ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ከያዙ ወዲህ ሁለተኛው የሆነውን ካቢኔያቸውን ሰሞኑን አዋቅረዋል፡፡ ከዚሁ ጋርም የሥራ አስፈጻሚውን ሥልጣንና ተግባር የሚወስነው አዋጅ ተሻሽሏል፡፡ በርግጥ የሚንስቴር መስሪያ ቤቶችን አወቃቀር መቀየር አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ለአዲስ ጠቅላይ ሚንስትር ይቅርና ለነባርም ቢሆን እንደተጨባጭ ሁኔታው እያዩ ተቋማዊ ሽግሽግ እና ሹም ሽር ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በተለይ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች አንጋፋ አመራሮቻቸውን ከሃላፊነት ማግለላቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚንስትሩ አዲስ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ ሲጠበቅ ነው የቆየው፡፡ [ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

ከዚህ ይልቅ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው ትኩረት የሳቡት፡፡ መጀመሪያ አዲሱ የከቢኔ አደረጃጀት ባንድ ጊዜ ስምንት ሚንስቴር መስሪያ ቤቶችን ይቀንሳል ተብሎ እምብዛም አልተጠበቀም ማለት ይቻላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘም አንዳንድ ጥያቄዎችን ማንሳት ተገቢ ይሆናል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የሚንስቴር መስሪያ ቤቶቹን እንዴት ነው ያደራጇቸው? ካቢኔ አወቃቀራቸው ምን አዲስ ገጽታ አለው? አዲሱ ካቢኔያቸው እና አደረጃጀቱ ለሀገሪቱ ችግሮች እና ለውጡ አሁን ለደረሰበት ጊዜስ የሚመጥን ነው ወይ? የሚሉት ጉዳዮች በደንብ መዳሰስ ያለባቸው ናቸው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ የካቢኔው 50 በመቶ ለሴቶች ከመስጠታቸው ከሀገር ውስጥም ሆነ ከዐለም ዐቀፉ ኅብረተሰብ ሙገሳ አስገኝቶላቸዋል፡፡ የሴቶች ሹመት መስፈርትም ብቃት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህ ላይ አስተያየት ለመስጠት ጊዜ መጠበቅ ግድ ሊለን ይችል ይሆናል፡፡

ከዚህ ሌላ ከቀደምቶቻቸው የወረሷቸውን ተቋማት ከማሸጋሸግ ያለፈ ያመጡት አዲስ አወንታዊ ለውጥ የለም፡፡ ይልቁንስ ሌላ ጥያቄ የሚያስነሳ አደረጃጀት ነው ይዘው ብቅ ያሉት፡፡ በተለይ የሰላም ሚንስቴር ሲሉ በሰየሙት አዲስ ሚንስቴር በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጊዜ የነበረውን “cluster” የተሰኘ አወቃቀር የደገመ የጥርነፋ አወቃቀር ነው የደገመው፡፡ ሰላም ሚንስቴር ብሄራዊ ደኅንነትን፣ ኢምግሬሽንን፣ ስደተኞች ጉዳይን፣ ፌደራል ፖሊስን፣ የኢንፎርሜሽን ኔትወርክ እና ሴኩሪቲ ኤጀንሲን ለቆጣጠር እና የቀድሞውን ፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር ሃላፊነቶችንም ጨምሮ እንደተቋቋመ ነው የተገለጸው፡፡

እዚህ ላይ አንድ ቁልፍ ጥያቄ ማንሳት ግድ ይለናል፤ ከጸጥታ ከጸጥታ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተመሳሳይ መስሪያ ቤቶች ብቻ በተለየ መርጦ ባንድ ሚንስቴር መስሪያ ቤት መጠርነፍ ለምን ተፈለገ? የሚል ጥያቄ፡፡ ለዚህ ጥያቄ አጥጋቢ መልስ የሰጠ አካል አልሰማንም፡፡ አንዱ መከራከሪያ ግን ሁሉንም ተቋማት ወደ ሚንስቴር ደረጃ ከማሳደግ ይልቅ ባንድ ሚንስቴር በካቢኔው እንዲወከሉ ለማድረግ ነው ሊባል ይችላል፡፡ ይሄ አያስኬድም፡፡ በይፋ ያልተነገረ ሌላ ዐላማ ግን ያለ ይመስላል፡፡ ዋና አላማው ግን ምናልባት ጸጥታ እና ብሄራዊ ደኅንነት ነክ ተቋማትን የማማከል አካሄድ ነው የሚመስለው፡፡ ይሄ እየሆነ ያለው እንግዲህ እነዚህ ተቋማት ባንድ ላይ የሚሳተፉበት ብሄራዊ ደኅንነት ምክር ቤት ባለበት ሁኔታ ነው፡፡

