ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የድሬዳዋ ከተማ ከባድ የጸጥታና የደህንነት ችግሮችን ተጋርጦባታል። የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዚደንት አብዲ መሀመድ ኡመር ከስልጣንናቸው ተነስተው ክልሉ በሰላም እጦት የታመሰ ሰሞን ድሬዳዋም ከፍተኛ የጸጥታ ችግር አጋጥሟት ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታም መሞታቸው ይታወሳል።ይህ የሆነው ባለፈው አመት መጨረሻ ላይ ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የከተማዋ ነዋሪዎች በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንዳሉ ይናገራሉ። ሰለጉዳዩ ዝርዝር አለን ያንብቡት

Dire Dawa-FILE

ዋዜማ ራዲዮ- ከሰሞኑም የጥምቀት በአል አከባበር ጋር በተያያዘ ‘ፖሊስ ሰፈር’ እየተባለ የሚጠራ ቦታ ሀይማኖት ቀመስ ግጭት ለመቀስቀስ ከፍተኛ እንቅስቃሴዎች ታይተው የጸጥታ ችግሮች ተስተውለዋል።

ዋዜማ ራዲዮ በዚህ ላይ ያሰባሰበችው መረጃ እንደሚያሳየው ድሬዳዋን በዚህ ደረጃ ስጋት ውስጥ የጨመራት የሶማሌ ክልል የቀድሞ ፕሬዚዳንት አብዲ መሀመድ ኡመር ሰዎች የእርሳቸውን ከስልጣን ተወግዶ መታሰርን ተከትሎ ጅግጅጋን ለቀው ድሬዳዋ ውስጥ በመደበቃቸው ነው። እነዚህ ግለሰቦች ትጥቅ ጭምር የሚያንቀሳቅሱ እንደሆኑ ይነገራል።ነዋሪዎች እንደሚሉትም እነዚህ ሰዎች ምናልባትም እንታሰራለን በሚል ፍራቻ ከፍተኛ ገንዘብን እያንቀሳቀሱ የማተራመስ ስራን ይሰራሉ።

ጥር 16 ቀን በከተማዋ ችግሮች ዙሪያ መፍትሄ እንፈልጋለን ያሉ ወጣቶች በጀመሩት ተቃውሞ ከፖሊስ ጋር ተጋጭተዋል።

በኦሮሚያና ሶማሌ ተወላጅ ሰዎች ከንቲባነት በየተራ የምትመራው ድሬዳዋ የአሁኑ ከንቲባዋ የሶማሌ ተወላጅ የሆኑት ኢብራሂም ኡስማን ናቸው። ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማንም ለነዚህ ሰዎች ሽፋንን ይሰጣሉ በሚል በሰፊው ውንጀላ ይቀርብባቸዋል።

ለአብነት ባለፈው አመት በድሬዳዋ አቅራቢያ በምትገኘው ሲቲ ዞን የበርበርታ ማለትም የወጣቶች ንቅናቄ (በኦሮምያ የቄሮ እንቅስቃሴ እንደሚባለው) የአብዲ ኢሌን አስተዳደር በመቃወም ይደረጋል። ስለሆነም በሲቲ ዞን ይህ አይነት ንቅናቄ ሲደረግ የድሬዳዋ ከንቲባ ኢብራሂም ኡስማንም በወቅቱ የሶማሌ ክልል አስተዳደር ለነበረው አካል ወገንተኛ ሆነው በሲቲ ዞን ጣልቃ በመግባት ፖሊሶች እየላኩ ወጣቶችን እያሰሩ ተቃውም እንዲዳፈን ይጥሩ ነበር በሚል ስማቸው ይነሳል። ዛሬ ላይም ቢሆን ከከንቲባው ስር ያሉ ሰዎች ተቀየሩ እንጂ አቶ ኢብራሂም በስራቸው በመቀጠላቸው በከተማው የተለየ ነገር እንዳልመጣ የሚያነሱ አሉ።

