Dr Abiy Ahmed and Hailemariam Desalegn- PHOTO-EthioDaily
Dr Abiy Ahmed and Hailemariam Desalegn- PHOTO-EthioDaily

ዋዜማ ራዲዮ- ገዥው ግንባር መዋቅራዊና ፖለቲካዊ ለውጦችን ባያካሂድም የኦሕዴዱ ሊቀመንበር ዶክተር አብይ አሕመድ ወደ ጠቅላይ ሚንስትርነቱ መምጣታቸው በብዙ ወገኖች ዘንድ በተለይም በኦሮሞ ብሄር ተወላጆች ዘንድ የደስታ እና ተስፋ ስሜት ፈጥሯል፡፡ በርግጥ በእሳቸው አመራር ስር ኢሕአዴግ የሚከተለውን አካሄድ ጊዜ ወስደው በጥንቃቄ ማየት የሚፈልጉም ብዙ ናቸው፡፡ የተለያዩ ወገኖች የሚደሰቱበትና ተስፋ የሚያሳድሩበት የየራሳቸው ግልጽ እና ስውር ምክንያት ሊኖራው ይችላል፡፡ ሁሉም አሁን እያሳዩት ያለው ስሜት ግን ለመንግስት መልካም ዜና ነው የሆነለት፡፡

ዶክተር አብይ በፌደራል ደረጃ በቁልፍ ፖለቲካዊ መስሪያ ቤቶች ገና ልምድ ያላገኙ እና ከሞላ ጎደል ለአራት ኪሎ ፖለቲካ ራቅ ያሉ ቢሆኑም በመጠኑ ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያሳየው ኦሕዴድ ሊቀመንበር መሆናቸው፣ የሕወሃትን አንጋፋ መሪዎች የፖለቲካ አስተሳሰብ እንደማይጋሩ መታመኑ እና በዕድሜም ጎልማሳ መሆናቸው ብዙዎችን አስደስቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም በኢሕአዴግ ውስጥ በለውጥ ናፋቂ አመራሮች እና በነባሩ አመራር መካከል የተራዘመ ዴሞክራሲያዊ የሃሳብ ትግል ተደርጎ ለውጥ ናፋቂው ቡድን በማሸነፉ ለሥልጣን የበቁ ሰው አይደሉም፡፡ ይልቁንስ ሕዝባዊ አመጹንና የፖለቲካ ቀውሱን ለማስታገስ ሲባል በተለይ በወለፈንድ ርዕዮተ ዐለም ላይ የተቸከለው የሕወሃት ነባር አመራር በመልካም ፍቃዱ ለሥልጣን እንዳበቃቸው መረሳት የለበትም፡፡

ዶክተር አብይ ከተሰናባቹ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በላይ የገዘፉ ፈተናዎች ነው የሚጠብቋቸው

አንዱ ፈተናቸው “የሽግግር ጠቅላይ ሚንስትር መሆን ይችላሉ? ወይስ የቀውስ ጠቅላይ ሚንስትር?” በሚለው ጥያቄ ዙሪያ የሚሽከረከር ነው፡፡ በርግጥ ይህ ጥያቄ በሥልጣን በሚቆዩበት ጊዜ ልክ እና በኢሕአዴግ የለውጥ ፍላጎት ላይ ይመሰረታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ሀገሪቱ ከገባችበት ቀውስ እንዴት እንደምትወጣ ኢሕአዴግ ገና ፍኖተ ካርታ ማውጣት ስላልቻለ ወይም ስላልፈቀደ ለብዙ ጊዜ የቀውስ ጠቅላይ ሚንስትር ሆነው፣ በብዙ ችግሮች ተተብትበው የመቆየት ዕድላቸው ሰፊ ይመስላል፡፡

በፓርላመንታዊ ሥርዓት ውስጥ ያሉ ጠቅላይ ሚንስትር መሆናቸው እንደተጠበቀ ሆኖ የኢሕአዴግ አመራር ደሞ ቡድናዊ በመሆኑ በግላቸው የፈለጉትን አዲስ ካቢኔ ለማቋቋም በቂ ሥልጣን አይኖራቸውም፡፡ የሥራ ዘመናቸውን የሚጀምሩት በመንግስትና ፓርቲ መካከል ግልጽ መስመር የሚያበጅ እና በብሄር ተዋጽዖ እና ብቃት በሌላቸው በፓርቲ ካድሬዎች የተሞላውን የመንግስት ቢሮክራሲ ዘመናዊ እና በሳይንስ የሚመራ ለማድረግ ሥርዓት ባልተዘረጋበት ሁኔታ ነው፡፡ ሀገሪቱ ከፓርቲ ካድሬ ከተሞላ ካቢኔ ተላቅቃ ለውስብስብ ችግሮቿ የሚመጥን ብቃት እና ዕውቀት ያለው እና በጋራ ሃላፊነት መንፈስ የሚሰራ ሙያተኛ ካቢኔ (technocratic cabinet) ሳይኖራት አንድ ጠቅላይ ሚንስትር የፈለገውን ያህል ቢፍጨረጨር ለውጥ የማምጣት ዕድሉ አናሳ ነው፡፡

