pipeline-constructionየኡጋንዳና ኬንያ መሪዎች በመጋቢት ወር ሁለተኛ አጋማሽ ላይ ኡጋንዳ ወደ ኬንያዋ ላሙ ወደብ ልትዘረጋ ባቀደችው አወዛጋቢው ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ዙሪያ ናይሮቢ ላይ ተገናኝተው ቢወያዩም ስምምነት ሳይደርሱ ተለያይተዋል፡፡ ከሁለት ሳምንት በኋላ እንደገና ካምፓላ ላይ ተገናኝተው ለመደራደር ተስማምተዋል፡፡ ባለሙያዎችም ከቀጣዩ የመሪዎች ስብሰባ በፊት በላሙ፣ ሞምባሳና ታንዛኒያ ነዳጅ ማስተላለፊያ አማራጭ መስመሮች ላይ የሚያደርጉትን የአዋጭነት ጥናት ለማጠናቀቅ ደፋ ቀና እያሉ ነው፡፡
የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧው ለምን ዲፕሎማሲያዊ ሽኩቻ ሊፈጥር ቻለ? በአፍሪካ ቀንድ ንግድ ቀጠና እና ክፍለ አህጉራዊ ትብብር ላይ ምን አንድምታ ይኖረዋል? የሚሉትን ጥያቄዎች  የሚከተለው የቻላቸው ታደሰ ዘገባ ይመለከተዋል ያድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ


የባህር በር አልባ የሆነችው ኡጋንዳ ከሁለት ዓመት በኋላ ድፍድፍ ነዳጅ ዘይቷን አምርታ ለዓለም ኣቀፍ ገበያ ለማቅረብ ወደ ጎረቤት ሀገር ወደብ የሚያደርስላት ማስተላለፊያ ቧንቧው ለመገንባት ሦስት አማራጮች አሏት፡፡ በኬንያዋ ሰሜናዊ ወደብ ላሙ፣ በደቡባዊቷ ሞምባሳ ወደብ ወይም በታንዛኒያ ወደብ በኩል መጠቀም ተችላለች፡፡ ሆኖም እስካሁንም የመጨረሻ ውሳኔ ላይ ባለመድረሷ የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ አባል የሆኑትን ሦስቱን ሀገሮች በተሟሟቀ ዲፕሎማሲያውና ፖለቲካዊ ውዝግብና ፉክክር ውስጥ ማግዷቸዋል፡፡

ኬንያና ታንዛኒያም የክፍለ አህጉሩ የንግድና ትራንስፖርት ኮሪደር ማዕከል ለመሆን ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ኬንያና ታንዛኒያ ለአካባቢው ወደብ አልባ ሀገሮች የባህር በር አገልግሎት በማቅረብ የምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማዕከል ለመሆን የሚያደርጉት ፉክክር ወደኋላ በርካታ ኣመታትን ያስቆጠረ ታሪክ አለው፡፡ ሙሴቬኒ ቀድመው የጋራ ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታ ስምምነቱን የፈፀሙት ከኬንያ ጋር ሆኖ ሳለ በመጋቢት ወር ግን ከታንዛኒያ ጋር ውል መግባታቸው ኬንያዊያን የመከዳት ስሜት እንዲሰማቸው አድርጓቸዋል፡፡ ምንም እንኳን ታንዛኒያ እንደ ኬንያ ነዳጅ ዘይት ባይኖራትም ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧው በግዛቷ ማለፉ ግን ሰፊ የስራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ የክፍለ-አህጉሩ የንግድና ትራንስፖርት ማዕከል ሊያደርጋት እንደሚችል ተስፋ ስላደረገች ፕሮጄክቱን ለማግኘት ተግታ እየሰራች ነው፡፡Pipeline map
ሦስት የመጫዎቻ ካርዶችን በእጃቸው ያስገቡት ሙሴቬኒም ከኬንያ ጋር የድርድር በራቸውን አልዘጉም፡፡ ጉዳዩን በቅርብ የሚከታተሉ ታዛቢዎች ግን ኡጋንዳና ታንዛኒያ ማስተላለፊያ ቧንቧውን ለመዘርጋት በመጋቢት ወር የደረሱበትን ስምምነት ወደ መሬት ለማውረድ እያሟሟቁ ባሉበት ሰዓት ፕሬዝዳንት ኡሁሩና የኡጋንዳው አቻቸው በድርድር የመጠመዳቸው ፋይዳ ግልፅ አይደለም ይላሉ፡፡ “ጉዳዩ እኮ ከሞላ ጎደል አልቆለታል፣ የቀረ ነገር ቢኖር ለዲፕሎማሲ እንጥፍጣፊ ለደንቡ ያህል የመጨረሻ ዕድል መስጠት ብቻ ነው” የሚሉ አስተያየት ስጭዎችም በርክተዋል፡፡

