እስካሁን ስላልተያዙት 39 ተከሳሾች አቃቤ ህግ የፖሊስን ሪፖርት ያብራራ ሲሆን በብዛት የስም መመሳሰል ስላለ ተከሳሾቹን እስካሁን ለይቶ መያዝ እንዳልቻለ ተገልፀዋል፡፡

Former Somali regional head Abdi M. Oumer

ዋዜማ ራዲዮ- የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 4ኛ ወንጀል ችሎት ሚያዝያ 24 ቀን 2011 ዓም የተለያዩ መዝገቦችን ለማስተናገድ ተሰይሞ ነበር፡፡
አስቀድሞ ባየው የሶማሌ ክልል የቀድሞ ባለስልጣናት ጉዳይም የፌደራል ፖሊስ አሁን በቁጥጥር ስር ከዋሉት 6 ተከሳሾች ባለፈ 2 ተፈላጊዎችን በቁጥጥር ስር አውሎ አቅርቧል፡፡


በክልሉ በተለያዩ ስብሰባዎች እና በፌስቡክ ድህረ ገፅ ቅስቀሳ በማድረግ እና በጦር መሳርያ በመታገዝ ከሀምሌ 26-30 2010 ዓ.ም ባለው ጊዜ ውስጥ ለጠፋው የ59 ሰዎች ህይወት በርካታ አብያተ ክርስትያ መቃጠል እና ለበርካታ ሴት ልጆች መደፈር ተጠያቂ ናቸው የተባሉ የክልሉ የቀድሞ ከፍተኛ ሀላፊዎች እና ሄጎ የተባለ ቡድን አባላት ፤ በጥቅሉ 47 ሰዎች ላይ ክስ ተመስርቶ ነበር፡፡


ሆኖም እስካሁን የክልሉን የቀድሞ ርዕሰ መስተዳደር አብዲ መሀሙድ ኡመር እና ሌሎች 3 የቀድሞ አመራሮች እንዲሁም 2 የሄጎ አባል ናቸው የተባሉ ወጣቶች ብቻ ናቸው በቁጥጥር ስር የዋሉት፡፡

ችሎቱ የተሰየመው እስካሁን ባልተያዙት ላይ ፖሊስ የደረሰበትን ሪፖርት ለመመልከት ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ፖሊስ ሁለት ተጨማሪ ሰዎችን መያዙን እነሱም አባስ ሞሀመድ እና ኮሚሽነር አብዱላሂ አህመድ የተባሉ እንደሆኑ ገልፆ ችሎት ፊት አቅቧቸዋል፡፡
እናም በወንጀለኛ መቅጫ የስነስርዓት ህጉ አንቀፅ 128 መሰረት ቀዳሚው የፍርድ ቤት ተግባር የተከሳሾችን ማንነት ማረጋገጥ ነውና ስለማንነታቸው ተጠይቀው ተረጋግጧል፡፡
የተከሰሱበት ጉዳይ ከመነበቡ በፊት ግን ጠበቃ እንዲቆምላቸው የጠየቁ ሲሆን ሁለቱም ተከሳሾች አቅም የሌላቸው መሆኑን እና መንግስት እንዲያቆምላቸው እንደሚፈልጉ ለችሎቱ አስረድተዋል፡፡


ይሁን እንጂ አቅም የሌላቸው ስለመሆኑ በመሀላ እንዲያረጋግጡ ሲጠየቁ አባስ ሞሀመድ የተባሉት ተከሳሽ አልምልም በራሴ ጠበቃ ቀጥሬ አቆማለው ሲሉ ሀሳባቸውን ቀይረዋል፡፡ በዚህም መሰረት ለኮሚሽነር አብዱላሂ ብቻ የመንግስት ተከላካላይ ጠበቃ እንዲቆምላቸው ታዟል፡፡


በሌላ በኩል እስካሁን ስላልተያዙት 39 ተከሳሾች አቃቤ ህግ የፖሊስን ሪፖርት ያብራራ ሲሆን በብዛት የስም መመሳሰል ስላለ ተከሳሾቹን እስካሁን ለይቶ መያዝ እንዳልቻለ ተገልፀዋል፡፡


ለዚህም ታድያ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽንን እንዲተባበረው ቢጠይቅም ከበላይ አመራሮች ጋር ሳንነጋገር አይሆንም በማለት ለመተባበር ፍቃደኛ እንዳልሆነለት አብራርቷል፡፡
የክልሉ ፖሊስ ተፈላጊዎችን በመያዝ ረገድ እንዲያግዘው ትዕዛዝ እንዲሰጥለት የፌደራል ፖሊስ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡


በቁጥጥር ሰር ያሉ ተከሳሾች ጠበቆች በበኩላቸው ፖሊስ ከዚህ ቀደም ማግኘት አልቻልኩም ማለቱን አስታውሰው በየጊዜው በቁጥጥር ስር ያልዋሉትን ለመያዝ እየተባለ የሚሰጠው ቀጠሮ የባለጉዳዮቻቸውን የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት መብት እየተጋፋ መሆኑን ለችሎቱ ገልፀዋል፡፡


የፌደራል ፖሊስ በማንኛውም ቦታ በወንጀል የተፈለገን ግለሰብ የማምጣት ስልጣን እንዳለው በመግለፀም ምክንያቱ ተቀባይነት እንዳያገኝ የጠየቁ ሲሆን ያ ካልሆነ መዝገባችን ተለይቶ ቀጠሮ ይያዝበት ሲሉም ተቃውመዋል፡፡


የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ታድያ የፌደራል ፖሊስን ጥያቄ በመቀበል የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽ በወንጀል የሚፈለጉትን ግለሰቦች አፈላልጎ በመያዝ ረገድ አስፈላጊውን እገዛ እንዲያደርግ ጥዕዛዝ ሰጥቷል፡፡


እናም ፖሊስ ተፈላጊዎቹ ካሉ እንዲያቀርብ ከሌሉም ደግሞ በአድራሻቸው ስላለመገኘታቸው ማረጋገጫ እንዲያመጣ የታዘዘ ሲሆን ለዚህ ቀጠሮም ሰኔ 3 2011 ዓም ይዟል፡፡ [ዋዜማ ራዲዮ]