Parliament2

የሁሉም ህገመንግስታዊ ተቋማት ቁንጮ የሆነው የኢትዮጵያ የህግ አውጭው ምክር ቤት የተቋማዊ ድክመት ተምሳሌት እንደሆነ ለአምስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን ደርሷል፡፡ ህግ አውጭው ምክር ቤት ሆን ተብሎ በአሳፋሪ ደረጃ ላይ እንዲገኝ ያደረጉት ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ እና በተለይም እናት ድርጅታቸው ኢህአዴግ መሆናቸው እሙን ነው፡፡ ጠንካራ ፓርላማ ለግላቸውም ሆነ ለፓርቲያቸው ጠቅላይ ስልጣን ምን ያህል አስጊ እንደሚሆን ቀድመው አውቀውት ነበር፡፡

(የቻላቸው ታደሰ ዘገባ የተብራራ መረጃ ይዟል እዚህ ያድምጡት)

የዘንድሮው ፓርላማ ለአምስተኛ ዙር ስራውን የጀመረው በታሪካዊ ወቅት ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በመጀመሪያ ከአቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋቀረ ፓርላማ ነው፡፡ በተጨማሪም ገዥው ድርጅት ለመጀመሪያ ጊዜ የፓርላማውን ብቻ ሳይሆን የሁሉንም ክልሎች ምክር ቤቶች መቀመጫዎች ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሯል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ተደጋጋማ በምትነሳው ሀገር ከአምስት ሚሊዮን ህዝብ በላይ የረሃብ አደጋ አንዣቦበታል፡፡ በቅርቡ እንደተሰማው ደግሞ ዓለም ዓቀፉ የገንዘብ ድርጅት አይ.ኤም.ኤፍ የሀገሪቱ የውጭ ዕዳ ለታዳጊ ሀገሮች ካስቀመጠው ገደብ በአስር በመቶ አልፎ መገኘቱን በገለፀበት ማግስት የተቋቋመ ፓርላማ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል፡፡

 

በመጀመሪያ ደረጃ የሀገራችን ፓርላማ አንዱ ዋነኛ ተልዕኮ ስራ አስፈፃሚውን መቆጣጠር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በእንግሊዝኛው “parliamentary oversight” ተብሎ የሚታወቀው የህግ ውጭው አካል ሚና መሆኑ ነው፡፡ የቁጥጥር ተልዕኮውን ለመወጣት የሚጠቀምባቸው ዋነኛ ምሰሶዎቹ ደግሞ መንግስታዊ ተቋማትን የሚቆጣጠሩት የራሱ ቋሚ ኮሚቴዎች ናቸው፡፡ ትናንት ደግሞ ከነባር ቋሚ ኮሚቴዎቹ በተጨማሪ አዲስ የከፍተኛ ትምህርት፣ የመንግስት ልማት ድርጅቶች ቋሚ ኮሚቴዎችንና የመከላከያና ደህንነት ልዩ ቋሚ ኮሚቴ ማቋቋሙን አስታውቋል፡፡
አብዛኛዎቹ ቋሚ ኮሚቴዎች ስለሚቆጣጠሯቸው መንግስታዊ ተቋማት ብሎም በጥቅሉ ስለ መንግስት ህጎችና አሰራሮች ያላቸው ግንዛቤ እጅጉን አናሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በየወረዳው ለፓርላማ ዕጩ አድርጎ የሚያቀርባቸው አባሎቹ ትምህርት ዝግጅታቸው ዝቅተኛ መሆኑን ስናይ ነው፡፡ በየዘርፉ የሰለጠነ በርካታ ባለሙያ ባለባት ሀገር የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴዎች በገለልተኛ አማካሪ ባለሙያዎች እንኳ እንዲታገዙ አይደረግም፡፡ ሚንስትሮች ሪፖርት ከማቅረባቸው በፊት ግዙፍ የስድስት ወር ሪፖርቶቻቸውን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች የሚልኩት ጥቂት ቀናት ሲቀሩ ከመሆኑም በላይ ጥራዞቹ በጣም ዝርዝር ቴክኒካዊ ጉዳዮችን ያካተቱ ስለሚሆኑ ቋሚ ኮሚቴዎቹ ለመረዳት ሲከብዳቸው ይስተዋላል፡፡
ስለሆነም ሚንስትሮች የሚመሯቸው መስሪያ ቤቶች በርካታ የሀገር ሃብት አባክነው ወይም ሌሎች ግዙፍ ግድፈቶች እያሉባቸው ለፓርላማው የስድስት ወራት አፈፃፀም ሪፖርት ሲያቀርቡ ፓርላማው ሲሞግታቸው አይታይም፡፡ ሚንስትሮች እየተጨበጨበላቸው ወደ ፓርላማው መድረክ ገብተው እየተጨበጨበላቸው ወደ ስራቸው ሲመለሱ ማየት የተለመደ ሆኗል፡፡

በእርግጥ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፈ ጉባዔ አባዱላ አመራር አልፎ አልፎ የፓርላማ አባላት ከተለመደው ውጭ አንዳንድ ሚንስትሮችን ሲያፋጥጡ ታይቷል፡፡ የፓርላማውን ውስጣዊ አሰራር ለሚያውቅ ግን እንዲህ ዓይነቱ ጊዚያዊ ሁኔታ በገዥው ግንባር ውስጥ የሚቀያየረውን የግለሰቦች የሃይል አሰላለፍ ሁኔታ ያንፀባርቅ እንደሆን እንጂ ፓርላማው ጥርስ እያወጣ እንዳልሆነ መረዳት አይከብደውም፡፡

