Egyptian President Abdel Fattah al-Sisi and Coptic Pope  Tawadros II
Egyptian President Abdel Fattah al-Sisi and Coptic Pope Tawadros II

(ዋዜማ ሬዲዮ)- ግብፅ የአባይ ውሀን በተመለከተ ያላትን ጥቅም ለማስጠበቅ ከምታደርገው ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና በተጨማሪ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እንደ አማራጭ በመጠቀም የኢትዮዽያን ገዥዎች በአምልኮተ-ህግ ለመገደብ ሙከራ ስታደርግ ኖራለች። አሁን ያለውን የአባይ ውዝግብ በተመለከተም የግብፅ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሚና እንድትጫወት ልዩ ተልዕኮ ተሰጥቷታል። መዝገቡ ሀይሉ የእምነት ዶሴዎችን አገላብጦ የሰሞኑን ሁኔታ ተመልክቶ ያዘጋጀው ዘገባ እነሆ አድምጡት አልያም ንባብዎን ይቀጥሉ!


የግብጿን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሲኖዶስ በመወከል በኢትዮጵያ ና በግብጽ አብያተ ክርስቲያናት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያስተባብሩት አቡነ በኢማን በቅርቡ ለአልሞኒተር እንደገለጹት በአባይ ግድብ ምክንያት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለመፍታት ቤተክርስቲያናቸው ሚና እንዳላት ተናግረዋል።

ጳጳሱ ለድረገጹ በሰጡት ቃለ ምልልስ  ”የኢትዮጵያ ሕዝብ በግብጽ ሕዝብ ላይ ጉዳት እንዲደርስበት አይፈቅድም ” ሲሉም ያላቸውን ጽኑ እምነት ገልጸዋል። ይህም የኢትዮጵያ ሕዝብ ስሜት ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲን ተወካዮች ጋር በነበራቸው ውይይት ተደጋግሞ መገለጹን ያወሱት አቡነ በኢማን፥ “የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ ሕዝብ ድምጽ ነች። ኢትዮጵያውያን ደግሞ ለግብጽ ሕዝብ ያላቸውን ፍቅርና የግብጽን ጥቅም ለመስጠበቅ ያላቸውን ፍላጎት ገልጸዋል” በማለት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በምን መንገድ በመንግስት ላይ ተጽዕኖ ለመፍጠር እንደምትችል ያላቸውን ዕይታ ለድረገጹ ጠቁመዋል።

ይህ የጳጳሱ የአቡነ በኢማን ቃለምልልስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሁለቱ አገሮች መካከል በነበረው ታሪካዊ ግንኙነት ውስጥ የነበራትን ጥንታዊ ሚና ዳግመኛ ለመጫወት እንዳሰበች ይጠቁማል። ይህ የጳጳሱ አስተያየት ብቻ ሳይኾን የአብደል ፋታህ አል ሲሲ አስተዳደርም የሚጋራው ይመስላል። ከዚህም በፊት የሁለቱ አገሮች ፍጥጫ ባየለበትም ወቅት የግብጽ መንግስት ይህን የቤተክርስቲያኒቱን ጥንታዊ ሚና እንደ ለስላሳ ዲፕሎማሲ ለመጠቀም እያሰበ እንደነበረም ተደጋግሞ ተገልጿል። የግብጹ መሪ አብደል ፋታህ አልሲሲ ይህንኑ የአባይን ጉዳይ ለመወያየት በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበትም ወቅት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ አቡነ ማትያስንና የቤተክርስቲያኒቱን መሪዎች ማነጋገር የተልዕኳቸው አንዱ አካል አድርገውት እንደነበረም የሚታወስ ነው።

ይኹንና ይህ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሙከራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ያለችበትን የወቅቱን ኹኔታና በግብጽና በኢትዮጵያ አብያተክርስቲያናት መካከል ያለውን እምብዛም ያልጠና ግንኙነት ከግምት ውስጥ ያላስገባ እንደኾነ የሚተቹትም አልጠፉም። የድረገጹ ጋዜጠኛ በሁለቱ አብያተክርስቲያናት መካከል በዴር ሱልጣን ምክንያት ያለውን ግጭት በማንሳት እንዴት እንደሚፈታ ቢጠይቃቸውም የዴርሱልጣን ገዳማት ጉዳይ አሁን የሚነሳበት ወቅት አለመኾኑን በመግለጽ ብቻ በቀላሉ አልፈውታል።

የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ የነበራት የበላይነት እስካበቃበት እስከ 1943 ዓመተ ምህረት ድረስ ሁለቱን አገሮች ከሚያስተሳስሯቸው ሁለቱ ዓበይት ጉዳዮች መካከል አንዱ ግብጽ በአባይ ላይ የነበራት ፍላጎት ሲኾን ሁለተኛውና በኢትዮጵያ በኩል እንደዋነኛ ጉዳይ ይወሰድ የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ የነበራት ጥገኝነት ነበር። ጥገኝነቱ እንዲፈጠር ምክንያት የኾነው ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ከምስረታዋ ጀምሮ እስከ 1943 ዓመተ ምህረት ድረስ የራሷ ጳጳስ ያልነበራትና በእስክንድርያው መንበር የምትተዳደር ስለነበረች ነው።

