Bereketዋዜማ ራዲዮ- የምስራቅ ጎጃም ዞን መቀመጫ በሆነችው የደብረ ማርቆስ ከተማ ሐምሌ 4 ቀን በተቀሰቀሰ ታቀውሞ በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱና ከተማዋ እስከምሽት ድረስ  ተኩስ ሲሰማባት መዋሏን ዋዜማ ከከተማዋ ነዋሪዎችና አመራሮች ለማረጋገጥ ችላለች፡፡
ከተማዋ  በተኩስ ስትናጥ ብትውልም ባልተለመደ መልኩ የጸጥታ አካላት በህዝብ ላይ ጉዳት ላለማድረስ ኃላፊነታታቸውን እየተወጡ መሆናቸውን የዋዜማ ምንጮች ይናገራሉ። ለክፉ የማይሰጥ የመቁሰል ጉዳይ የደረሰባቸው መኖራቸው ተነግሯል።

የገዢው ፓርቲ ነባር ታጋዮች አቶ በረከት ስምዖንና ሌላ የፓርቲው ሹም በሀገሪቱ የተጀመረውን የፖለቲካ ለውጥ ለመቀልበስ በክልሉ እየተንቀሳቀሱና እያሴሩ ነው የሚል መረጃ መናፈሱን ተከትሎ የአካባቢው ማህበረሰብ አመራሮቹ አርፈውበታል ወደ ተባለው ጎዛመን ሆቴል ለተቃውሞ ማምራቱን የክልሉ አመራሮች ያስረዳሉ።
ምንም እንኳ ሁለቱ ሹማምንት ከቅዳሜ ጀምሮ ከባህር ዳር ወደ ደብረ ማርቆስ ሳይገቡ እንዳልቀረ በከተማዋ ሲናፈስ የቆየ ቢሆንም አንዳንድ ወጣቶች አቶ በረከትና ሌሎች በስም ካልተጠቀሱ ግለሰቦች ጋር በመሆን በጎዛመን ሆቴል ዛሬ ጠዋት መታየታቸው መረጃ እንደደረሳቸውና ወዳ ረፉበት ሆቴል በማቅናት ለመያዝ ሞክረዋል ተብሏል፡፡ ነገር ግን የሆቴሉ የጥበቃ ስራተኞች ወጣቶችን እንዳይገቡ መከልከላቸውን ተከትሎ በተነሳ ግብግብ ሆቴሉ በድንጋይ  ጉዳት ሊድረስበት መቻሉን ዋዜማ ለማወቅ ችላለች፡፡

ከብር ሸለቆ መምጣታቸው የተነገረ የመከላከያ ሰራዊት አባላት አመሻሹን ከተማዋን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠራቸውን ዘግይቶ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ግጭቱ እንዲባባስ ምክንያት የሆነው የትራፊክ ፖሊሶች የባጃጅ አሽከርካሪዎችን ህጋዊ ያልሆነ ስንደቅ አላማ አውለብልባችኋል በሚል ቅጣት በመጣላቸው የተቆጡ ወጣቶች ከፀጥታ አካላት ጋር ግብ ግብ ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ መሆኑን እማኞች ነግረውናል።
የዛሬው ግጭቱት ከጠዋቱ 5፡00 ስዓት አካባቢ የጀመረ ሲሆን እስከ ምሽት 12፡00 ሰዓት ድረስ የቀጠለ ሲሆን ፖሊስ  ጥይት ወደ ሰማይ በመተኮስ ወጣቶችን ለመበተን እየሞከረ እንደነበር ለማወቕ ተችሏል፡፡ ነገር ግን ወጣቶቹ ምንም የማፈግፈግ ባህሪ ከማሳየት ይልቅ ቁጣቸው ተጋግሎ መዋሉም ተነገሯል፡፡

የአቶ በረከት ናቸው የተባሉ የግል ሰነዶች ተገኝቷል ተበሏል፡፡ ይሁን እንጂ ዋዜማ በወጣቶቹ እጅ ገብቷል የተባለውን የባለስልጣኑ የግል ሰነድን በተመለከት ከከተማዋ ፖሊስ ለማረጋገጥ ዋዜማ ያደረገችው ሙከራ አልተሳካም፡፡
ነገር ግን አንድ ስሜ አይጠቀስ ያሉ የዞኑ አመራር በሆቴሉ ላይና በሌሎች መሰረተ ልማት ላይ መጠነኛ ጉዳት ቢደርስም እሳቸው እስከሚያወቁበት (ቢያንስ ከቀኑ 11፡00 ስዓት) ድረስ በከተማዋ ነዋሪና በጸጥታ ኃይሎች ጨምሮ በሰው ህይወት ላይ ምንም የከፋ ጉዳት እንዳልደረስ አረጋግጠዋል፡፡

ወደ ከተማዋ ገብተዋል ስለተባሉት ባለስልጣናት የተሰራጨውን መረጃ ትክክለኝነት በተመለከት ዋዜማ ያነጋገረቻቸው የዞን አመራር ጉዳዩን በግላቸው እንደማያውቁና መንግስት በህብረተሰቡ ውስጥ የሚንሸራሸሩ መረጃዎችን ሳይንቅ በማጥራት ህብረተሰቡ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረግ ይገባዋል ብለዋል፡፡

የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አቶ ንጉሱ ጥላሁን ግን ማምሻውን በፌስቡክ ገጻቸው በከተማዋ በተሳሳተ መረጃ በተነሳሱ ወጣቶች በሆቴሉ ላይ ቃጠሎና ጉዳት መድረሱን አረጋግጠዋል፡፡
በስም ባይጠቅሱም ደብረ ማረቆስ ከተማ መግባታቸውና ለተቀሰቀሰው ተቃውሞ መነሻ ሆነዋል ከተባሉት ግለሰቦች ውስጥ አንዱ በባህር ዳር የክልሉ ምክር ቤት ስብሰባ ላይ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