ሌላው ጉዳይ ፌደራል ፖሊስ በዚሁ ጥርነፋ ውስጥ ሲካተት አቃቤ ሕግ ለምን ተነጥሎ ቀረ? የሚለው ነው፡፡ ለዚህም ግልጽ ማብራሪያ አልቀረበም፡፡ የጠየቀም የለም፡፡ እዚህ ላይ አቃቤ ሕግን የመምራቱን ሃላፊነት የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ገና በማለዳው መያዙንም ማስታወስ ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ሌላው አስገራሚ ጉዳይ ሰላም ሚንስቴር ተጠሪነቱ ለውጭ ጉዳይ ሚንስቴር መሆን የሚገባውን የውጭ ግንኙነት ስትራቴጂ ጥናት ዋና ማዕከል መጠቅለሉ ነው፡፡

የሥራ አስፈጻሚውን ሥልጣን እና ተግባር በሚወስነው አዋጅ ሰላም ሚንስቴር እነዚህን ተቋማት ከመጠርነፍ ውጭ ሌላ ምን የራሱ ሃላፊነቶች ያሉት ስለመሆኑ ገና ግልጽ አልሆነም፡፡

ሰላም ሚንስቴር የሸፈነው ሌላ ጉዳይም አለ፡፡ እንደሚታወቀው የፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር ሃላፊነት ፌደራላዊ ሥርዓቱን ይሸረሽራል የሚል ትችት ሲቀርብበት የኖረ ነው፡፡ የክልሎችን ሥልጣን ይጋፋል፤ የፌደሬሽን ምክር ቤትን ሕገ መንግስታዊ ሥልጣን ይሻማል የሚሉ ተገቡ ትችቶች ሲቀርቡበት ነው የኖሩት፡፡ አሁንም ግን ጠቅላይ ሚንስትሩ አላፈረሱትም፡፡ ይልቁንስ ያፈረሱ መስለው የመስሪያ ቤቱን ሃላፊነቶች ኮሽታ ሳያሰሙ ወደ አዲሱ ሰላም ሚንስቴር ነው ያዞሩት፡፡

ፓርላማው ከጥቂት ወራት በፊት የፌደራሉን እና ክልል መንግስታትን ግንኙነት የሚመራበትን አዋጅ አጽድቋል፡፡ ምንም እንኳ ገና ይፋ ተደርጎ ሥራ ላይ መዋሉ ባይገለጽም ቅሉ… አዋጁ ሥራ ላይ ሲውል በሥራ አስፈጻሚው በኩል ራሱን የቻለ የበይነ መንግስታት ግንኙነት ማስተባበሪያ ተቋም ይቋቋም ይሆን? ሃላፊነቱ ለፌደራል ጉዳዮች ይሰጥ ይሆን? ወይንስ ፌደሬሽን ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ ስር ይከናወን ይሆን? የሚሉ ጥያቄዎች ገና ሁነኛ ምላሽ አላገኙም፡፡ የሰሞኑ አወቃቀር ግን የሚጠቁመን ግን የበይነ-መንግሥታት ግንኙነት የመምራ ሃላፊነት ለሰላም ሚንስቴር ሊሰጥ እንደሚችል ነው፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ ለፓርላማው ባቀረቡት በጣም አጭር ማብራሪያ ግን የገንዘብ ወጭ እና ሰው ሃይልን ብክነትን ለመቆጠብ እና ተደራራቢ ሃላፊነቶችን ለማስቀረት ሲሉ የመስሪያ ቤቶቹን ቁጥር እንደቀነሱ ተናግረዋል፡፡ በርግጥም ሀገሪቱ ከገጠማት የገንዘብ እጥረት አንጻር አንዱ ትልቁ ምክንያታቸው ወጭ ቁጠባ እንደሆነ ባይናገሩትም ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ይሄ ጉዳይ ደሞ ከዐለም ዐቀፍ አበዳሪ ተቋማት ጋር መያያዙ አይቀርም፡፡