ኢህአዴግ በተፈጥሮው ህዝባዊ አመኔታ ያላቸውና በግልፅነትና ተጠያቂነት መርሆዎች የሚመሩ ጠንካራ ሀገራዊ ተቋማትን መፍጠር አልፈለገም፤ ቢፈልግም እንኳን በአቅም ውስንነት ሳቢያ አልቻለም፡፡ ስለሆነም በየአምስት ዓመቱ ስልጣኑን ባደሰ ቁጥር የሚንስቴር መስሪያ ቤቶችን አወቃቀር ሲቀያይር ይስተዋላል፡፡ ይህም ሃያ አራት ዓመታት ሙሉ መርጋት ያልቻለ መንግስት ለመሆኑ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡
ኢህአዴግ-መራሹ መንግስት የህዝብ ተወካዮች ሚንስቴርን ብቻ ሳይሆን የፌደሬሽን ምክር ቤትንም አዳክሞታል፡፡ በተለይ የፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴርን ካቋቋመ ወዲህ፡፡ ሆን ተብሎም በፌደሬሽን ምክር ቤትና እና በፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር መካከል የሃላፊነት መደራረብና የጥቅም ግጭት እንዲኖር ተደርጓል፡፡
በህገመንግስቱ መሰረት የፌደሬሽን ምክር ቤት የክልሎችን የበጀት ድጎማ ቀመርና የገቢ ክፍፍል እንደሚወስን ይታወቃል፡፡ በመርህ ደረጃ ሲታይ እንዲህ ዓይነቱ አንገብጋቢ ጉዳይ በፌደራል መንግስት ስርዓት ውስጥ ብዙ ክርክርና ንትርክን የሚያስከትል እንደሆነ እሙን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን አንድ ገዥ ግንባር ሁሉንም ክልሎች ጠርንፎ በመያዝ አቅመ ቢስ ስላደረጋቸው በጉዳዩ ላይ በቂ ክርክር ሲካሄድ አይሰማም፡፡ ያም ሆኖ የዘጠኙም ክልሎች ፕሬዝዳንቶች ሁሌም በፌደሬሽን ምክር ቤት የፊት ወንበር ላይ ተኮልኩለው የሚታዩበት ዋናው ምክንያት አንገብጋቢውን አጀንዳ ራሳቸው በቅርብ መከታተል ስለሚፈልጉ ነው፡፡

ፌደሬሽን ምክር ቤት በፌደራል መንግስቱ ተቋማትና በክልሎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንም እንዲፈታ በህገመንግስቱ ስልጣን ተሰቶታል፡፡ ሆኖም ሆን ተብሎ እንዲዳከም የተደረገው ምክር ለዚህ ሃላፊነቱ የሚሆን የህግ ማዕቀፍ ሳይኖረው መቆየቱ የፓርላሜንታዊ ስርዓቱ እንቆቅልሽ ሆኖ ኖሯል፡፡ አስገራሚው ነገር ምክር ቤቱ ይህንኑ የህግ ማዕቀፍ ለማውጣት የወሰነው ገና በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ ነበር፡፡ እስካሁንም የበይነ-ክልሎች ጉዳዮች ሲስተናገዱ የኖሩት በህገመንግስታው መዋቅር ሳይሆን በኢመደበኛው የፓርቲ መዋቅር መሆኑን እንረዳለን፡፡ ከጅምሩም መንግስት የፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴርን ሲያቋቁም ዓላማው ራስን በራስ የማስተዳደር ስልጣን ያላቸውን ክልሎችን ስልጣን ከጀርባ ለመሸርሸር ጭምር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

በህወሃቱ አባይ ፀሃይ መሰረቱ በደንብ ለተጣለው የፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር ሰሞኑን ደግሞ ባላንጣው የሆነውን የፌደሬሽን ምክር ቤት በአፈ ጉባዔነት ሲመሩ የነበሩት የብአዴኑ ካሳ ተክለ ብርሃን መሾማቸው ነገሩን ምፀት ያደረገዋል፡፡ ሆኖም ሰውዬውም ተቋሙን የበለጠ በማጠናከር የመንግስት ቀኝ እጅ ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያደርጉት ይጠበቃል፡፡

በጠቅላላው ያለፉት ሃያ ዓመታት የሚያሳዩን ፓርላሜንታዊ ስርዓትና ህገመንግስታዊነት በእጅጉ እንዲቀጭጩ መደረጉን ነው፡፡ ሁሌም በሀገሪቱ የዕለት ተዕለት ህይወት ስራ አስፈፃሚው መንግስትና ገዥው ድርጅት ገናና ሆነው ይታያሉ፡፡ መንግስት ከህግ ማመንጨት ጀምሮ እስከ መፈፀም ድረስ ያለ ተቆጣጣሪ ልጓም የፈለገውን ሲሰራ ኖሯል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ ፓርላማውም ወደፊት በታሪክ መዝገብ ውስጥ ሊሰፍር የሚችል ሚና ስለመጫወት አለመጫወቱ ፍርዱን ለህዝቡ መተው ሳይሻል አይቀርም፡፡