አሁን ድርድር እየተካሄደበት ያለው የላሙ የጋራ ነዳጅ ቧንቧ ግንባታ 4.2 ቢሊዮን ዶላር ወጭ የሚጠይቅ ሲሆን የታንዛኒያው ግን 5.5. ቢሊዮን ዶላር ይጠይቃል፡፡ ኬንያ እበዛም ያልተደሰተችበት በሞምባሳ ወደብ በኩል የሚዘረጋው ሦስተኛው አማራጭ መስመር ደግሞ 4.4 ቢሊዮን ዶላር ይፈጃል፡፡ የላሙ መስመር ከሁሉም አጭርና ወጭ ቆጣቢ ሆኖ ሳለ ሙሴቬኒ ፊታቸውን ወደ ታንዛኒያ ለምን አዞሩ? ለሚለው ጥያቄ የሚቀርቡት ምክንያቶች ፖለቲካዊ መሆናቸው ኬንያዊያንን ከንክኗቸዋል፡፡ ዓለም ዓቀፍ አማካሪ ድርጅቶች “ፕሮጄክቱ በተግባር ላይ በሚውልበት ጊዜ አብዛኛውን መሬት በባለቤትነት የያዙት ኩኩዩዎች የሚጠይቁትን የመሬት ካሳ መጠን ያንሩታል፤ ውዝግቡም ረዥም ጊዜ ይወስዳል” በማለት ምክር መለገሳቸው ኬንያዊያንን ቢያስኮርፍም ኡጋንዳ ግን ቆም ብላ እንድታስብ አድርጓታል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ላሙ ወደብን፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያን ያቀፈው ላፕሴት (Lapsset) የተሰኘው የንግድና ትራንስፖርት ኮሪደር ፕሮጄክት በተጀመረበት ጊዜ በኬንያ በኩል ከፍተኛ የመሬት ካሳ ውዝግብ ታይቶ ነበር፡፡

በሌላ በኩል ኢኮኖሚያዊ አዋጭነቱ የሚነገርለት የላሙ መስመር ለጎረቤት ሱማሊያ ድንበር ቅርብ በመሆኑ ለሽብርተኝነት ስጋት የተጋለጠ ያደርገዋል የሚለውም ሌላኛው የኡጋንዳ የጎን ውጋት ሆኗል፡፡ በኬንያ ስር የሰደደው ሙስናም ቢሆን ፕሮጄክቱን እንደሚያጓትተው ታዛቢዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ የኬንያ መንግስት ግን “ሽብርተንነት የጋራ ችግራችን ነው፣ ሌሎቹ ስጋቶቻችሁም ቢሆኑ በቀላሉ የሚፈቱ ናቸው” እያለ የሚሰጠው ዋስትና ኡጋንዳን ማማለል የቻለ አይመስልም፡፡ ላሙ ወደብም ግንባታው ገና አለመጀመሩ ኡጋንዳ ከሁለት ዓመት በኋላ ነዳጅ ድፍድፏን ለገበያ በምታቀርብበት ጊዜ ላይደርስላት እንደሚችል የአማካሪ ድርጅቶቹ ጥናት መጠቆሙ ሙሴቬኒ ታንዛኒያን ጠበቅ አድርገው እንዲይዙ ገፋፍቷቸዋል፡፡ በዓለም ዓቀፍ አማካሪዎች የቀረበው የአዋጭነት ጥናት ኡጋንዳ መጠነኛ ማስፋፊያ የሚጠይቀውን ነባሩን የታንዛኒያን ታንጋ ወደብ እንድትጠቀም ይመክራል፡፡

