ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በውስብስብ ፈተናዎች ውስጥ በመውደቅና በመነሳት መካክል መሆኑ ይታወቃል። ድርጅቱ ተስፋ የለውም የሚሉ አንዳሉ ሁሉ ድርጅቱ ወደ አዲስ ቅርፅና አደረጃጀት እያመራ ነው የሚሉም አሉ። የዋዜማው ቻላቸው ታደሰ ድርጅቱ እየያዘ ያለውን አዲስ አሰላለፍና ቀዳዳ ያመላከተበትን ዘገባ አንብቡት

Photo-FILE

የድሮው ኢሕአዴግ የለም ላይመለስ ከስሟል አሁን ያለነው በአዲስ ድህረ ኢሕአዴግ ወቅት ላይ ነው የሚል አስተያት ያላቸው የፖለቲካ ጉዳይ አዋቂዎች አሉ። በእርግጥ ያለነው ድህረ ኢሕአዴግ ወቅት ላይ ነውን?

አሁን የኢሕአዴግ አምባገነናዊ ባህል እንዳለ ቢሆንም፣ ድርጅታዊ መዋቅሩ ግን መዳከሙ በግልጽ ይታያል፡፡ መንግሥትን የሚመራው ራሱ ኢሕአዴግ ነው ለማለትም የማይቻልበት ደረጃ ላይ ተደርሷል፡፡ ውስጣዊ በይነ-ድርጅታዊ ቅራኔውም ወደ አዲስ አሳሳቢ ደረጃ ተሸጋግሯል፡፡ በሚመራው መንግሥት ውስጥም የቅድመ ተከተል መደበላለቅ ይስተዋላል፡፡ ችግር ፈች አዳዲስ የፖለቲካ እና ፖሊሲ መፍትሄዎች ነጥፈውበታል፡፡ ቡድናዊ አመራር በሚፈልግበት በዚህ ፈታኝ ወቅት፣ በሊቀመንበሩ መዳፍ ስር ብቻ እየወደቀ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አምና የወረሷቸው የውስጠ ኢሕአዴግ ቅራኔዎችም ተባባሱ እንጅ ፈጽሞ አልሰከኑም፡፡ ባጭሩ ግንባሩ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ሊያስጀመር ይቅርና፣ የራሱ ውስጣዊ ጣጣ ለሀገሪቱ ህልውና፣ አንድነትና ሰላም ስጋት እየሆነ መጥቷል፡፡
ምናልባት ግንባሩ ከፈረሰ፣ በድህረ-ኢሕአዴግ ዘመን ምን ዐይነት አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ ሊወለድ ይችላል? በፌደሬሽኑ እና ፌደራላዊ ሥርዓቱ ላይስ ምን አንድምታ ይኖረዋል?

የመፍረስ ምክንያቶች
ለኢሕአዴግ መፍረስ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከውስጥ ርዕዮተ ዐለማዊ ልዩነት እና ድርጅታዊ ቅራኔዎችን፣ ከድርጅት ደሞ ሕወሃትንና ደኢሕዴንን ውስጥ ያሉ በተለይ የክልልነት ጥያቄ ያነሱ ብሄርተኞችን ሚና መጥቀስ ይቻላል፡፡ ትልቁ ስጋትም ከውስጥ የሚመጣው ነው፡፡ ከውስጡ ከሚቆረቆሩለት ይልቅ የተሰላቹበት እየበዙ መጥተዋል፡፡


ለኢሕአዴግ መፍረስ አንዳንድ ወገኖች እንደ ምክንያት የሚያነሱት ርዕዮተ ዐለምን ነው፡፡ በኢሕዴግ ደረጃ ግን እስካሁን ይህ ነው የሚባል የርዕዮተ ዐለም ለውጥ አልተደረገም፡፡ ኦዴፓ እና አዴፓ ግን በተናጥል መግልጫዎቻቸው፣ አብዮታዊ ዲሞክራሲን ለማጠልሸት ሞክረዋል፡፡

