(ዋዜማ ራዲዮ)

ጤና ይስጥልኝ ጌታዬ!
ገረመው እባላለሁ፡፡ እሳት የላስኩ የፊንፊኔ ደላላ ነኝ፡፡ ምስጉን ጉዳይ ገዳይ ስለመሆኔ እግዜርም ሰይጣንም ያውቃሉ፡፡ ኪራይ ሰብሳቢ መሆኔን ድሪባም ኩማም ያውቃሉ፡፡
ዉሎአዳሬ ብሔራዊ፣ አመሻሼ አብዮታዊላየን ባር ቤቴ፣ ቴሌ ባር ግዛቴ
ጥሎብኝ አልረጋም፡፡ ካዛንቺስ ነው ሲሉኝ ሳሪስ፣ ቀበና ነው ሲሉኝ ባምቢስ!!
ድሮስ የፊንፊኔ ደላላ ምን ቀልብ አለው ብለው ነው!? እንኳን ደላላ ፊንፊኔስ ቀልብ አላት እንዴ ዛሬ?
እርስዎ ግን እንዴት ከርመዋል?


ጌታዬ! ጠፋሁብዎ አይደል? ማን ያልጠፋ አለ ብለው ነው ከሰሞኑ? እንኳን እኔ ገረመው አንድ ተራ የቢዝነስ ደላላ፣ በእንግሊዝ አፍ የሚቀኘው የቢዝነስ ጋዜጠኛ ሽቅርቅሩ! ያው ዓመታዊ የሽርሽር ፕሮግራሙን አራዝሞ ከነ ቤተሰቡ ዲሲ ነው። ወቅቱ ነዋ!


የደምበሉ የምሩ ነጋ ለዓመታዊ የጤና ምርመራ ሩቅ ምሥራቅ ነው፡፡ አኪኮ ስዩም የላቲን ሹሩባ ልትሠራ ብራዚል ናት፡፡ ሳሚ ጣሪያ የፊንፊኔን ብርድ መቋቋም አቃተኝ ብሎ ዱባይ ጁመይራ ቢች መንታ የአረብ ፀሐይ ይሞቃል፡፡ ሳቢር አርጋው በዓመታዊው የሐጅ ሶላት ሰበብ ከበረዶ የነጣ ጀለቢያ አጥልቆ መካ መዲና ይንጎማለላል፡፡ ወቅቱ ነዋ!


ጋሽ ሳቢር ወያኔ ወለድ ቢሊየነር ቢሆንም አየሩ አላማረውም፡፡ መካ መዲና ዚያራ የሄደውም ለዚሁ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ጓደኞቹ የጀለቢያውን ንጣት በቫይበር አይተው ‹‹በቢ 29 ሳሙና ነው እንዴ ያሳጠብከው?›› እያሉ ራሱ በሚያስመጣው ምርት ይቀልዱበታል፡፡ እሱም ቀልድና ጨዋታ ነፍሱ ነው፡፡


ጌታዬ! ሳቢርን መቼም ያውቁታል አይደል? የአገሪቱን ዶላር እሱ እኮ ነው የሚያጥበው፡፡ እንደኔ እንደኔ ወለኔው ቢሊየነር ሳቢር የአገሪቱ ‹‹የአስቤዛ ሚኒስትር›› ቢባል ትክክል ይመስለኛል፡፡ የማያስመጣው ሸቀጥ የለም እኮ፡፡


ኢነርጃይዘር የሱ ነው፣ ደረቅ ሳሙና የሱ ነው፣ ፈሳሽ ሳሙና የሱ ነው፡፡ የዱቄት ሳሙና የሱ ነው፣ እንኳን የልብስ ሳሙና የጥርስ ሳሙናም የሱ ነው፤ ኮልጌትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ እንኳን የጥርስ ሳሙና የጫማ ሳሙናም የሱ ነው፤ ኪዊ ቀለምን ማጥቀስ ይቻላል፣ ዘይት የሱ፣ ቢክ እስክሪብቶ የሱብስኩት የሱ፣ ሲነርላይን የሱ፣ ህትመት ወረቀት፣ ፎቶኮፒ ወረቀት፣ የብር ወረቀትሃሃሃአንዳንዴ እንዲያውም ከውጭ የሚያስመጣው አስቤዛ ሲያልቅበት ሰው ሁሉ ያስመጣል ይባላል፡፡ እውነቴን እኮ ነው….አንድ ሰሞን ረጲን የክብሪት እንጨት በሚያካክሉ ኢንዶኒዢያዎች አጥለቅልቋት ነበር….፡፡


ጌታዬ! እንደኔ እንደኔእነ ሳቢር ዘይደዋል፡፡ ምንም እንኳ የአውራው ፓርቲ ቀኝ እጆች ቢሆኑም ዘወር ማለታቸውን አልጠላሁትም፡፡ አብዮት ልጆቿን የምትበላበት ጊዜ ነዋ….፡፡ ምክንያቱም ጌታዬ…! ጋሽ ከተማ ከበደ ቂሊንጦ ሲበስበስ፣ ጌቱ ገለቴ በዱባይ መንፈላሰስ የቻለው በምን ሆነና? ከመግባት መውጣት በመምረጡ አይደልምን?
ምክንያቱም ጌታዬ! ከበደ ተሠራን ያየ፣ ከኢህአዴግ ጋር አይቀልድማ፡፡