የኡጋንዳው መተላለፊያ ቧንቧ የሚያልፈው ነዳጅ ዘይት ክምችት ባለበት ሰሜናዊ ኬንያ በኩል በመሆኑ ለኬንያ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ የመምታት ያህል ሆኖላት ነበር፡፡ የመስመሩ መመረጥ ኬንያን፣ ደቡብ ሱዳንና ኢትዮጵያን ካቀፈው የአፍሪካ ቀንድ ትራንስፖርትና ንግድ ቀጠና ከሆነው ላፕሴት ኮሪደር ጋር ስለሚተሳሰር ለኬንያ አዋጭነት እንዳለው እሙን ነው፡፡ ኬንያ በመሰረተ-ልማት ኋላ የቀሩትን ሰሜናዊ ግዛቶቿን ለማልማት ተስፋ የጣለችው የመሰረተ-ልማት ዕድሎችን በሚሰፋው የኡጋንዳው ቧንቧ ዝርጋታ ላይ ነበር፡፡ ድርድሩ ከከሸፈ ግን ኬንያ የላሙ ወደብን ለማልማት ያላት ፍላጎት እንደሚቀንስ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡ ያም ሆኖ ነዳጇን ለዓለም ገበያ ለማቅረብ በነዳጅ ከበለፀገው ሰሜናዊ ግዛቷ ወደ ላሙ ወደብ በተናጥል የግሏን ነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ መዘርጋቷ አይቀርም፡፡ ሆኖም እያንዳንዱን በርሜል ድፍድፍ ለማጓጓዝ 14 ዶላር ወጭ የሚጠይቃት ሲሆን ከኡጋንዳ ጋር በጋራ ማስተላለፊያ ቧንቧ ብትጠቀም ግን ወጪዋ በ35 በመቶ እንደሚቀንስላት ከኬንያ መንግስት የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከኢኮኖሚያዊ ስሌት አንፃር ከታዬ ኡጋንዳም ከጋራ ማስተላለፊያ ቧንቧው ተጠቃሚ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም፡፡

ኡጋንዳ የላሙን መስመር መጠቀሟ ለአፍሪካ ቀንድ ኢኮኖሚያዊ ትስስር በር ከፋቺ እንደሚሆን ለተነገረለትና 23 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለሚጠይቀው ላፕሴትም መልካም ዜና እንደሚሆን ተገምቶ ነበር፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብ ሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ላፕሴት በማጓተቱ የኢትዮጵያ መንግስት በጅቩቲ በኩል የነዳጅ ማስተላለፊያ ቧንቧ ግንባታውን ማጠናከሩ ለላፕሴት እንደ መጥፎ ዜና ተደርጎ ተወስዷል፡፡

በታንዛኒያ በኩል የሚዘረጋው ቧንቧ በዝነኛው ሰሬንጌቲ ፓርክ በኩል ስለሚያልፍ ከታንዛኒያዊና ኣለም ዓቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ተቃውሞ እየገጠመው ነው፡፡ ተቃውሞው የታንዛኒያን መንግስት ውሳኔ ማስቀየር ከቻለ ኬንያ ተስፋ ይኖራታል፡፡ ይህ መሆን ዕድሉ ግን በጣም ዝቅተኛ እንደሆነ ይታመናል፡፡

በዚህ ፕሮጄክት ውዝግብ ውስጥ መንግሰታቱ ብቻ ሳይሆኑ ሦስት ዓለም ዓቀፍ የነዳጅ ኩባንያዎችም ፍጥጫ ውስጥ ገብተዋል፡፡ በኬንያና ኡጋንዳ በነዳጅ ልማት ላይ የተሰማራው የእንግሊዙ ቱሎው ኩባንያ የላሙ ወደብ መስመርን እንደሚመርጥ ያሳወቀ ሲሆን በተመሳሳይ በሁለቱ ሀገሮች ፕሮጄክቶች ያሉት የፈረንሳዩ ቶታል ነዳጅ ኩባንያ ግን የታንዛኒያውን መስመር መርጧል፡፡ በአንፃሩ ኡጋንዳ ላይ ብቻ የሚንቀሳቀሰው መንግስታዊው የቻይናው ነዳጅ ኮርፖሬሽን ግን አቋሙን ገና አላሳወቀም፡፡ ይህም ፍጥጫ በመጨረሻው መስመር ምርጫ ላይ ኩባንያዎቹ ረዥም እጆቻቸውን እንደሚያስገቡ አመላካች ሆኗል ይላሉ ጉዳዩን የሚከታተሉ ታዘቢዎች፡፡ ኡጋንዳ ፊቷን ወደ ታንዛኒያ በማዞሯ ውሳኔም የቶታል እጅ እንዳለበት ይነገራል፡፡ musevini Uhuru

