FILE
  • መንግሥት 5 አውሮፕላኖችና 11 የአሰሳ ድሮኖች ገዝቷል

ዋዜማ ራዲዮ- የኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የበረሃ አንበጣ ርጭትና አውሮፕላኖችን የመከስከስ አደጋ መካለከል የሚስችለው የደሕንነት መቆጣጠሪያ ጣቢያ (Situation Room) መገንባቱን ዋዜማ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ አረጋግጣለች፡፡ 

የመቆጣጠሪያ ጣቢያው ለበረሃ አንበጣ ርጭት የሚንቀሳቀሱ አውሮፕላኖችንና የአሰሳ ድሮኖችን እንቅስቃሴ፣ የሚከታተልና መረጃ የሚሰጥ መሆኑን ዋዜማ የነጋገረቻቸው ኃላፊ ጠቁመዋል፡፡  የርጭት አውሮፕላኖችና የአሰሳ ድሮኖቹ ከመንቀሳቀሳቸው በፊት ያለውን አየር ሁኔታ መረጃ መሰጠት ያስችላል የተባለው የመቆጣጠሪያ ጣቢያ፣ ከዚህ በፊት ባለመኖሩ አራት አውሮፕላኖች በርጭት ላይ እያሉ መከስከሳቸው ኃላፊው አስታውሰዋል፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ በኢትዮጵያ ተከስቶ በነበረው የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ወቅት ጋጠሙት አራት የአውሮፕላን መከስከስ አደጋዎች የአየር ሁኔታውንና የመሬት አቀማመጥ ሁኔታ መረጃ አስቀድሞ መረጃ የሚሰጥን የሚቆጣጠር ጣቢያ ባለመኖሩ ነበር፡፡ 

በወቅቱ በርጭት ላይ እያሉ የተከሰከሱት አውሮፕላኖች አብራሪዎች ስለ አየር ሁኔታውና ስለ መሬት አቀማመጡ ምቹነት ቅድመ መረጃ የሚገኙበት ሁኔታ ባለመኖሩ አደጋው ሊጋጥም መቻሉንም አስታውሰዋል፡፡

አሁን ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ሊያጋጥማት የሚችለውን የበረሃ አንበጣና በአገር ውስጥ ያለውን የአሰሳ ሥራ በመቆጣጠሪያ ጣቢያው እየተከናወነ ነው ተብሏል፡፡

በሌላ በኩል ግብርና ሚኒስቴር ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የፌዴራል መንግሥት አምስት የርጭት አውሮፕላኖችንና 11 የአሰሳ ድሮኖች መግዛቱን የዋዜማ ምንጭ ጠቁመዋል፡፡ ከተገዙት አውሮፐላኖች መካከል ሁለቱ አውሮፕላኖች ኢትዮጵያ መግባታቸውንና አንዱ መቅርቡ እንደሚገባ ተረድተናል፡፡

መንግሥት የገዛቸው የአሰሳ ድሮኖች ከዓለም ባንክ በብድርና ድጋፍ በተገኘ ገንዘብ፣ በተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት(ፋኦ) የቴክኒክ ድጋፍ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል፡፡ ይሁን እንጅ ለአሰሳ ድሮኖቹ ግዥ  የወጣውን ገንዘብ መጠን ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ 

ከአሰሳ ድሮኖቹ በተጨማሪ መንግሥት የርጭት ድሮኖችን የመግዛት ዕቅድ እንዳለው የጠቆሙት ኃላፊው፣ የበረሃ አንበጣ በሰብል ልማት ላይ የሚያስከትለውን የምርት መቀነስ ለመከላከል በቴክኖሎጅ የተደገፈ አሰራርን ተግባራዊ ለማድረግ እየሞከረ ነው፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]