ጋሽ ከቤ ምንም እንኳ በአራጣ፣ ስንቱን ቢያደርግ ያጣና የነጣአሁን ግን አንገቱን የደፋ፣ ቆቡን የሰፋ ቤተክስቲያን ሳሚ ሚስኪን ሽማግሌ ሆኗል፡፡ እንዲህ ያለን 70 ዓመት አዛውንት፣ 40 ዓመት ሙሉ በንግድ መርካቶን ያቀናን የሶዶ ጎበዝ፣ አላግባብ ማንገላታት ከአንድ ሆደ ሰፊ ርዕሰ ብሔር አይጠበቅም፡፡


እውነት እውነት እልዎታለሁ ጌታዬ…! የጋሽ ከበደ ተሠራ ዳግም መታሰርን ስሰማ ልቤ ነው የተሰበረው፤ ሕሊናዬ ነው አብሮት የታሠረው፡፡ ምንም ደላላ ብሆን ይሰማኛል፡፡ መፈታቱን አስመልክቶ ሰባት ቀን ሙሉ ድግስ ተሰናድቶ ገና የድግሱ ሳህን ከጠረጴዛ ሳይነሳሳ መልሰው ዘብጥያ ወረወሩት፡፡ እግዜር ይይላቸው!


ኋላ ላይ ጋሽ ሙላቱም ቢኾን ነገሩ ጸጽቶት ነው መሰለኝ ለጋሽ ከቤ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ሰደደለት ሲሉ ሰማሁ፡፡

ውድ ከበደ ተሠራ!
ይቅርታ ያልኩህ በስህተት በመሆኑ ይቅርታ እጠይቅሀለሁ፡፡ ይቅርታ እንደማይገባህ እያወቁ ይቅር እንድልህ ያደረጉኝን ግን በይቅር ባዩ አምላክ ስም እምላለሁ ይቅር አልላቸውም፡፡
አክባሪህ፣ ሙላቱ ተሾመ (/)
ኢፌድሪ፣ ፕሬዚደንት

እንዲህ ዓይነት መራር ‹‹የምህረት ክህደት ቃል›› ዐይቼም ሰምቼም አላውቅ፡፡


ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ ጌታዬ!!
የከበደ ተሠራ ልጅ በሌላ አራጣ አበዳሪ ጉድ ተሠራ ሲባል ሰማሁ ልበል? ይሄ አዲሱ አራጣ ተበዳሪ ዳዊት ከበደ ይባላል፡፡ አበዳሪው ደግሞ ዐብይ አበራ የሚባል እንደው ቅዥቅዥ ያለ ሰውዬ ነው፡፡ ባካል አውቀዋለሁ፡፡ ሰሞኑን ኢህአዴግ ጥርስ ውስጥ ገባ ሲሉኝ ብዙም ያልደነቀኝ ለዚያ ነው፡፡ ዐብይ አበራ ሰው የሚለውን መስማት የተወው እኮ ገና ድሮ 97 ምርጫ ማግስት ነው፡፡


ያኔ እኔ ሳውቀው ልጅ እግር ነበር፡፡ ከኔ ቮልስ እምብዛምም የማትሻል ወያኔ ዴክስ ነበረችው፡፡ የተቃጠለ 4ኪሎ ሞላጫ ነው ታዲያ፡፡ ማለዳ ካፌ ጎን ‹‹ጠጠር ቤት›› በሚባለው የቤተክህነት አፓርታማ ላይ ባለ አንድ መኝታ ስቱዲዮ ዉስጥ ሲኖር ገና አውቀዋለሁ፡፡ ጎረቤቶቹ የኢህአዴግ ካድሬዎች መሆናቸው ለብልጽግናው በር ሳይከፍትለት አልቀረም፡፡ ከሴኮ ጋር ባንድ ሲኒ ቡና ቺርስ ተባብለው ነበር ቀኑን የሚጀምሩት፡፡


ዐብይ አበራ ገና ቁርጥና ሽንጥ ከማለቱ ሽንጣም ሊሙዚን መሾፈር ጀመረ ተባለ፡፡ ከሊሙዚን ሾፍርና ወደ ሊሙዚን አከራይነት፣ ከሊሙዚን አከራይነት ወደ ሆቴል ባለቤትነት ተመነደገ፡፡ በልጁ ፍጥነት ደንግጣ የትውልድ ሰፈሩ ‹‹4 ኪሎ›› እንኳ 3ኪሎ ቀነሰች ተብሎ ተቀለደ፡፡
መቼስ አዲስ ቪው ሆቴልን ያውቁታል፣ ጌታዬ፡፡ ከራስ አምባ ሆቴል የሚጎራበት ነው፡፡ ‹‹አዲስ ቪው›› በቀበና ወንዝ ላይ የቁም ሽንት የሚሸና የሚመስል ግዙፍና ጥጋበኛ ሆቴል ነው፡፡ በዚህ ሆቴል ዉስጥ ሀበሻ ሀብታም አራጣ ይበደርበታል፤ ፈረንጅ ሀብታም ደግሞ ጥቁር ልጅ ይገበያይበታል፡፡ ዋሸሁ?