ይህ ለሁሉ ነገር መሰረት የነበረው የቤተክርስቲያኒቱ ስልጣን በግብጻውያን እጅ መቆየቱ የግብጽ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ የነበራት ተጽዕኖ መገለጫ ብቻም ሳይኾን በአገሪቱ ፖለቲካም ላይ በተዘዋዋሪ ለነበራት ተጽዕኖ በር የከፈተም ነበር። ጳጳስ ሳይኖር ለቤተክርስቲያን አገልግሎት አስፈላጊ የኾኑት የአዲስ ቤተክርስቲያን ተከላ የካህናትና የዲያቆናት ሹመት የሚስተጓጎሉ ከመኾኑም በላይ ነገስታቱም የፖለቲካ ስልጣናቸውን ለመያዝ መቀባት የነበረባቸውም በጳጳሳት ስለነበረ የግብጽ ቤተክርስቲያን በኢትዮጵያ ፖለቲካዊም መንፈሳዊም ስልጣን ቁልፉን በእጇ ይዛ እንደቆየች የሚያሳይ ነው። ይህንንም የቤተክርስቲያኒቱን ተጽዕኖ የግብጽ ነገስታትም ሊጠቀሙበት ይሞክሩ እንደነበሩም ታሪክ ይነግረናል።

እስልምና ግብጽን ከተቆጣጠረበት ዘመን ጀምሮ ከእስላማውያን የግብጽ እሚሮች በደልና መገፋት ይደርስባት የነበረው የግብጿ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ይህን በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ የነበራትን ተጽእኖ ከአሚሮቹ ጋር እንደመደራደሪያም ታቀርበው ነበር። የእስልምና ተጽዕኖ ቤተክርስቲያኒቱን ጨርሶ እንዳያጠፋት የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች በኢትዮጵያ የነበራቸውን ተሰሚነት በመጠቀም በሁለቱ አገራት መካከል በዓባይ ምክንያት ይነሳ ለነበረው ውጥረት ራሳቸውን እንደ አስታራቂ አድርገው ሲያቀርቡ እንደኖሩም የታሪክ ጸሐፊዎች ያወሱታል። ይህም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ  ቤተክርስቲያን ላይ የነበራት ተጽዕኖ ከእጇ እንዳይወጣ ሐሰተኛ ዶክመንት አዘጋጅታ  ወደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እስከማስገባትና ይህንኑ ዶክመንት መሰረት ያደረገ ሕግ በአገሪቱ ለረጅም ጊዜ በስራ ላይ በነበረው የሕግ መጽሐፍ ማለትም ፍትሐ ነገሥት ውስጥ የበላይነቷን ለዘለቄታው የሚያጸና አንቀጽ አካታ እስከማቅረብ ድረስ ደርሳም ነበር።

ይህ በግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን የገባው ሐሰተኛ ዶክመንት በ 325 ዓመተ ምህረት በኒቅያ ተደርጎ በነበረውና የኒቅያ ጉባዔ በመባል በሚታወቀው ዝነኛ ስብሰባ ላይ እንደተደነገገ የተነገረለት ዶክመንት ነበር። ሐሰተኛው ዶክመንት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ራሷን ችላ የቆመች ቤተክርስቲያን መኾን እንደማይገባትና ከኢትዮጵያውያን መካከልም አቡን ወይም ጳጳስ መሾም እንደሌለባት የሚከለክል ድንጋጌ የያዘ ነበር። ይህም ክልከላ ፍትሐ ነገሥት ከአረብኛ ወደ ግእዝ በሚተረጎምበትም ወቅት እንደ አንድ አንቀጽ እንዲሰፍር አድርገውም ነበር።

ጥንታውያኑ የኢትዮጵያ ነገሥታት ይህን ያህል ማታለል እየተፈጸመባቸው እንደነበረ ባይረዱትም በአባይ ምክንያት በግብጻውያን ላይ የነበራቸውን የበላይነት ተረድተውት እንደነበረ የታሪክ መዛግብት ይነግሩናል። ጥቂት የማይባሉ የኢትዮጵያ ነገሥታት ዓባይን እንገድባለን እያሉ ይዝቱም ነበር። በምን የቴክኖሎጂ አቅም ያደርጉታል የሚለው ጥያቄ ሲነሳ ባይሰማም የግብጽ አሚሮች ይህን የኢትዮጵያን ነገሥታት ዛቻ ችላ ማለት አቅቷቸው ሲርዱም እንደነበረ በየዜና መዋዕሎቹ የምናገኘው ታሪክ ያስረዳናል። እንዲያውም ፋቲሚድ ሱልጣን አል ሙስታንሲር በተባለው የግብጽ ንጉሥ ዘመን የኢትዮጵያው ንጉሥ ባሰራው ግድብ ምክንያት የአባይ ወንዝ ወደ ግብጽ መውረድ አቁሞ እንደነበረና የወቅቱን የአሌክሳንድርያውን ፓትርያርክ አቡነ ሚካኤልን ሽምግልና ልኮ እንዳስከፈተውም በግብጻውያን ታሪክ ተጽፏል።