ኢሕአዴግ-መራሹ መንግሥት እንደ አትዮጵያ አየር መንገድ፣ ቴሌኮሚኒኬሽን እና ሃይል ማመንጨት የመሳሰሉ ቁልፍ የመንግሥት ኢኮኖሚ አውታሮችን ወደ ግል ባለሃብቶች ለማዞር ወስነናልን ካለ ወዲህ የዐለም ባንክ እና ዐለም ዐቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጋር ያለው ግንኙነት የሰመረለት ይመስላል፡፡

እነዚህ አበዳሪ ተቋማት በተለይ ዐለም ዐቀፉ ገንዘብ ድርጅት ደሞ የመንግሥት ተቋማት ሲለጠጡ አይስማማውም፡፡ እናም ከፍ ያለ ብድር እንዲለቀቅላችሁ ከፈለጋችሁ የተቋማቶቻችሁን ቁጥር ቀንሱ የሚል ግፊት በመንግሥት ላይ ማሳደሩ አይቀርም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ የዐለም ዐቀፉን ገንዘብ ድርጅት ስም ባያነሱም የሚንስቴር መስሪያ ቤቶችን ቁጥር ለመቀነስ ግን አንድ ገፊ ምክንያት ሆኗቸው እንደሚሆን ለእውነታ የቀረበ ግምት መያዝ አያስቸግርም፡፡

ላለፉት ሦስት ዐመታት ሕዝቡ ካነሳቸው ጥያቄዎች መካከልም ፍትሃዊ የሥልጣን እና ሃብት ክፍፍል፣ የፍትሃዊ ዕድገት ተጠቃሚነት፣ የዲሞክራሲ እና ሰብዓዊ መብቶች መከበር የመሳሰሉት አንኳር ጥያቄዎች ነበሩ፤ አሁንም ናቸው፡፡ አሁን ግን በገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ደረጃ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ተለዋውጠዋል፡፡ የትናንቱ ኦሕዴድ፣ የአሁኑ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) የጠቅላይ ሚንስትርነት ሥልጣኑን ጨብጧል፡፡ ቀደም ሲል ከያዛቸው ውጭ ጉዳይ ሚንስቴር እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሌላ ሰሞኑን ደሞ የሀገር ውስጥ ገቢን የመሳሰሉ ትላልቅ ሥልጣኖች ጠቅልሎ ይዟል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንንም እንዲሁ፡፡

የቀድሞው ብአዴን፣ የአሁኑ የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) በበኩሉ በሀገሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነውን ብሄር ይወክላል፡፡ በሕዝባዊ አመጹ ጊዜም ኦሮሚያ ክልል ቀጥሎ የአማራ ክልል ሕዝብ ነበር ለአሁኑ ለውጥ መምጣት ዐይነተኛ አስተዋጽዖ ያደረገው፡፡ ያም ሆኖ እንደካሁን ቀደሙ ሁሉ በሰሞኑ የፌደራል ሥልጣን ድልድልም አዴፓ ፍትሃዊ ድርሻውን ማግኘት እንዳልቻለ ግልጽ ሆኗል፡፡

በገዥው ግንባር ውስጥ ቁልፍ የስልጣን ማዕከል የሆነው ስራ አስፈፃሚው ከአራቱ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ ሰላሳ ስድስት አባላት ያሉት ነው። ወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮችም በዚህ ምክር ቤት ይወሰናሉ። ኦዴፓ በካቢኔ ውስጥ አራት የስራ አስፈፃሚ አባላትን ሚንስትር አድርጎ ሲያሾም አዴፓና ደኢሕዴን አንድ አንድ የሰራ አስፈፃሚ አባላቶቻቸው ብቻ ካቢኔውን ተቀላቅለዋል።

