ዋዜማ ራዲዮ – በኢትዮጵያ ተዓማኒ ምርጫ ለማካሄድ የሕገ መንግስት ማሻሻያ ጭምር የሚያስፈልጋቸው እርምጃዎች መወሰድ አለበት። ምርጫው የቀረው ጊዜ አስራ ሰባት ወራት ነው። አዳዲስ ክልሎች እውቅና ይሰጠን ብለው አሰፍስፈዋል። ህዝበ ውሳኔ የሚጠብቁና የማንነት ጥያቄ ያላቸውም አሉ። ምርጫ ቦርድ እነዚህን ሁሉ ጉዳዮች ማስተናገድ ይጠበቅበታል። ታዲያ የፖለቲካ ፓርቲዎቹና መንግስት የታለመውን ተዓማኒ ምርጫ ማድረግ ይቻላቸዋል? ቻላቸው ታደሰ ይህን ዘገባ አዘጋጅቷል

ዜግነት

በተለይ ከውጭ የመጡት የፖለቲካ ድርጅቶቹ ድርብ ዜግነትን የሚከለክለው አዋጅ ትልቅ መሰናክል እንደሆነባቸው ደጋግመው አንስተዋል፡፡ አሁን በውይይቱ ከሚሳተፉት የፖለቲካ ቡድን መሪዎች ውስጥም ድርብ ዜግነት ያላቸው እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡

እዚህ ላይ እንግዲህ አሁን ሕገ መንግሥቱ ባልተሻሻለበት ሁኔታ የውጭ ዜግነት ያላቸው ፖለቲከኞች በተገኙባቸው መድረኮች የሚተላለፉ የውሳኔ ሃሳቦች እንደምን ቅቡል እና ሕጋዊ ሊሆኑ ይችላሉ? በሕጋዊነት በምርጫ ቦርድ ያልተመዘገቡ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሕዝብ ስም የምርጫ አዋጅ እና ሕገ መንግሥት ስለማሻሻል መነጋገራቸውስ አግባብነቱ እንዴት ይታያል? ትጥቁን በይፋ ያልፈታው ኦነግስ ተሳታፊ መሆኑ ጥያቄ አያስነሳም ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች መነሳት ያላባቸው ናቸው፡፡ የኦነግን ጉዳይ ወረድ ብለን እናነሰዋለን፡፡

አንዳንዶቹ የፖለቲካ ድርጅቶች ሕጋዊ ሆነው መመዝገብ ቢፈልጉ ምርጫ ቦርድ ቢያንስ አመራሮቹ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ብቻ ያላቸው መሆኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ቦርዱ ድርብ ዜግነት መያዝ አለመያዛቸውን በምን ዘዴ ያጣራዋል? የሚለው ግን ሌላ ፈተና ነው፡፡ ይህን ማድረግ የሚችለው ራሱ መንግሥት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ አማራጭ አድርገው ያቀረቡት ፖለቲከኞቹ የውጭ ዜግታቸውን ይተውት የሚል ነው፡፡ ይሄ ደሞ እንደየግለሰቡ የሚለያይ የግል ውሳኔ እንጅ በፖለቲካ ድርድር የሚፈታ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ብዙዎቹ የድርጅት አመራሮች የዜግነትን ጉዳይ ደጋግመው የሚያነሱት ራሳቸው የድርጅቶቻቸው አመራር ሆነው ለመቀጠል፣ ለምርጫም ራሳቸውን ዕጩ ተወዳዳሪ አድርገው ለማቅረብ ጽኑ ፍላጎት ስላላቸው መሆኑ የታወቀ ነው፡፡

አሁን ለምሳሌ ለዜግነት ሕጉ ሲባል ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ለኢሕአዴግ በቀላሉ የሚሞከር አይደለም፡፡ በርግጥ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይም ስለ ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ ተስፋ አልሰጡም፡፡ ኢሕአዴግ ቢሞክረው እንኳ ለየትኛውም ሕገ መንግሥታዊ ማሻሻያ የአባል ድርጅቶቹንም ይሁን የክልሎችን ድጋፍ ለማግኘቱ አስተማማኝ ዋስትና ሊኖረው አይችልም፡፡ እናም የዜግነት አዋጁ ጥቂት የማይባሉ ፖለቲከኞችን ከምርጫ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ ውጭ ሊያደርጋቸው እንደሚችል ከወዲሁ ይገመታል፡፡ ይሄም ታዲያ በምህረት መግባታችን ጥቅሙ ምንድን ነው? የሚል ቅሬታ ሊፈጥርባቸው ይችላል፡፡