ሕወሃት ባንጻሩ ጥብቅና ቆሞለታል፡፡ ያም ሆኖ ከመግለጫ ያለፈ፣ ኦዴፓም ሆነ አዴፓ መሬት የቆነጠጠ የርዕዮተ ዐለም ለውጥን በድርጅት ፕሮግራማቸው አላካተቱም፡፡ ሁለቱም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ እንደሚፈልጉ ፍንጭ ሰጥተዋል፡፡ መግለጫቸውን እና ንግግራቸውን እንደ ርዕዮተ ዐለም ለውጥ መውሰድ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በተለይ ሕዝበኝነት ከተጋባባቸው ወዲህ አቋማቸው እየዋዠቀ መምጣታቸውም ይህንኑ ያጠናክራል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደሞ ኦሕዴድ/ኦዴፓ የብሄር ፖለቲካን ከማናናቅ እና ሕገ መንግሥትታዊ ማሻሻያ ከጠየቀበት አቋሙ አፈግፍጓል፡፡ አዴፓም ቢሆን አሁን ከገጠመው የአመራር መዳከም አንጻር፣ በቀደመ አቋሙ ምን ያህል ይገፋበታል የሚለው አጠራጣሪ ነው፡፡


እንደ ግንባርም ሆነ አባል ድርጅቶች በተናጥል ለምን ግልጽ የርዕዮተ ዐለም ለውጥ እንዳላደረጉ መላ ምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፤ አንደኛው፣ አባል ድርጅቶች በተናጥልም ሆነ እንደ ኢሕአዴግ የርዕዮተ ዐለም ለውጥ የሥልጣን መሠረታችን ይሸረሽርብናል ወይስ ያጠናክርልናል ብለው ስለሚጨነቁ ይሆናል የሚለው መላ ምት ነው፡፡ ሌላኛው መላ ምት አንዱ የሌላኛውን ዕቅድ ስለማያውቅ፣ አንዳው ቀድመው የርዕዮተ ዐለም ለውጥን በይፋ በፕሮግራማቸው ቢያካትቱ፣ በግንባሩ ውስጥ ቦታቸውን እና የሃይል ሚዛናቸውን እንዳያሳጣቸው መስጋታቸው እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ሦስተኛው፣ ምናልባት ገና አዳዲስ የፖለቲካ አሰላለፎችን እያጤኑ ሊሆን ይችላል፡፡

ሌሎች ከግንባሩ እና ከውጭ ያሉ ብሄርተኛ ሃይሎችም ሕገ መንግሥቱ እንደወረደ በተሟላ ሁኔታ ይተግበር፣ ሕብረ ብሄራዊ ፌደራሊዝምም ይስፈን ባይ ናቸው፡፡ “ፌደራሊስት” እና “አሃዳዊ”የሚል የጎራ ክፍፍል በማምጣት፣ ኢሕአዴግ ሊያመጣው ይችላል ባሉት የርዕዮተ ዐለም ለውጥ ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እየታተሩ ነው፡፡ “አሃዳዊ” የሚለው ፍረጃ፣ ከኢሕአዴግ ውስጥ አዴፓን፣ ከውጭ ደሞ እንደ ኢዜማ ያሉ ፓርቲዎችን አንገት ለማስደፋት መሆኑም ግልጽ ነው፡፡


ባጠቃላይ ከማሻሻያ ጠያቂዎች ይልቅ፣ “ፌደራሊስት” የሚል ቅጥያ ለራሳቸው የደረቡት ሃይሎች ድምጽ ነው ጎልቶ የሚሰማው፡፡ ኢሕአዴግን የርዕዮተ ዐለም ልዩነት ያፈርሰዋል የሚለው መከራከሪያም ውሃ እምብዛም አሳማኝ የሚሆን አይመስልም፡፡ ከርዕዮተ ዐለም ፍትጊያ ይልቅ ጎልቶ የሚታየው፣ የሥልጣን ሽኩቻ እና በተገኘው ክፍተት የራስን ብሄር ጥቅም የማስጠበቅ አካሄድ ነው፡፡


በይነ ድርጅታዊ ቅራኔ ግን ኢሕአዴግን የማፍረስ አቅም ያለው እየሆነ ነው፡፡ ቅራኔው ብዙ መነሻዎች ይኖሩታል፡፡ በተለይ የሕወሃት እና አዴፓ ቅራኔ በሚመሯቸው ክልሎች መካከልም ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችል ሆኗል፡፡ በተለይ ከሕወሃት ድርጅታዊ ግትርነት አንጻር ቅራኔውን ያጦዘው፣ ላጭር ጊዜ ፖለቲካዊ ግብ ነው ብሎ ማሰብ ያስቸግራል፡፡ ከአዴፓ ጋር አብሮ ላለመስራት ማንገራገሩም፣ እንደ ተጎራባች ክልል በጋራ ጉዳዮች ላይ አለመነጋገር ወይም በኢሕአዴግ መድረክ መስተጋብሩን ማቆምን ያጠቃልላል፡፡

