ዋዜማ ራዲዮ- በመደበኛው የባንኮችና የጥቁር ገበያ መካከል ተፈጥሮ የነበረው የተጋነነ የምንዛሪ የዋጋ ልዩነት አሁን ማሽቆልቆል መጀመሩን ዋዜማ ያሰባሰበችው መረጃ ያመለክታል።

የበዓላት ወቅት መጠኑ ከፍ ያለ የውጪ ምንዛሪ ወደ ጥቁር ገበያው የሚገባበት የነበረ ቢሆንም የዘንድሮው የዘመን መለዋጫ የጥቁር ገበያ ከበፊቱ ተቀዝቅቅዞ ታይቷል። የዋዜማ ሪፖርተር በበዓሉ ዋዜማ የጥቁር ገበያ ምንዛሪ በሚደረግባቸው አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው 74 ብር ደርሶ የነበረው የአንድ ዶላር ምንዛሪ ወደ 59 ብር ከ50 ሳንቲም ዝቅ ብሎ ሲመነዘር ነበር።

የምንዛሪ አገልግሎት ከሚሰጡ ስውር አቀባባዮችም ቁጥራቸው ቀንሶ ታይቷል። ይህ የጥቁር ገበያ ማሽቆልቆል የተከሰተው መንግስት መውሰድ በጀመራቸው አንዳንድ የገንዘብ ፖሊሲ እርምጃዎች ሳቢያ ስለመሆን(አለመሆኑ) ለዘርፉ ቅርብ የሆኑና ስማቸውን የሸሸጉ የብሄራዊ ባንክ የስራ ሀላፊ ጠይቀናል።

ሀላፊው እንደሚሉት ባንኩ ጠበቅ ያለ የገንዘብ ፖሊሲ መከተሉ በጥቁር ገበያው ለታየው መቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑን እንደሚያምኑ ነግረውናል። ከቅርብ ወራት ወዲህ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ግለሰቦች ንብረታቸውን በማስያዣነት ተጠቅመው ከባንክ በሚያገኙት ገንዘብ የውጭ ምንዛሬን ከጥቁር ገበያ ገዝቶ ከሀገር በማስወጣት እንዲሁም በሀገር ውስጥ ሲደብቁ እንደነበርና ይህም ለጥቁር ገበያ መናር እንድ ምክንያት ሆኖ ሰንብቷል።

ይህም ብቻ ሳይሆን ቤት ንብረትን እየሸጡ የውጭ ምንዛሬን የመግዛት እንቅስቃሴም በሰፊው ሲታይ እንደነበርም አንስተውልናል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች የዋጋ ንረትን ከማባባሳቸው በላይ የሀገሪቱ የደህንነት ስጋት እየሆኑ በመምጣታቸው በብሄራዊ ባንኩ በንብረት መያዣ ብድር መስጠት እንዲቆም ባንኮችን ማዘዙ እንዲሁም መንግስት የቤት ሽያጭ ላይ እገዳ መጣሉ የጥቁር ገበያ ተዋናዮች የሚንቀሳቀሱበት የኢትዮጵያ ብር እንዲያጥራቸው አድርጓል። የውጭ ምንዛሬ ጥቁር (ትይዩ) ገበያ ላይ የዋጋ ማሽቆልቆል የታየውም ገበያውን ለማንቀሳቀስ የሚያስፈልገው ገንዘብ የሚገኝባቸው መንገዶች ላይ እገዳ በመጣሉ የፍላጎት መቀዛቀዝ በመታየቱም እንደሆነ ነው ያነሱልን።

የጥቁር ገበያው ላይ የታየው የዋጋ ለውጥ ብቻም ሳይሆን ከውጭ ሀገራት “በህገ ወጥ” መንገድ ሀገር ውስጥ የሚላከው ገንዘብ ላይም ተጽእኖ መታየቱም ዋዜማ ራዲዮ ታዝባለች።በውጭ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሀገር ውስጥ ላለ ወደጅ ዘመዶቻቸው ገንዘብን ሲልኩ የውጭ ምንዛሬውን እዛው ያሉበት ሀገር ላለ ኢትዮጵያዊ ገንዘብ አዘዋዋሪ ይሰጡና : ገንዘብ አዘዋዋሪው ደግሞ ኢትዮጵያ ባለ አጋሩ በኩል ገንዘብ ለተላከለት ግለሰብ በኢትዮጵያ ብር ገንዘቡ እንዲደርሰው ማድረግ የተለመደ ነው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በውጭ ሀገራት ያሉ ኢትዮጵያውያን በዚህ መልኩ ገንዘብን ለመላክ መቸገራቸውን ዋዜማ ራዲዮ ሰምታለች።

ይህም ብቻ ሳይሆን ተመሳሳይ መንገድን በመጠቀም ውጭ ሀገር ባሉ ሰዎች የውጭ ምንዛሬ ክፍያ እየተፈጸመላቸው እነሱ ደግሞ ሀገር ውስጥ በጥቁር ገበያ ዋጋ በብር እየከፈሉ የተለያዩ ምርቶችን የሚያመጡ ግለሰቦችም  ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ከገበያው መመናመን መጀመራቸውን ሳይንሳዊ ባልሆነ መንገድ ባደረግነው ቅኝት ተገንዝበናል።

ንብረት አስመጭዎቹ ውጭ ሀገር በምንዛሬ ተከፍሎላቸው እነሱ ደግሞ በምላሹ ሀገር ውስጥ ላለ የስራ አጋር በብር ክፍያን ሲፈጽሙ በባንክ በኩል ያለው እንቅስቃሴ በመንግስት የፀጥታ ተቋም ክትትል ይደረግበትና ያስጠይቀናል የሚል ፍራቻ መኖሩንም በስራው ላይ ሲሳተፉ ከነበሩ ግለሰቦች ተረድተናል።

የብሄራዊ ባንክ የስራ ሀላፊው እንዳሉን ብሄራዊ ባንኩ በቅርቡ ለባንኮች የደንበኞቻቸውን  እንቅስቃሴ በደንብ እንዲያውቁ ባስተላለፈው መመሪያ መሰረት የታወቀ የንግድ ስራ ላይ ሳይሆኑ በባንክ ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ የሚያዘዋውሩ ግለሰቦች መረጃ ለብሄራዊ ባንክና ለፋይናንሻል ኢንተሊጀንስ ተቋም እንዲላክ እንደሚደረግ ነግረውናል።

በዚህ አሰራርም ብዙ የሚጠረጥሩ የገንዘብ እንቅስቃሴዎች ላይ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ አንስተው መመሪያው የጥቁር ገበያው እና የህገ ወጥ ገንዘብ እንቅስቃሴው ላይ አንጻራዊ ተጽእኖ ማምጣቱን ተቋማቸው እንደሚያምን ገልጸውልናል። [ዋዜማ ራዲዮ]