ኡጋንዳ 1.7 ቢሊዮን በርሜን ያልተጣራ ዕምቅ ድፍድፍ ነዳጅ እንዳላት ሲገመት ኬንያ በበኩሏ 600 ሚሊዮን በርሜን የሚገመት የድፍድፍ ክምችት ማምረት እንደምትችል በጥናት ተረጋግጧል፡፡ ኡጋንዳ የታንዛኒያውን መስመር የምትጠቀም ከሆነ እኤአ በ2022 የመጀመሪያ ነዳጅ ምርቷን እንደምታመርት የምትጠበቀው ኬንያ ለተጨማሪ ጊዚያት ሊጓተትባት እንደሚችል ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ፡፡ ሁለቱ ሀገሮች አዝጋሚ የሆነውን ዕድገታቸውን ለማቀላጠፍ ነዳጅ ምርታቸውን ለዓለም ዓቀፍ ገበያ ማቅረብ እንደሚጠበቅባቸው ዓለም ባንክ እየመከረ ነው፡፡

የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሩ ከመዘርጋቱ በፊት ወጪው፣ የመስመር ዝርጋታው አመቺነት፣ የኬንያ ነዳጅ ክምችት መጠንና የሦስቱ ወደቦች አስተማማኝነት ግምት ውስጥ ይገባሉ፡፡ ከኡጋንዳ በኩል የሚሰማው ለኬንያ ጆሮ የማይጣፍጥ ዜና ግን የሙሴቬኒ መንግስት ለፖለቲካዊና ደህንነት-ነክ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠቱን የሚሳይ ነው፡፡ ይህም የኡሁሩ ኬንያታንና ሙሴቬኒን የጠበቀ ወዳጅነት የሚፈትን ዲፕሎማሲያዊ አጣብቂኝ ፈጥሯል፡፡ በኬንያ ስልጣን ላይ ያለው መንግስት ከሙሴቬኒ ጋር መልካም ግንኙነት ያለው ሲሆን በራይላ ኦዲንጋ የሚመራው ዋነኛው ተቃዋሚ ፓርቲ ግን ከሙሴቬኒ ጋር ሆድና ጀርባ ነው፡፡ በአንፃሩ የኬንያው ተቃዋሚ ፓርቲና የታንዛኒያው ገዥ ፓርቲ ሞቅ ያለ ግንኙነት አላቸው፡፡

ሙሴቪኔ እንደገና አቋማቸውን ቀይረው ታንዛኒያን በመክዳት በይፋ ማስተላለፊያ ቧንቧውን በኬንያ በኩል ለመገንባት ይወስኑ ይሆን? የማስተላለፊያ ቧንቧው ዝርጋታ እየተጓተተ በመሆኑ ኡጋንዳ በቅርቡ የመጨረሻ ውሳኔዋን እንደምታሳውቅ ይጠበቃል፡፡ የኬንያ ዲፕሎማሲያዊ ጉትጎታና ለምምጥ ፍሬ አፍርቶ ስምምነት ላይ ከደረሱ ግን ለሁለቱም ሀገሮች ብቻ ሳይሆን ለክፍለ-አህጉሩ ኢኮኖሚያዊ ትብብርና መሰረተ-ልማት መስፋፋት ላቅ ያለ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው ተስፋ ተጥሏል፡፡ በሌላ በኩል በኬንያና ታንዛኒያ መካከል ተባብሶ የቀጠለው ክፍለ-አህጉራዊ ኃያል የመሆን ፉክክር በምስራቅ አፍሪካ ኢኮኖሚያዊ ውህደት የወደፊት ዕጣ ፋንታ ላይ ጥቁር ጥላ እንዳያጥልበት ስጋት አሳድሯል፡፡