አፄ ዘርአ ያዕቆብም በዘመናቸው በግብጻውያን ክርስቲያኖች ላይ ይደርስ የነበረውን መከራ በማስመልከት አባይን እንደሚገድቡም ዝተው እንደነበረ ተነግሮላቸው ነበር። አፄ ዘርአ ያዕቆብ ለግብጻውያኑ በላኩት የማስፈራሪያ መልዕክታቸውም ውስጥ አባይን ከመገደብ የተቆጠቡት እግዚአብሔርንና መገደቡ ሊፈጥር የሚችለውን እልቂት በመፍራት ብቻ እንደኾነም መናገረቸውን ታሪክ መዝግቦላቸዋል።

ይህ ኢትዮጵያውያን ነገሥታት በግብጽ ነገሥታት ላይ የነበራቸው ተጽዕኖ በምዕራቡ ዓለምም የታወቀ እንደነበረም የሚጠቁሙ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎችም ነበሩ። ለምሳሌም ያህል ኦርላንዶ ፋሪዮሶ የተሰኘውና  ሉዶቪኮ ኦሪዮስቶ በተባለ የሪናይሳንስ ዘመን ባለቅኔ የተገጠመው ቅኔ ይህንን በአባይ ምክንያት በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል የሚፈጠረውን ውጥረት  የሚጠቁም ይዘት ነበረው። የግጥሙን አንድ ክፍል ለአማርኛ እንዲስማማ አድርገን ስናነበው እንዲህ ይላል።

ይገብራል አሉ የግብጹ ሡልጣን

ማዞር ለሚቻለው እንዳሻው አባይን

ካይሮና ግዛቷን መቅሰፍት እንዳይመታት

ድርቅና መከራ እንዳያስጨንቃት

በተመሳሳይ ኹኔታም እኤአ በ 1871 የተደረሰው አይዳ የተሰኘው የጁሴፔ ቨርዲ አሳዛኝ ኦፔራም ይህንኑ በሁለቱ አገሮች መካከል የነበረውን ፍጥጫ የሚያሳይ ይዘት ነበረው። ይህን ኦፔራ በተለይ ሙዋቹ ጣሊያናዊ የኦፔራ አቀንቃኝ ሉቺያኖ ፓቫሮቲ ከተወነባቸው ዘመን አይሽሬ ኦፔራዎች መካከል አንዱ እንደኾነም የነገርለታል። በኦፔራው ውስጥ ያለችው ዋነኛዋ ገጸ ባሕርይ አይዳ ኢትዮጵያዊት ልዕልት ስትኾን ከግብጻዊ የጦር ጄኔራል ጋር የነበራት ፍቅር ያመጣባትን መከራ የሚያሳይ ነው። በሁለቱ አገሮች መካከል በተነሳው ጦርነት ውስጥ በምታፈቅረው ግብጻዊ ጄኔራል እና በኢትዮጵያዊው ንጉሥ አባቷ መካከል መወሰን አቅቷት የሚፈጥርባት ችግር የኦፔራው ዋነኛ ታሪክ ነው።

ይህ ለረጅም ዘመን የቆየው የአባይ ቀውስ ሲዳኝ የኖረው በግብጽና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስትያናት መካከል በነበረው ጠንካራ ግንኙነት ነበር። የግብጹ ጳጳስ አቡነ በኢማን የግብጽ ቤተ ክርስቲያን አሁንም ለችግሩ መፍትሔ ለማምጣት የምትጫወተው ሚና አላት ቢሉም አስተያየታቸው የወቅቱን ኹኔታ ያገናዘበ አይመስልም። ንግግራቸው ሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት ጥንት የነበራቸውን ጥገኝነት ዛመን ያለፈበት መኾኑንም አላገናዘበም።

ከ 1943 ወዲህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የራሷ ጳጳሳት ስላሏት በግብጽ ቤተ ክርስቲያን ላይ ጥገኛ የምትኾንበት ዋነኛው ምክንያት አሁን የለም። ከዚህም ሁሉ በላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ የምትፈጥርበትም ምንም አይነት መንገድ መኖሩም ፍንጭ የለም። እንኳን ለግብጽ ሕዝብ ስትል ከመንግሥት ጋር ልትከራከር ይቅርና በልማት ስም የተነኩባትን ገዳማት ጉዳይ እንኳን ለማንሳት ፍላጎትም አቅምም እንደሌላት የቅርብ ጊዜው ታሪካችን የሚነግረን ጉዳይ ነው።

አባ በኢማን ይህን አጋጣሚ ምናልባት ለአንድ ጉዳይ ሊጠቀሙበት ያሰቡ ይመስላል። አሁንም በአክራሪ እስልምና አራማጆች እየተቸገረች ያለችውን ቤተ ክርስቲያናቸውን ሕልውና በግብጽ ፖለቲካ ውስጥ ጠቃሚ መኾኗን በማሳየት ተቀባይነት እንድታገኝ ከማሰብ የመነጨ ሙከራ መኾኑን መገመት ይቻላል።