Ahmed Shide, Minster of Finance- FILE

ዋዜማ- በዚህ አመት በተለየ ሁኔታ የፌዴራል እና የክልል መንግስት ተቋማት በከባድ የበጀት እጥረት እየተፈተኑ መሆኑን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያሳያል። በዚህም ሳቢያ ለበርካታ ፕሮጀክቶች መከፈል የነበረበት ገንዘብ አልተከፈለም። የወጡ የግዥ ጨረታዎች ተሰርዘዋል። መደበኛ ስራዎችን በአግባቡ ማከናወን አዳጋች ሆኗል። በአንዳንድ ክልሎች ለመንግስት ሰራተኞች መከፈል ያለበት ደሞዝ ለወራት ያልተከፈለበት ሁኔታ መፈጠሩም ታይቷል።

የፌዴራል መንግስት ለዚህ አመት ፤ ማለትም ለ2015 አ.ም በጀት በታሪክ ከፍተኛ የሆነውን 786 ቢሊየን ብር በጀትን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ማጸደቁ የሚታወስ ነው። ሆኖም ዋዜማ በገንዘብ ሚኒስቴር ካሉ ምንጮቿ እንደሰማችው የተጠቀሰው በጀት ይጽደቅ እንጂ ፣ መንግስት ያጸደቀውን ያክል ብር ለባለበጀት መስሪያ ቤቶች አላሰራጨም። 

በጀቱ ሲጸድቅ ወደ 300 ቢሊየን ብር አካባቢ ጉድለት ነበረበት። ይህንንም ጉድለት በብድር እና ዕርዳታ ይሞላል የሚል ግምት በመንግስት በኩል ነበር።ሆኖም ኢትዮጵያ የዕዳ ክፍያ ጊዜ የተመለከተ ንግግሯን ከዓለም የገንዘብ ድርጅት ጋር ባለማጠናቀቋ ሳቢያ የበጀት ጉድለቱ ሊሞላ አልቻለም። 

መንግስት የበጀት ጉድለቱን ለመሙላት ንግድ ባንኮች ከሚሰጡት ብድር 20 በመቶውን በቦንድ እንዲያበድሩት በብሄራዊ ባንክ በኩል መመሪያ ማውጣቱ ይታወሳል።ሆኖም መመሪያው የተወሰነ ገቢ ያስገኝ ይሆናል እንጂ የዚህ አመቱን የ300 ቢሊየን ብር የበጀት ጉድለት ሊሞላለት አልቻለም። በበጀት አመቱ ስድስት ወራት ከብሄራዊ ባንክ በህትመት የተበደረው 100 ቢሊየን ብርም ለዚሁ የበጀት ጉድለት ማሟያ ታስቦ የነበረ ቢሆንም የዋጋ ንረት አምጪ እንደሆነ ተነስቷል። 

በዚህ ሳቢያ በፌዴራልም ሆነ በክልል የመንግስት ተቋማት ከፍተኛ የበጀት እጥረት አጋጥሟል። ክልሎች የፌዴራል መንግስቱ የበጀት ድጎማ ተጠቃሚ እንደመሆናቸው የበጀት ችግሩ በሰፊው አግኝቷቸዋል። 

በተለይ በመንገድ ዘርፍ ላይ ያጋጠመው የበጀት እጥረት ከፍተኛ እንደሆነ የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምንጮቻችን ነግረውናል። የሰሜኑ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት ማብቃቱን ተከትሎ ፤ በጦርነቱ ሳቢያ ቆመው የነበሩ ፕሮጀክቶች ያመጡት ኪሳራ የታየው በዚህ አመት መሆኑ የበጀት ጫናውን ከፍ አድርጎታል።

በርካታ ተቋራጮች ይሰሩባቸው የነበሩት እቃዎች መዘረፋቸው እንዲሁም በጦርነቱ መውደማቸውን ተከትሎ ያቀረቡት የካሳ ጥያቄም ለመንግስት ከባድ ራስ ምታት መሆኑን ሰምተናል። 

ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር ምንጮቻችን እንደሰማነው ከሆነ ; ከካሳ እና ከግንባታ ዋጋ ከፍተኛ መናር ጋር በተያያዘ ተንጠልጥለው ያሉት ፕሮጀክቶች ከ40 በላይ ናቸው። በተለይ አንዳንዶቹ የውጭ ተቋራጮች የደረሰባቸውን ኪሳራ አካክሰው ውል የማቋረጥ አዝማሚያም አሳይተዋል። በመንገድ ሳቢያ ያጋጠመውን የገንዘብ ቀውስ በዚህ አመት ተይዞ ከነበረው በጀትም በላይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቅርቡ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽን በሰጡበት ጊዜ ፣ መንግስት አዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ሳይጀምር የተጀመሩትን ፕሮጀክቶች ብቻ ለማስጨረስ አንድ ትሪሊየን ብር ያስፈልጋል ማለታቸው የሚታወስ ነው። ከመንገድ ሌላ የማዳበሪያ ዋጋ እና የሌሎች ግንባታዎች ዋጋ መወደድ የተያዘው በጀት ላይ ተጽእኖ ነበረው።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ሁለት የንግድ ተቋም ባለቤቶች እንዳሉን ከሆነም በተለያዩ የፌዴራል መንግስት ተቋማት ለመደበኛ ግዥ ጨረታዎች ወጥተው ካሸነፉ በሁዋላ ጨረታው በበጀት እጥረጥ ሳቢያ ተሰርዞባቸዋል።

ኦሮሚያ ክልልም ደሞዛቸው እስከሶስት ሳምንት ዘግይቶ የተከፈላቸው የክልሉ ተቋማት መኖራቸውን የዞን ሀላፊነት ላይ ያሉ ሰራተኞች ነግረውናል።

ለኦሮምያ እና ደቡብ ክልል የግንባታ ተቋማት ምርቶችን ያቀረቡ ሌሎች ሁለት ነጋዴዎች ደግሞ ላቀረቡት እቃ ከተቋማቱ በጥቅሉ የ100 ሚለየን ብር ቼክ ከተጻፈላቸው ስድስት ወራት ቢያልፉም የተፈረመላቸው ቼክ በቂ ስንቅ ስለሌለው ጠብቁ መባላቸውን ነግረውናል። 

በሌላ በኩል በደቡብ ክልል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት እንደሰማነው ከሆነም ፣ ተቋሙ በስራ ማስኬጃ በጀት እጥረት ሳቢያ ሰራተኞች መደበኛ ስራቸውን አቁመዋል። 

እንደ ደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ያሉ ክሌሎች ደግሞ ለተለያዩ ቢሮ ሰራተኞች እስከ ሶስት ወር ደሞዝ መክፈል እንዳቃታቸው ሰምተናል። በተለይ የዚህ  ክልል የበጀት እጥረት ቀጣይ ክልል ከሚኖረኝ በጀት እከፍላለሁ ብሎ ብድር እስከመውሰድ እንዳደረሰው ከምንጮቻችን ሰምተናል።ሁሉም ክልሎች የፌዴራል መንግስት ድጎማ ጥገኛ መሆናቸውም ፣ የፌዴራል መንግስት ላይ የታየው ተጽእኖ አርፎባቸዋል።

በተለይ በዚህ አመት የፌዴራል መንግስት ባልተለመደ ሁኔታ በአጋማሽ አመት ላይ ተጨማሪ በጀት አለማጸደቁ ችግሩን አስፍቶታል። እንደሰማነው ከሆነም የፌዴራል መንግስት መንግስት ተጨማሪ በጀቱን ያልያዘው ቀድሞ ከመነሻው ያጸደቀውንም ገንዘብ ማግኘት ባለመቻሉ ነው። [ዋዜማ]

ማረሚያ: በዚህ ዘገባ ውስጥ የጅማ ዩንቨርሲቲ የሰራተኞቹን ደሞዝ ለአንድ ሳምንት ማዘግየቱን ገልፀን ነበር። ዩንቨርሲቲው ክፍያ ያዘገየሁት በክፍያ አሰራር ላይ ባጋጠመ እክል እንጂ በበጀት እጥረት አይደለም ሲል ነግሮናል። እኛም ዩንቨርሲቲው የጠየቀንን ማረሚያ ማድረጋችንን እንገልፃለን።