በሌሎች መለስተኛ የምርጫ ደንቦች እና መመሪያዎች የተካተቱ ገደቦችን እንኳ በቀላሉ ማሻሻል ይቻል ይሆናል፡፡ ራሱ ምርጫ ቦርድ ሊያሻሽላቸው የሚችላቸውም ይኖራሉ፡፡

የፓርቲዎች ቁጥር

የፖለቲካ ድርጅቶችን ቁጥር ሰለመቀነስ ከተቃዋሚዎችም ከጠቅላይ ሚንስትሩም በውይይቱ ላይ ተነስቷል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ሦስት አራት ድርጅቶች ብትሆኑ እገዛ ለመስጠት ያመቸናል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ይሄ አባባላቸው ባንድ በኩል ግን የተለመደውን የኢሕአዴግን የጌታ እና ሎሌነት ባሕሪ መልሶ የሚያመጣ ይመስላል፡፡ የፖለቲካ ቡድኖቹ አመራሮችም ይሉኝታ የያዛቸው ነው የሚመስሉት፡፡ መቸም ተቃዋሚ ድርጅት ሆነው በጠቅላላው የለውጥ ሃይሉን እና የለውጡን ሂደት ላለመተቸት የተማማሉ መስለው መታየታቸው ሳያስገምታቸው አይቀርም፡፡

በሌላ በኩል ድርጅቶቹ የመንግሥትን እገዛ ስላገኙ ብቻ ይወሃዳሉ ብሎ መጠበቅም የዋህነት ነው፡፡ አዳዲስ ብሄረሰብን መሠረት ያደረጉ የክልልነት እና ዞን ጥያቄዎች እየመጡ ባለበት ሰዓት እና የብሄር ፖሊቲካው እንደገና እየጦዘ ባለበት ወቅት ውህደት ይሳካል ብሎ ማሰብ አስቸጋሪ ነው፡፡ ክልልነት ደሞ አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶችን ይወልዳል፡፡ የብሄር ፖለቲካው እስካለ ድረስ የብሄረሰብ ነጋዴዎች እና ጥቅመኞች የፖለቲካ ድርጅቶችን እየፈለፈሉ መቀጠላቸው የማይቀር ነው፡፡ ምናልባት የመንግሥት ጣልቃ ገብነት ከተገታ ግን ጥቆቶቹ የመዋሃድ ተስፋ ይኖራቸው ይሆናል፡፡

ላሁኑ ግን የሚጠብቅባቸውን ሕጋዊ ግዴታ መወጣት ያልቻሉትን ጥቃቅን ቡድኖች ምርጫ ቦርድ በሕጋዊ አሠራሩ እንዲሰርዛቸው ማድረግ አንዱ ተመራጭ አስተዳደራዊ መንገድ ሊሆን ይችላል፡፡

