Gonder City2ዋዜማ ራዲዮ- በመንግስት የፀጥታ ኃይሎች እና በጎንደር ከተማ ነዋሪዎች መካከል ማክሰኞ ዕለት የተቀሰቀሰው ግጭት ዛሬም ቀጥሎ የዋለ ሲሆን መንግስት አምስት ሰዎች “በተባራሪ ጥይት” መገደላቸውን አምኗል። የመንግስት መስሪያ ቤቶች እና ሌሎች አገልግሎት መስጪያ ተቋማት ተዘግተው ውለዋል።

በጎንደር ከተማ ረፋዱን መሰማት የጀመረው የተኩስ ድምፅ ቀኑን ሙሉ ቀጥሎ ውሎ ወደ 11 ሰዓት ገደማ ረገብ ማለቱን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዋዜማ ተናግረዋል። ምሽቱን ተኩስ መቆሙንም ያስረዳሉ።

የዛሬው ዕለት የተኩስ ልውውጥ ከመጀመሪያው ቀን የከፋ እንደነበር የሚገልፁት ነዋሪዎች ከጎንደር ውጭ እና ከገጠር የመጡ ታጣቂዎች እንደተሳተፉበት ይናገራሉ። መሳሪያ ከታጠቁት ግለሰቦች የተወሰኑቱ ከበለሳ እና አርማጭሆ የመጡ እንደነበር ያብራራሉ።

“ዛሬ ጎንደር የጦርነት ቀጠና ነበር የምትመስለው” ትላለች አንዲት የከተማይቱ ነዋሪ። “በየደቂቃው ከላይም ከታችም ይተኮሳል። ወደ 10 ሰዓት አካባቢ የነበረው አስፈሪ ነበር” ስትል ሁኔታውን ትገልጻለች።

በግጭቱ የሞት እና የመቁሰል አደጋ ቢደርስም መንግስት ማምሻውን ለገዢው ፓርቲ ቅርብ በሆነው ሬድዮ ፋና በኩል ካመነው የአምስት ሰዎች ሞት ውጭ ከሌላ ወገን ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም። ከመንገድ የወደቀ አስክሬን የሚያነሳው ጠፍቶ መመልከታቸውን የዓይን እማኞች ይናገራሉ።

በከተማይቱ ባለው አለመረጋጋት እንደ ሆቴሎች እና ወርቅ ቤቶች ያሉ አገልግሎት መስጫዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል። መስታወቶቻቸው ከተሰባበሩባቸው፣ ክፍሎቻቸው ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው እና ንብረቶቻቸው ከተዘረፉባቸው መካከል ቋራ፣ ባህረ ሰላም፣ ጣና እና ዞብል ሆቴሎች ይገኙበታል።

“ጥይት የማይፈራ ህዝብ ዛሬ ነው ያየሁት” ይላል የከተማው ነዋሪ ባህረ ሰላም ሆቴል የወረሩትን ሰዎች ለመበተን የመንግስት ፀጥታ ኃይሎች እንዴት እንዳዳገታቸው ሲገልፅ። “ወደ ሰማይ ደጋግመው ከተኩሱ በሁዋላ ቆመው ማየት ጀመሩ” ይላል።