በሌላ በኩል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በሁዋላ የድሬዳዋ የባለቤትነት ጥያቄ እንደ አዲስ በከፍተኛ ግለት እየተነሳ ነው።በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ስልጣን የመጡ ሰሞን ድሬዳዋ የኦሮሞ እንደሆነች አድርገው ተናግረዋል በሚል በከተማው ያሉ የሶማሌ ቋንቋ ተናጋሪዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ ይነገራል። ምንም እንኳ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምን መነሻነት እንደተናገሩ ግልጽ ባይሆንም።

ድሬዳዋ ከተማ በሶማሌ እና ኦሮምኛ ተናጋሪዎች በየተራ ትመራ እንጂ የባለቤትነት ጥያቄዋ ውስጥ ለውስጥ እየተብላላ የቆየ ነው።በተለምዶ በአስተዳደራዊ መዋቅሯ ጨምሮ በሌሎች ዘርፎችም 40 በመቶ ኦሮሞ 40 ሶማሌ 20 በመቶ ደግሞ የሌሎች ብሄሮች ድርሻን የሚወስዱባት ከተማ ነች። ይህን አወቃቀር እንደሚባለው የብሄር ስብጥሩን አይወክልም ሲሉ ብዙዎች ይቃወሙታል። እንደውም አፓርታይድ የሚል ስያሜ የተሰጠው ክፍፍልም ነው።

አሁን የዚህች ከተማ የማናት? ጥያቄ አደጋን ከስቷል። የሶማሌ ቋንቋም ሆነ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች የእኛ ናት ጥያቄ እየተነሳባት ነው።በዚህም ብቻ ሳይሆን የባለቤትነቱ ጥያቄ እንዴት ይፈታ በሚለው ጉዳይም ላይ አለመግባባት አለ። የተወሰኑ ወገኖች የ40 40 20 ክፍፍል እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶ የከተማዋ እጣ ፈንታ ይለይ የሚሉም አሉ።

በተለይ የከተማዋ እጣ ፈንታ በህዝበ ውሳኔ ይለይ የሚለው ፍላጎት በኦሮምያ ክልል ባለስልጣናት በኩል አመዝኖ ይታያል። በሁለቱ ተፎካካሪ ብሄር ልሂቃን ሽኩቻ በህዝብ በልጦ ለመገኘት በድሬዳዋ ሰፊ የህገወጥ መኖሪያ ቤት ግንባታና መሬት መቀራመት መስፋፋቱን ነዋሪዎች ያስረዳሉ።

የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የይገባኛል ጥያቄ በድሬዳዋ ሳይሆን በሞያሌና ሌሎች ስፍራዎችም ላይ በጉልህ እየታዩ ነው።በጉዳዩም ላይ የክልሎቹ አመራሮች በቅርቡ እንደተወያዩም ተሰምቷል። ሆኖም የሶማሌ ክልሉ ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፋ ዑመር የሁለቱ ክልሎች የድንበር ጉዳይ ለጊዜው ባይነሳ ፍላጎታቸው መሆኑ ይነገራል። ልዩ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖችና ማንነትን አስታከው ረብሻን ለሚፈልጉ አካላትም አሁን ድሬዳዋ ምቹ ሆናለች። ሄጎ የሚባሉ በአብዲ ኢሌይ አደራጅነት ይንቀሳቀሱ የነበሩ ወጣቶች በሶማሌ ክልል ይበተኑ እንጂ እንቅስቃሴያቸው በድሬዳዋ እንዳለ ይነገራል።

በስፍራው ያለ ችግርን ከኦሮምያ ክልል ጋር ባለ መስተጋብር ከመፍታት አንጻር የሶማሌ ክልል አስተዳደር በውስጡ ያለው የእርስ በርስ አለመተማመን ችግር ሳይሆንበት አልቀረም። አሁን ላይ ክልሉን የሚመራው የሶማሌ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ፖርቲ(ሶህዴፓ) አመራሮች መካከል ግጭት መፈጠሩ ይሰማል።የክልሉ አስተዳዳሪ አቶ ሙስጠፋ ዑመርን በገንዘብ ሚኒስትሩና በሶህዴፓ ሊቀመንበር አቶ አህመድ ሽዴ አቀናባሪነት ከስልጣናቸው ለማስነሳት ጥረት ተደርጓል በሚል አለመግባባት ተፈጥሯል።