሰላም ሀይሎችን” ከህዝቡ የመነጠል ስራ እንዲሰራ አዟል።

ይሁንና የደህንነት መስሪያቤቱ በጉዳዩ ላይ ለሳምንታት ሲዘጋጅበት የነበረና የስለላ ሰራተኞቹን ከረጅም ቀናት በፊት አሰማርቶ የሚቃወሙትን ለማደን ሲያደባ መቆየቱን የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ። ሌሊቱን በስልክ ከአዲስ አበባ ሹማምንት ጋር ረጅም ስብሰባ የተደረገ ሲሆን የክልል ባልስልጣናትም እስክ ማለዳ የዘለቀ ውይይት አድርገዋል ተብሏል። ተቃውሞው መንግስት ባላሰበው መንገድ ወደ ሰፊ ህዝባዊ ቁጣ መሸጋገሩ አዲስ አበባ ድረስ ድንጋጤ መፍጠሩ እየተነገረ ነው። የደህንነት መስሪያቤቱ የአማራ ክልል ለግሟል በአካባቢው መረጋጋት ለማምጣት አልቻለም ሲል ከሶታል። “የጎንደር አካባቢ ከጊዜ ወደጊዜ የተቃዋሚዎች ማዕከል እንዲሆንና ለህግና ስርዓት አልገዛም እንዲል ያደረጉት የአማራ ክልል ውስጥ ያሉ የውስጥ አርበኞች ናቸው” በሚል መገምገሙን የክልሉ መስተዳድር ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል።

ትናንት ጠዋት በጎንደር በተቀሰቀው ግጭት በትንሹ ስድስት ሰዎች መገደላቸውን የከተማው ነዋሪዎች የገለጹ ሲሆን መንግስት በበኩሉ ሶስት የፌደራል ፖሊስ አባላት እና አንድ ግለሰብ መሞታቸውን አስታውቋል፡፡

ማከሰኞ ሐምሌ 5 የተቀሰቀሰው ግጭት የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች የወልቃይት የማንነት ጥያቄ አስተባባሪዎችን ለማሰር ወደ ጎንደር ከተማ በተሰማሩበት ወቅት የተጫረ እንደሆነ የከተማው ነዋሪዎች ለዋዜማ ገልጸዋል፡፡ እስራቱ የተጀመረው መቼ እንደነበር ግን በነዋሪዎቹ በኩል የሚቀርበው የጊዜ መረጃ የተለያየ ነው፡፡ እንዳንዶች ከለሊቱ 10 ሰዓት እንደጀመረ ሲናገሩ ሌሎች ከጠዋቱ እንድ ሰዓት ይላሉ፡፡ ጥቂቶች ደግሞ ከረፋዱ አራት ሰዓት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ሁሉም ነዋሪዎች ግን ከፍተኛ የተኩስ ድምጽ ይሰማ የነበረው በማራኪ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 18 ውስጥ እንደነበር ይስማማሉ፡፡ ቦታው ደሳለኝ ትምህርት ቤት አካባቢ እንደሆነም ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ቦታ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ከተማዋ ተስፋፍቶ አብዛኛውን ቦታ እንዳዳረሰ ይገልጻሉ፡፡ ወደ አዘዞም መዝለቁን ይናገራሉ፡፡

“ከሰዓት በኋላ ወደ ስራ ለመሄድ ከባድ ነበር” ትላለች ጠዋቱን በስራ ገበታዋ አሳልፋ ነገሮች እስኪበርዱ ወደ ቤቷ ሄዳ የነበረች የመንግስት ሰራተኛ፡፡ “ለተቃውሞ የወጡት አብዛኛዎቹ ወጣቶች ናቸው” ስትል ታክላለች፡፡

የተቆጡት የከተማዋ ነዋሪዎች ወደ 10 ሰዓት ግድም ፒያሳ ቋራ ሆቴል ጀርባ ቆሞ የነበረውን እና ንብረትነቱ የ“ሰላም ባስ” የሆነውን አውቶብስ አቃጥለዋል፡፡ የተቃጠለው አውቶብስ ሰኞ ዕለት ከአዲስ አበባ ተሳፋሪ ጭነው ወደ ጎንደር ከሄዱ ሁለት አውቶብሶች አንደኛው ነበር፡፡

ለማክሰኞ ሁለት አውቶብስ የሚሞላ በቂ ተሳፋሪ ባለመኖሩ አንዱ ወደ ኋላ እንዲቆይ መደረጉን የሰላም ባስ ምንጮች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ የተቃጠለው አውቶብስ ረቡዕ ከሌላ አውቶብስ ጋር በመሆን ወደ አዲስ አበባ ለመመለስ ትኬት ተሸጦለት ነበር፡፡

ከሶስት ዓመት በፊት ከቻይናው “ዮቶንግ” የአውቶብስ ማምረቻ ከተገዙት የህዝብ ማመላላሻዎች አንዱ የሆነው እውቶብሱ ወደ 24 ሚሊዮን ብር አካባቢ እንደወጣበት ምንጮች ያስረዳሉ፡፡ በጎንደር የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ “ሰላም ባስ” ከነገ ጀምሮ ወደ ከተማይቱ የሚያደርገውን መደበኛ ጉዞ ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን ምንጮች ጨምረው ገልጸዋል፡፡

ለተቃውሞ የወጡ የከተማይቱ ነዋሪዎች አውቶብሱን ከማቃጠል ባሻገር መንገዶችን በአካባቢው ባገኙት ነገር ሁሉ ሲዘጉ እንደነበር የአይን እማኞች ለዋዜማ ተናግረዋል፡፡ በማህበራዊ ድረ-ገጽ የተሰራጨ ያልተረጋገጠ ፎቶ አልጋ ሁሉ መንገድ ለመዝጊያነት ጥቅም ላይ መዋሉን አሳይቷል፡፡

ማክሰኞ ቀኑን ሙሉ በተኩስ ስትናጥ የዋለችው ጎንደር ማምሻውን በተመሳሳይ ሁኔታ መቀጠሏን ነዋሪዎች ያስረዳሉ፡፡ የተኩስ ድምጹም እስከ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ተኩል ድረስ ይሰማ ነበር፡፡ ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የጎንደር ነዋሪዎች ማምሻውን ቤታቸው ከትተው መጪውን በስጋት እየጠበቁ ነበር፡፡

“ሁሉም ቤቱን ዘግቶ ነው ያለው” ይላል አንድ በማስጎበኘት ስራ ላይ የተሰማራ ወጣት፡፡