አሁን ሊሳካ የማይችለውን የሕገ መንግሥት ማሻሻያን እንተወውና መንግሥት ግን አሁንም ለተቋም ግንባታ በቂ ጊዜ እና ዝግጅት ያለው አይመስልም፡፡ የምርጫ ቦርዱ አዋጅ እና ሌሎች የምርጫ ሕጎች እና ደንቦች ማሻሻያ ገና አላለቀም፡፡ ከፖለቲካዊ ቀውስ የወጡ እና ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ማድረግ የሚፈልጉ ሀገሮች ደሞ የተራዘመ ሂደትን፣ ጥልቅ ጥናት እና ድርድርን የሚጠይቅ የምርጫ ሕግ እና ሥርዓት ማበጀት እንዳለባቸው የሌሎች ሀገሮች ልምድ ያሳያል፡፡ ይሄ በእኛ ሀገር እየሆነ አይመስልም፡፡ ምርጫ ቦርዱ ራሱ ሥልጣኑ እና ነጻነቱ ተጨምሮለት ወደ ኮሚሽንነት ከፍ ይላል ወይስ በዚያው ስያሜው እና አወቃቀሩ ይቀጥላል? የሚለው ጉዳይም ገና ምላሽ አላገኘም፡፡ ገና አዋጁ ከጸደቀለት በኋላ ነው ራሱን እስከታች ድረስ እንደገና ማዋቀር የሚጀምረው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅም በመሻሻል ሂደት ላይ ነው ገና፡፡ ለነጻ እና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ደጋፊ የሆኑት የሲቪል ማህበራት እና የፕሬስ ሕጎችም እንዲሁ በመሻሻል ሂደት ላይ ናቸው፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙሃንን መልሶ በገለልተኛነት የማዋቀሩ ነገር ጨርሶ አልተጀመረም፤ የማሻሻያ ሃሳቡም በይፋ አልቀረበም፡፡

የኦነግ ፈተና

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከቀድሞው አቋማቸው ለዘብ ብለው ቀጣዩ ምርጫ መቸ ይካሄድ? የሚለውን በውይይት ለመፍታት ሃሳብ ማቅረባቸው ግን አንድ ተስፋ ሰጭ ነገር ነው፡፡

በጠቅላላው ስለ ሁሉም ድርጅቶች ፈተና ይህን ካልን እስኪ ደሞ ኦነግን በተናጥል እንየው፡፡

ኦነግ ሰሞኑን “ምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሆነህ ተመዝገብ አለኝ፣ እኔም የለም፣ አልመዘገብም” አልኩ ብሎ አቋሙን ገልጧል፡፡ እንደ ምክንያት ያስቀመጠው ደሞ “በ1983/84 ሕጋዊ ነበርኩ፤ በዚያው ይያዝልኝ” የሚል ነው፡፡ ቦርዱ ደሞ አልተቀበለውም፤ እንዲቀበለውም ሕጉ አይፈቅድለትም፡፡ ኦነግ ይህን አቋም ሊያንጸባርቅ እንደሚችል እና ከምርጫ ቦርድ ጋር ሊወዛገብ እንደሚችል ዋዜማ ቀደም ሲሉ ግምቷን አስቀምጣ ነበር፡፡

አሁን ይሄ እሰጣገባ የተነሳው ምናልባት ኦነግ ከምርጫ ቦርድ የሕጋዊነት ሰርትፍኬት ለማግኘት ጠይቆ “መጀመሪያ ሕጋዊ ፓርቲ ሆነህ ተመዝገብ” የሚል ምላሽ ስለተሰጠው ይመስላል፡፡ በርግጥ ከውጭ ከመጡት ድርጅቶች እስካሁን በቦርዱ የተመዘገበ እንደሌለ ነው የሚታወቀው፡፡ ምናልባትም የምርጫ አዋጁ ማሻሻያ አንድ በጎ ነገር ይዞልን ይመጣ ይሆናል የሚል ተስፋ ያላቸው ይመስላል፡፡ ኦነግን ልዩ የሚደርገው ግን ከቦርዱ ጋር አተካራ በመግጠም የመጀመሪያው መሆኑ እና ጠመንጃውን በይፋ ያላስቀመጠ ብቸኛው ድርጅት መሆኑ ነው፡፡

ኦነግ “ከመንግሥት ጋር ትጥቅ ስለመፍታት ውል አልገባሁም፤ በኦሮሚያ ክልል አሁንም ታጣቂዎች አሉኝ” እያለ በአደባባይ ሲለፍፍ ከኖረ በኋላ በቅርቡ ከመንግሥት ጋር አዲስ ስምምነት እንደደረሰ ተነግሯል፡፡ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ ዳውድ ኢብሳም ተስማምተናል ብለው ሲጨባበጡ አይተናል፡፡