የገዥው ግንባር አሰራር አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር የፖሊሲ ማሻሻያ እንዲያመነጩ እና በማያወላ አመራር እንዲያስፈጽሙ የሚያስችላቸው አለመሆኑም ሌላ ተያያዥ መሰናክል ነው የሚሆንባቸው፡፡ በመሠረቱ በኢሕአዴግ አሰራር አንድ ግለሰብ ይቅርና የገዥው ግንባር አባል ድርጅቶችና የመንግስት መዋቅር በሙሉ ለኢሕአዴግ ርዕዮተ ዐለም፣ ፖሊሲዎችና መርሆዎች ሙሉ ተገዥ ናቸው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር እና የግንባሩ ሊቀመንበር የሚሆን ግለሰብ የኢሕአዴግን ቀኖና ሙሉ አስፈጻሚ ነው፡፡

በተለይ ዶክተር አብይ እንደ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ሁሉ የግንባሩ አስኳል ከሆነው ሕወሃት ውጭ የተመረጡት ስለሆኑ ለሩብ ክፍለ ዘመን ጭቆና የመረረውን ሕዝብ ወደ ቃል ኪዳኗ ምድር የሚያደርሱ ሐዋሪያ አድርጎ ማየት በምንም መልኩ የሚያዋጣ አይደለም፡፡ ለሩብ ክፍለ ዘመን የቆየው አወቃቀርና ፖሊሲ ባልተቀየረበት ሁኔታ ብዙዎች የሰነቁት ተስፋ እውን የሚሆነው በተለይ የሕወሃት እና የቀሪዎቹ አባል ድርጅቶች ፍቃደኝነት ሲታከልበት ብቻ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ለአዲሱ ተመራጭ ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሠረታዊ ለውጥ ለማድረግ እንዳልተዘጋጀ ደሞ መግለጫዎቹ ሁሉ ግልጽ እያደረጉ ነው፡፡

በቅርቡ ከኢሕአዴግ አደረጃጀቶች “ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢሕአዴግ ነው!” የሚል ቋንቋ መሰማቱ ዶክተር አብይ ስለሚጠብቃቸው ጥብቅ የቡድን አመራር ፍንጭ የሚሰጥ ነው፡፡ እሳቸው ሊቀመንበር ሆነው ከመመረጣቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የግንባሩ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ “ኢሕአዴግ አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ መስመሩን እንደገና አጠናክሮ ይገፋበታል” ሲል መግለጹም የዚሁ ፈተና አካል ነው፡፡

በገዥው ግንባር በኩል ስናየው ደሞ አዲሱ ተመራጭ በኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች መካከል አፍጥጠውና አግጥጠው የመጡትን የሥልጣን እና ሃብት ክፍፍል ቅሬታዎች ማስታረቅ እና እየላላ የመጣውን የግንባሩን አንድነት የመጠበቅ ፈተና አለባቸው፡፡ ለዚህ ጉዳይ ኢሕአዴግ የመፍትሄ አቅጣጫ ሊያበጅለት ይቅርና ገና በቂ ውይይት እንኳ እንዳላደረገበት መናገር ይቻላል፡፡

በፌደራሉ እና ክልል መንግስታት መካከልም ቢሆን የተዛባ የሥልጣን እና ሃብት ክፍፍል ቅሬታ አለ፡፡ ይሄ ቅሬታ በአማራ እና ኦሮሞ ሕዝብ አመጽም እንደ አንኳር ችግር ተነስቷል፡፡ እናም ለቅሬታው ፖለቲካዊና ሕገ መንግስታዊ ምላሾች እንዲያገኝ ሕዝቡ ከአዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ብቁ አመራር ይጠብቃል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ይሄን ማድረግ ስለመቻላቸው ወደፊት የሚታይ ሆኖ ብዙ መሰናክሎች እንደሚጠብቋቸው ግን ግልጽ ነው፡፡

በድርጅት ደረጃ የኢሕአዴግን የማዋሃድ የቤት ስራም ከዶክተር አብይ ፊት የተደቀነ መሆኑ ሌላው ድርጅታዊ ፈተና ነው፡፡ ኢሕአዴግን ወደ አንድ ኅብረ ብሄራዊ ፓርቲ የማሸጋገር አጀንዳ በመጭው ክረምት በግንባሩ ጠቅላላ ጉባዔ ውይይት እንደሚደረግበት ስለተነገረ ለዚያ ዝግጅት በማድረግረገድ፤ ውህደቱ ድጋፍ ካገኘ ደሞ ለውጡ የሚቀሰቅሳቸውን የርዕዮተ ዐለም፣ የአወቃቀር እና የጥቅም ግጭቶች የማስታረቅ ከባድ ፈተና ፊት ለፊታቸው ተደቅኗል፡፡

ባጠቃላይ ከድርጅታዊ ጀርባቸው እና ፖለቲካ ልምዳቸው አንጻር በአስቸጋሪ ቀውስ ውስጥ ያለች ሀገር የሚመሩ በመሆናቸው ዐይኖች ሁሉ እሳቸው ላይ እንደሚያርፉ ጥርጥር የለውም፡፡ ለዚህ ሁሉ ውስብስብ ችግር ምን ዐይነት አመራር እነደሚሰጡ በመጭዎቹ ወራት ፍንጭ መታየቱ አይቀርም፡፡ ችግሩ ቋፍ ላይ ያለው ሕዝብ ምን ያህል መታገስ ይችላል? የሚለው ነው፡፡ [በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ] 

https://youtu.be/E37hFPGLYLI