ዐቢይ ግን በቅርቡ መግለጫቸው ፍጥጫውን በፖለቲካ የሚያጋጥም ነው በማለት ሊያቃልሉት ነው የሞከሩት፡፡ በርካታ የፖለቲካ ታዛቢዎችም ሆኑ ራሳቸው ጠበኞቹ ግን እንደዚያ አቃለው እንደማያዩት ግልጽ ነው፡፡ ምናልባት ዐቢይ ማቃለል የመረጡት፣ ችግሩን እስካሁን ለመፍታት ለምን አልሞከሩም የሚል ጥያቄ እንዳይነሳባቸው ለመከላከል እንደሆነ አንድ ግምት መያዝ ይችላል፡፡ ምክንያቱም ፍጥጫውን ማርገብ እንደ ጠቅላይ ሚንስትርነታቸው እና እንደ ግንባሩ ሊቀመንበርነታቸው ድርብ ሃላፊነት ነው ያለባቸው፡፡ በርግጥ ችግሩን ለመፍታት መድረክ እንደሚዘጋጅ በደፈናው ጠቁመዋል፡፡


እዚህ ላይ ግን ሦስት መሰናክሎች ጎልተው ይወጣሉ፤ አንደኛው፣ የማስታረቂያው መድረክ ከሚገባው በላይ መዘግየቱ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ ኢሕአዴግ ግንባሩን ዐቀፍ የሆኑ የጋራ ችግሮች ላይ እንጅ፣ የሁለት አባል ድርጅቶቹን ቅራኔ ወይም ጠብ የሚፈታበት ተቋማዊ አሰራርና ልምድ የለውም፡፡ ካሁን በፊት ቅራኔ ተነሳ ከተባለም ባንድ ድርጅት (ማለትም በሕወሃት) ውስጥ ብቻ የተወሰነ ስለነበር፣ ኢሕአዴግ እንደ ግንባር ጉልህ ሚና አልነበረውም፡፡ ሦስተኛ፣ መድረኩ ቢዘጋጅ እንኳ የእሳቸውንም ሆነ የግንባሩን አስታራቂነት ሚና፣ ሕወሃት ሊቀበለው ይችላል ወይ? የሚለው አጠራጣሪ ይሆናል፡፡ የዐቢይ መንግሥት ትግራይ ውስጥ እንደሌለ መቸም የአደባባይ ሚስጢር ከሆነ ከራርሟል፡፡ በአራተኛ ደረጃም፣ የዐቢይ ድርጅት ኦሕዴድ/ኦዴፓም የሁለቱን ድርጅቶች ዕርቅ የመፈለጉ አጠራጣሪነትም ከግምት መግባት ያለበት ነው፡፡


ሕወሃት የግንባሩን አንድነት የሚፈታተነው እንግዲህ ራሱን በማግለል ነው የሚሆነው፡፡ በርግጥ ከግንባሩ መውጣቱ ቢጎዳው እንጅ አይጠቅመውም፡፡ ሌላ አዋጭ የፖለቲካ አሰላለፍ ለመመስረት ደሞ ቢያንስ፣ መልካ ምድራዊ ሁኔታዎች ምቹ አይሆኑለትም፡፡ እገነጠላለሁ የሚለው ካርዱም፣ ከኢሕአዴግ ውስጥ ሊያስደነግጣቸው የሚችሉ ሃይሎች እየጠፉ ነው፡፡


የደኢሕዴን ብሄርተኞችም በክልልነት ጥያቄያቸው ከገፉበት፣ በኢሕአዴግ ዕጣ ፋንታ እና በመጻዒ የፖለቲካ አሰላለፎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደራቸው አይቀርም፡፡ በተለይ ሲዳማዎች የራሳቸውን ክልል መስርተው ከወጡ፣ የደኢሕዴን ህልውና በቀጭን ገመድ ላይ መንጠልጠሉ የማይቀር ነው፡፡ ሌሎች የክልልነት ጥያቄዎችንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በእጅ አዙር አፍኖ ማቆየት አስቸጋሪ ነው፡፡ ከእንግዲህ የደኢሕዴን ህልውና በቀናት ብቻ የሚሰላ እየሆነ ነው፡፡