አዲስ ቪው ሆቴል ሄዶ የጉዲፈቻ ልጅ ያላቀፈች ፈረንጅ አላየሁም ማለት ቀበና ወንዝ ወርጄ አሳ አጠመድኩ እንደማለት ያለ ኩሸት ነው፡፡ አብይ አበራ በሌላ ስሙ ‹‹ዐብይ ጉዲፈቻ›› የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ለፈረንጅ የወዳደቁ ልጆችን ከቀበና ወንዝ ለቅሞ ይቸበችባል፡፡ ገንዘብ ለቸገረው ፈረንጅ የዱቤ አገልግሎት ይሰጣል፡፡ ዐብይማ ነፍሱ አይማርም!


እርስዎ ግን እንዴት ነዎት?
እኔ ይኸው ግማሽ ወዳጆቼን ቂሊንጦ እየተወረወሩብኝ አለሁ፡፡ ጥርስ የማያስከድነኝን ኢንጂነር ፈቃደን እንኳ አላስተረፉልኝም? 23 ቀበሌና ሻላ መናፈሻ ስንቱን ቀደን እንዳልሰፋን፣ ስንቱን እንዳልቦጨቅን፣ ስንቱን ፒስታና ጊሽጣ ራስ ባለሥልጣን አስፋልት እስኪሆን ድረስ በሐሜት እንዳልዳመጥነውአይ ኢንጂነርአንድም ቀን ሸራተን ሂልተን ሳይዝናናከሻላ መናፈሻ ሳይወጣ ጉድ አረጉት፡፡ ለማንኛውም ነፍስ ይማር ብያለሁ፣ ኢንጂነር፡፡


እውነት ለመናገርከሌሎች ታሳሪዎች እንኳ እምብዛምም እውቂያ የለንም፡፡ በዚህኛው የእስር ዘመቻ ሙሰኞቹ የተወከሉት በምክትሎቻቸው መሰለኝ፡፡ ልክ ቅሪላ ላይ የወዳጅነት ጨዋታ ሲሆን ትልቅ ቡድን በተቀያሪ ተጫዋቾች እንደሚወከለው ማለቴ ነው፡፡

አንድ ወዳጄ ከታሳሪዎች ስም ዝርዝር ዉስጥ እዚህ ግባ የሚባል የቱባ ባለሥልጣን ስም ቢያጣ ‹‹እነዚህ ሰዎች በብዕር ስማቸው ነው እንዴ የታሰሩት›› ብሎ ጠየቀ፡፡ እውነቱን እኮ ነው፡፡


ጌታዬ! እርስዎ ግን እንዴት ነዎት?
የቀን ገቢ ግምቱስ እንዴት አረገዎት?
የገቢ ግምቱ ለንደኔ ዐይነት ደላሎች ሳቅም ሐዘንም አምጥቶልናል፡፡ መርካቶ ገቢዎችና ጉምሩክ ቅርንጫፍ ሽንት ቤት ዉስጥ በድንጋጤ ለሞቱት ነጋዴ ጋሽ ግዛቸው ነፍስ ይማር ብያለሁ፡፡ በሰማይ ቤት ከመገመት ያድንዎ!


ነግሬዎ እንደሁ አላውቅም….! የኔ ጸጉር ቆራጭ ምላሱ ከደላላም ይረዝማል፡፡ መቼ ለታ ገቢዎች በቀን 200 ሰዎችን ጸጉር ታስተካክላለህ ብለው ገመቱበት፡፡ በጣም ተናደደ፡፡ ‹‹ኸረ ጎበዝ! እንኳን የደንበኞቼን ጸጉር፣ አንገትአንገታቸውን በሜንጫ ብቀላስ በቀን 200 ሰው እጨርሳለሁ?›› ብሎ ተናገረ፡፡ ይህን ጊዜ ገማቾች ሄደው ፖሊሶች መጡ፡፡ በህቡዕ ሰንሰለት ተሳትፎ አለህ ብለው ማዕከላዊ ወሰዱት፡፡


እዚህ ቸርችል ደግሞ አንድ ጋሽ ወልዴ የሚባል ጉራጌ በቀን 100 የሬሳ ሳጥን ትሸጣለህ ብለው ገቢዎች ያዙት፡፡ ከት ብሎ ከሳቀ በኋላ ምን ቢላቸው ጥሩ ነው…‹‹አባ! እንኳን አሁን 97 ላይም እንደዛ አልሸጥንም››


ጌታዬ! እርስዎ ግን እንዴት ነዎት?
ደላላ በቃህ ካልተባለ አያበቃም፡፡ እባክዎ በቃህ ይበሉኝ፡፡ በጉዳይ አስፈጻሚነት ካላሰሩኝ እንገናኛለን፡፡
ቸር ይሰንብቱልኝ፡፡
ገረመው ነኝ፣ ከቴሌ ባር– ለዋዜማ ራዲዮ