እዚህ ላይ እንግዲህ ኦነግንም ሆነ ሌሎችን ድርጅቶች ከኤርትራም ይሆን ከሌላ ሀገር ጋብዞ ያመጣቸው ፌደራል መንግሥቱ ነው፡፡ በዚያ ላይ ደሞ ኦነግ ታጣቂ ድርጅት ነው፡፡ እናም የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በምን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣኑ ነው ከኦነግ ጋር የሚነጋገረው? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ ተዳፍኖ ቀርቷል፡፡ ስምምነቱም ልክ እንደ አሥመራው ስምምነት ያልተብራሩት ነገሮች አሉት፡፡ ስምምነቱ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ኦነግ መካከል ነው? በኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ እና በኦነግ መካከል ነው? ወይንስ በፌደራል መንግሥቱ እና ኦነግ መካከል ነው? የሚለው ጥያቄ በጊዜው ብዥታ ፈትሮ ነበር፡፡ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንም ርስበርሱ የሚጣረሱ ዜና ነበር ያስተላለፉት፡፡

ሌላው ግርታ የፈጠረው ነገር “ኦነግ እና ሠራዊቱ ከመንግሥት ጋር ተባብረው ለመስራት ተስማምተዋል” የሚለው የመንግሥት አገላለጽ ነው፡፡ እንዴት በመንግሥት መገናኛ ብዙኻን ኦነግ እና ሠራዊቱ ተብሎ ሊገለጽ እንደቻለ ለሰሚው ግራ ነበር፡፡ መንግሥት “የትጥቅን ነገር አሥመራ ላይ ጨርሰነዋል” ባለበት አፉ መልሶ ለኦነግ ሠራዊት በተዘዋዋሪ እውቅና መስጠቱ አስተዛዛቢ ሆኖል፡፡

ለመሆኑ ኦነግ ለምንድን ነው ድጋሚ መዝገብ ያልፈለገው? ቢመዘገብስ ምን ይጎልበታል? የሚለውን ጥያቄ እናንሳው፡፡ መቸም ኦነግ ምዝገባውን ያልፈለገበትን ስውር ምክንያት እንዳለው ለእውነታ የቀረበ ግምት መያዝ ይቻላል፡፡ ድጋሚ የሚመዘገብ ከሆነ በሕጉ መሰረት ትጥቅ የፈታ መሆኑን እና በሰላማዊ መንገድ ለመታገል የወሰነ መሆኑን በይፋ በምርጫ ቦርድ ሰነድ ላይ መፈረም ያለበት መሆኑ አጣብቂኝ ውስጥ እንደሚያስገባው ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይህን ሳያደርግ ደሞ ሕጋዊ የሕልውና ሰርትፍኬት ሊያገኝ እንደማይችል ያውቀዋል፡፡

በሌላ በኩል የኦነግ አቋም የአሥመራው ስምምነት ድጋሚ ሕጋዊ ሆኖ ስለመመዝገብ ምንም የሚገልጸው ነገር የለም ወይ? ወደሚል ጥያቄ ይወስደናል፡፡ መንግሥት የስምምነቱን ዝርዝር እስካላሳወቀ ድረስ በዚህ ጉዳይ ላይ መላ ምት ብቻ እየሰጠን ለመቆየት መገደዳችን አይቀርም፡፡

ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምርጫ ቦርድ ከኦነግ ጋር ምን ዐይነት የሥራ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል? ትጥቁን በይፋ ካልፈታ ድርጅት ጋር ለመነጋገር፣ የቃል ወይም የደብዳቤ ልውውጥ ለማድረግ ምን ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን አለው? ብለን ብናነሳ ስህተት አንሆንም፡፡ ይልቅስ ቦርዱ ከኦነግ ጋር የሥራ ግንኙነት ከማድረጉ በፊት ለመንግሥት አንድ መሠረታዊ ጥያቄ ማንሳት ያለበት ይመስለናል፡፡ ኦነግ ትጥቅ ስለመፍታቱ እና በሀገሪቱ አንድም ታጣቂ ሠራዊት የሌለው ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት ስለመሆኑ መንግሥት ይፋዊ ማረጋገጫ እንዲሰጠው መጠየቅ… ቦርዱ ይህን የመጠየቅ መብት አለው፤ መንግሥትም ምላሽ የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡ ቦርዱ ሙሉ ነጻነት ኖሮት እንዲሰራ እፈልጋለሁ ብሎ የድሮ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ የነበሩትን ብርቱካን ሚደቅሳን ለቦርዱ የሾመ መንግሥት ይህን ግዴታውን ለመወጣት ፈጽሞ ሊሳነው አይገባም፡፡