አንዳንድ ወገኖች ከሚያስቡት በተቃራኒ በተቃውሞ ጎራ የተሰለፉ የኦሮሞ ብሄርተኛ ፖለቲካ ቡድኖች እና መብት ተሟጋቾችም የጠቅላይ ሚንስትሩን መንግሥት ክፉኛ በመተቸት ተጠምደዋል ማለት አይቻልም፡፡ እንዲያውም ቀስ በቀስ በጠቅላይ ሚንስትሩ አካሄድ ደስተኛ እየሆኑ እንደመጡ መታዘብ ይቻላል፡፡ የብሄርኛ ፖለቲከኞች የመጀመሪያው ቁልፉ ጥያቄ የምንታገልለት ብሄር በሥልጣን ማማ ላይ መቀመጥ አለበት የሚል እንደሆነ ደሞ ይታወቃል፡፡

እናም አሁን የሚታየው አካሄድ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ከኦሮሞ ብሄር ያለፈው ዐይነት ሕዝባዊ አመጽ እንደማይቀሰቀስ አምኖ ይሆን ለሕዝባዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ መስጠቱን ትቶ በዋናነት ስልጣኑን ብቻ እያደላደለ ያለው? የኦሮሞ ነጻነት ግንባር መሪዎች በማናለብኝነት ሲፏልሉ ፊት ለፊት መጋፈጥ የማይፈልገውስ ከፊሉን የኦሮሞ ሕዝብ ድጋፍ ላለማጣት ይሆን? የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ቀዳሚ ትኩረት የሀገሪቱን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ሁሉን አካታች የሆነ ውይይት ማድረግ እና መፍትሄ መሻት ነው? ወይንስ የብሄር ሥልጣንን ማደላደል ነው? የሚሉ ጥያቄዎች እንድናነሳ የሚያስገድደን ሆኗል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች ሳይዘገይ ካሁኑ መፈተሸ ያለባቸው ይመስለናል፡፡

የሰሞኑ የካቢኔ ሽግሽግ የፓርላማውን ደካማነትም ያሳየ ሆኖ አልፏል፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ስልጣን ከመልቀቃቸው ጥቂት ቀደም ብሎ ፓርላማው መነቃቃት ማሳየቱ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ተስፋ አጭሮ ነበር፡፡ በሰሞኑ ካቢኔ አወቃቀር ያሳየው አቋም ግን ፓርላማው ወደለመደው የድርጅት እና የብሄር/ብሄረሰብ ፖለቲካ ጓዳ ተመልሶ መደበቁን የሚያረጋግጥ ነው ፡፡ የመንግስት ስራ አስፈጻሚ አካላትን ስልጣን እና ተግባር የሚወስነው ማሻሻያ አዋጅ የረባ ውይይት ሳይደረግበት ነው የጸደቀው፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ አንዳች እንኳ የረባ ጥያቄ አልቀረበላቸውም፡፡ የፓርላማው ባህሪ ሥራ አስፈጻሚው አካል የፈለገውን ሁሉ እንዲያደርግ እንደገና በር የሚከፍት ነው፡፡ እንዲህ ያለውን ፓርላማ ይዞ ዲሞክራሲያዊ ተሃድሶን ማምጣት ደሞ በጣም በጣም አዳጋች ነው የሚነው፡፡

እንደ መጀመሪያው ካቢኔያቸው ሁሉ ያሁኑም ከድርጅት እና ብሄር ተዋጽዖ መውጣት አልቻለም፡፡ አደረጃጀቱም የሀገሪቱን ችግሮች ምላሽ ሊሰጥ በሚችል መልኩ አልተዋቀረም፡፡ በዚህ ሁኔታ ታዲያ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ መንግሥት ሀገሪቱን ወደ ዲሞክራሲያዊ የተሃድሶ ለውጥ ይዟት ሊጓዝ ይችላልን? እስካሁን ከወሰዳቸው ለውጦች በላይስ ምን አዳዲስ ለውጦች ሊያመጣ ይችላል? የሚሉት ጉዳዮች አሳሳቢ ሆነው መቀጠላቸው የማይቀር ነው፡፡

[ዝርዝር የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/mDpm_GSmlhU