ኦህዴድ/ኦዴፓም ቢሆን ተከድኖ ይብሰል በሚል ይዞት እንጅ፣ ኦነግና ሌሎች አክራሪዎች መዋቅሩን ከስሩ ሲሸረሸሩት እንደቆዩ የአደባባይ ሚስጢር ነው፡፡ የጸጥታ መዋቅር ማሻሻያ ባለመተግበሩ፣ ሌሎች ክልሎችም በአማራ ክልል ላይ የደረሰው የባለሥልጣናት ግድያ እንደማያጋጥማቸው ዋስትና የለም፡፡ መዋቅራዊ የጸጥታና ፖለቲካዊ ችግሮች እንደሆኑ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይነት ያላቸው ናቸው፡፡ ከትግራይ ውጭ የድርጅት እና መንግሥት መዋቅር ተዳክሟል፡፡ መጠነ ሰፊ የጸጥታ ሃይል መፈረካከስን ለማስቀረት ምን ርምጃዎች ይወሰድ? የሚል የመንግሥት ተነሳሽነት አይታይም፡፡ ዐቢይ በዚህ አያያዛቸው፣ አዲስ አበባን ብቻ የሚያስተዳድሩ ጠቅላይ ሚንስትር እንዳይሆኑ ስጋት አለ፡፡
ከውጭ ደሞ ኦነግን እና ሌሎች የኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞችን ኢሕአዴግ እንዲፈርስ ግፊት ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡


ገፊ ሃይሎች እና አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ
መቸም የዐቢይ የኢሕአዴግ የውህደት አጀንዳ እንዳሰቡት ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ በቅርቡ በሰጡት መግለጫም አንዳንድ ጉዳዮች በቅድሚያ እንዲስተካሉ ስለተጠየቀ መዘግየቱን ገልጸዋል፡፡ ችግሩ ግን ድርጅቱ የትኛውንም የጋራ ጉዳይ ማስተካከል የሚችልበት ቁመና ላይ አለመገኘቱ ነው፡፡ ሰውዬው እስካሁን ከተከተሉት አዝማሚያ ተነስተን ብናይ፣ ኢሕአዴግን አሁን ባለው ቅርጹ ወይም ይዘቱ የሀገራዊ ለውጥ ሞተር ሊያደርጉት የፈለጉ አይመስልም፡፡ እንዴት ያለ አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ ሊፈጥሩ አስበው ይሆን? የሚለው ግን ገና ግልጽ አይደለም፡፡


በርግጥ አሁን ባለው ፓርላማ ሕወሃት ቢወጣም፣ ጠቅላይ ሚንስትሩ በቀሪው ኢሕአዴግ መንግሥትነቱን ይዘው መቀጠል ይችላሉ፡፡ ካስፈለጋቸውም በሕወሃት ፋንታ በቁጥር ተመጣጣኙን ሶሕዴፓን አባል ለማድረግ የሚቸግራቸው አይሆንም፡፡ ምናልባት ከውጭ ፖሊስ አንጻር ግን ያለ ሕወሃት እንደ ዐይን ብሌናቸው የሚሳሱለት የኤርትራ ወዳጅነት ለማስቀጠል መቸገራቸው አይቀሬ ይሆናል፡፡


የኢሕአዴግ መዋቅር ከመንግሥት መዋቅር ጋር የተሳሰረ በመሆኑ፣ እንደ ግንባር የሚፈርስ ከሆነ ፌደሬሽኑም ሆነ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የመበታተን አደጋ ሊገጥመው ይችላል፡፡ ዐቢይ ግን ቢያንስ እስከ ቀጣዩ ምርጫ ድረስ ግንባሩን ጠጋግነው ማቆየት የፈለጉ ነው የሚመስለው፡፡ በዚህም ትልቁ ስጋትን ሊያስወግዱት ይችሉ ይሆናል፡፡