መንግሥት የድሮውን ጽሕፈት ቤቱን ለኦነግ በቅርቡ የመለሰው አሥመራ ላይ በተደረሰው ስምምነት መሠረት መሆኑን ኦነግ ራሱ ገልጧል፡፡ ምንም እንኳ ጎለሌ የሚገኘው ጸሕፈት ቤቱ ከጅምሩ የማን ንብረት እንደነበር ባይገለጽም ቅሉ… ችግሩ ግን ይሄ ሳይሆን ኦነግ “የድሮ ጽሕፈት ቤቴ ከተመለሰልኝ በዚያውም የድሮው ሕጋዊ ሰውነቴ እንዳለ መቀጠል አለበት” የሚል አቋም የያዘ መስሎ መታየቱ ነው፡፡ ሁለቱ ነገሮች ግን ሰፊ ልዩነት ያላቸው ናቸው፤ ጽሕፈት ቤት መመለስ ወይም አለመመለስ ተራ አስተዳደራዊ ጉዳይ ሲሆን ባንጻሩ ሕጋዊ እና በሰላማዊ መንገድ የሚንቀሳቀስ ፓርቲ መሆኑን ቃል ገብቶ መመዝገብ ወይም አለመመዝገብ ግን ግዙፍ ሕገ መንግሥታዊ ጉዳይ ነው፡፡

ኦነግ በዚህ አካሄዱ ድሮ “በሽግግሩ ካቢኔ የነበሩኝ የሥልጣን ቦታዎች ይመለሱልኝ፤ ከሽግግሩ መንግሥት ምክር ቤት በሃይል ተገፍቼ ስለወጣሁ አሁን ባለው ምክር ቤትም ተመጣጣኝ መቀመጫ እንዳገኝ በልዩ ሁኔታ ይታይልኝ” ላለማለቱ ምንም ዋስትና አለ? እስካሁን ከታዘብነው ተነስተን ስናየው ምንም ዋስትና የለም ማለት ይቻላል፡፡

ባጠቃላይ አሁን ሁሉም ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሀገር ውስጥ ጠቅልለው መገኘታቸው አንድ ጥሩ ዕድል ነው፡፡ መንግሥት የውይይት መድረኩን ማዘጋጀቱን ትልቅ ርምጃ ነው፡፡ መንግሥትም ውጭ የነበሩትን ድርጅቶች ስላስመጣ፣ ሀገር ውስጥ ላሉትም የሕወሃትን ፈላጭ ቆራጭነት ያስወገደ ለውጥ ስለጀመረ መድረኮቹ ግን ያው እንደ ድሮው መንግሥት-መር እየሆኑ እንዳይሆን ስጋት አለ፡፡

መንግሥት አሁን የምርጫ እና የፖለቲካ ፓርቲዎችን ምዝገባ አዋጅ በቶሎ አሻሽሎ ካልጨረሰ ምርጫ ቦርድ ሥራውን ለመስራት ይቸገራል፡፡ ብዙ ግዙፍ ነገሮችም ባጭር ጊዜ ውስጥ እንዲከናወኑ የተፈለገ ይመስላል፡፡ በዚያ ላይ የክልልነት ሕዝበ ውሳኔዎች እና የሕዝብ እና ቤቶች ቆጠራ ሥራዎች ተደርበው መጥተዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅቡልነት ያላቸው፣ ሀገሪቱን ወደፊት የሚያሻግሩ የምርጫ ተቋማት እና ሕግጋት እንደምን መዘርጋት እንደሚቻል በጣም በጣም አጠራጣሪ ነው፡፡ [ተጨማሪ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/WyDtpiy7M9E