ከኢሕአዴግ ውጭ በለውጥ መራሹ ሃይል ዙሪያ ያሉ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች የየራሳቸውን ግፊት እያደረጉ እንደሆነ ግምት ያላቸው ወገኖች አሉ፡፡ ግንባር ቀደሞቹም ግፊት አድራጊዎች ኦነግ፣ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞች እና አዜማ እንደሆኑ ይታመናል፡፡ የግፊታቸው ጥልቀት እና ግብ ግን ሊለያይ ይችላል፡፡ አንዳንዶቹ ኢሕአዴግ ውስጥ ታቅፈው፣ የድርጅቱን መዋቅር ሊጠቀሙበት ይፈልጉ ይሆናል፡፡ ሌሎች ደሞ በግንባሩ መቃብር ላይ ሌላ የአሰላለፍ ስሌት ይኖራቸዋል፡፡ ዞሮ ዞሮ ኢሕአዴግ ውስጣዊ ችግሩን ካልፈታ፣ እነዚህ ሃይሎች በወደፊቱ አሰላለፍ ላይ ሚናቸው ሊጎለበት ይችላል፡፡


ሃች አምና ሸማቂ እና ሰላማዊ ተቃዋሚ ድርጅቶች ከውጭ ሀገር ሲገቡ፣ በለውጥ ሂደቱ የዘመናችን ኢሕአፓዎች እና መኢሶኖች እነማን ይሆኑ የሚል ጥያቄ ዋዜማ ራዲዮ አንስታ ነበር፡፡ አሁን የኦሮሞና ትግራይ ፌደራሊስት ነን ባይ ብሄርተኞች፣ አዜማን በመኢሶን ቦታ እንዳስቀመጡት መታዘብ ይቻላል፡፡ በዐቢይ መንግሥት ላይ ጉልህ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሆነም ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል፣ ከሕወሃት ጋር ወደመቀራረብ ያዘነበሉት፡፡ ለጋው አዜማ፣ ጉልህ ተጽዕኖ ለማድረግ የሚያበቃ ድርጅታዊ መዋቅር እና ፖለቲካዊ ጡንቻ አለው ወይ? የዐቢይ ኦዴፓስ ከአዜማ ጋር የሚጣጣሙ መርሆዎችን ሊከተል ይችላል ወይ? ጉድኝት ቢኖርስ ለዘላቂ ግብ ነው ወይስ ለታክቲክ ነው? የሚሉትን ጉዳዮች ግን ጊዜ ሰጥቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡


ያም ሆኖ አክራሪዎቹ አሁን አሁን በለውጥ ሃይሉ ላይ የሰላ ትችታቸውን እያቀዛቀዙ መጥተዋል፡፡ ኦነግም አባሎቼ ታሰሩብኝ ከሚለው ክሱ ባለፈ፣ ትችቱን ቀንሷል፡፡ ዐቢይ ሲዳማ ላይ ያልተጠበቀ ሃይል መጠቀማቸው እና ክልሉንም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ማድረጋቸው ከኦሮሞ አክራሪ ብሄርተኞች ነቀፋ እንደሚያስከትልባቸው ተጠብቆ የነበረ ቢሆንም፣ የተፈራው ግን ሳይሆን ቀርቷል፡፡ ይህ የሆነው እንግዲህ ለብሄርተኞቹ ከሀገራዊ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር እና መብት ይልቅ፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ውስጣዊ አንድነት ስለበለጠባቸው ሊሆን ይችላል፡፡


ቀጥሎስ?
አሁን ባለው ሁኔታ ከየትኛውም የግንባሩ አባል ድርጅት፣ በአክራሪ ብሄርተኞች ላይ ሊሰለጥኑ የሚችሉ ዲሞክራቲክ ሃይሎች ያሉ አይመስልም፡፡ እናም በፖለቲካ ምህዳሩ ወደፊትም እየገነኑ የሚሄዱት አክራሪ ብሄርተኞች እንዳይሆኑ ያሰጋል፡፡ ላለፉት ሦስት አስርት ዐመታት ፌደሬሽኑን አንድ አድርጎ የያዘው ሕገ መንግሥታዊነት መዳበሩ ሳይሆን፣ የኢሕአዴግ ወጥ መዋቅር ነበር ማለት ይቻላል፡፡ አሁን ያ መዋቅር ፈተና ሲገጥመው፣ የፌደሬሽኑ ዕጣ ፋንታ መበታተን ወይም የርስ በርስ ግጭት እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ ለብሄር ድርጅቶች እና ለብሄር ፖለቲካ ሲባል፣ የሀገሪቱ አንድነት፣ ሰላምና የዲሞክራሲያዊ ለውጥ ተስፋ መስዕዋት ሆኖ ቀርቧል ማለት ይቻላል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]