የዘገባው ጨመቅ-

  • ጥቃቱ ተራ የከብት ዝርፊያና የጎሳ ግጭት አልነበረም
  • ድርጊቱ የደቡብ ሱዳን አማፅያን መሪ ሪክ ማቻርን ለመግደል ያነጣጠረ ጭምር ነበር
  • ከአደጋው አስቀድሞ የመከላከያ ሰራዊት ከአካባቢው እንዲወጣ ተደርጓል 
  • ነዋሪዎች ከወራት በፊት ለጠሚር ሀይለማርያም የፀጥታ ሀይል በአካባቢው እንዲሰፍር ተማፅነው ነበር
  • የኢትዮዽያ መንግስት ነዋሪዎችን በግድ ትጥቅ አስፈትቶ ራሳቸውን መከላከል እንዳይችሉ አድርጓቸዋል

(ዋዜማ ራዲዮ) በጋምቤላ  ጠረፍ ባሉ አካባቢዎች በታጣቂዎች አማካኝነት የደረሰው ጭፍጨፋ ኢትዮጵያውያንን አስቆጥቷል። የ208 ሰዎችን ህይወት ሲቀጠፍ እና ወደ 100 የሚጠጉ ህጻናት እና እናቶች ታግተው ሲወሰዱ ተገቢውን የመከላከል እርምጃ በፍጥነት አልወሰደም በሚል እየተወቀሰ የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት ከጥቃቱ ጀርባ የደቡብ ሱዳን መንግስት ወይም አማፃያኑ እንደሌሉበት ለመግለፅ ጊዜ አልፈጀበትም። ጉዳዩንም የተለመደ የጎሳ ጥቃት እንደሆነ በመግለፅ ነገርየውን ለማለዘብ ሞክሯል።

South Sudan White Army members

ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ግን ግድያው በተራ የጎሳ የከብት ዝርፊያ የተነሳ ሳይሆን የደቡብ ሱዳን ቀውስ ውጤት ነው። ደቡብ ሱዳንን ላለፉት ሶስት ዓመታት እያመሳት የሚገኘው የእርስ በእርስ ግጭት መፍትሄ ሊበጅለት ጫፍ ደርሷል በሚባልበት ወቅት ጥቃቱ መፈጸሙ እንደው በአጋጣሚ የሆነ አይደለም ይላሉ የአካባቢው ተወላጆች።

በኢትዮጵያውያን ላይ የደረሰው ጥቃት የደቡብ ሱዳንን አማፅያን ዋና ወታደራዊ ቤዝ ከማጥቃት ጋር የሚያገናኙት አሉ። የአማፅያኑን መሪ እና የቀድሞ የደቡብ ሱዳን ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት ሬክ ማሻርን ለመግደል የተጠነሰሰ ሴራ አካል ነው የሚሉ መረጃዎችም ከአካባቢው አፈትልከዋል።

የደቡብ ሱዳን አማፅያን ዋና ወታደራዊ መናኸሪያቸውን ያደረጉት ፓጋክ በምትባለው የደቡብ ሱዳን የድንበር ከተማ ነው። ፖጋክ የአርብ ዕለቱ ጥቃት ከደረሰባቸው ቦታዎች አንዱ ከሆነው ላሬ ወረዳ 20 ኪሎ ሜትር የማይሞላ ርቀት ብቻ ነው ያለው። ላሬን እና ፓጋክን የሚለየው ኢትዮጵያን እና ደቡብ ሱዳንን የሚያዋስነው ጃኰዎ ወንዝ ነው።

ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ጃኰዎ እና ማኰይ የተሰኙት ሌሎቹ በኑዌር ዞን የሚገኙት ወረዳዎችም ከፓጋክ አቅራቢያ የሚገኙ ናቸው። “በወረዳዎቹ ነዋሪዎች ላይ የተፈፀመው ግድያ መጀመሪያውኑ ታቅዶ የነበረው ለፓጋክ ነበር” ይላል ዋዜማ ያነጋገረው የአካባቢው ተወላጅ።

ፓጋክ ላይ ጥቃት ለማድረስ ታስቦ የነበረው የሬክ ማሻር ወደ አካባቢው መጓዝ ተከትሎ እንደሆነ ምንጮች ይጠቁማሉ። በነዳጅ ሀብቷ በምትታወቀው የደቡብ ሱዳን ግዛት ቤንቲዩ ተጠልለው የቆዩት ማሻር ወደ ፓጋክ ያመሩት በኢትዮጵያ ላይ ጥቃቱ ከመፈፀሙ ሁለት ቀን አስቀድሞ ነበር።

ማሻር ወደ ቦታው ያመሩት ከፕሬዝዳንት ኪር ጋር በደረሱት ስምምነት መሰረት የምክትል ፕሬዝዳንትነት ቦታ ለመረከብ ወደ ጁባ ከማቅናታቸው በፊት ከከፍተኛ የጦር አመራሮቻቸው ጋር ለመምከር ነበር። ዛሬ ሰኞ ሚያዝያ 10 በጋምቤላ በኩል አድርገው ጁባ ይገባሉ ተብለው ሲጠበቁ የነበሩት ማሻር በ”ሎጀስቲክ ምክንያት” ዕቅዳቸውን ለነገ አዘዋውረዋል።

የአርቡን ጭፍጨፋ የፈፀሙት ታጣቂዎች ማሻርን እና የወታደራዊ ቤዛቸውን ኢላማ አድርገው መምጣታቸውን የሚያሳዩ “ምልክቶች” አሉ ባይ ናቸው የአካባቢው ተወላጆች። ታጣቂዎቹ ወታደራዊ ሬድዮ ይጠቀሙ እንደነበር፣ አር ፒ ጂ  እና ፒ ኬ ም የመሰሉ ከባድ መሳሪያዎችን መታጠቃቸውን እና የደቡብ ሱዳን ወታደራዊ ዩኒፎርም መልበሳቸውን ያስ ረዳሉ።

በላሬ፣ ጀኰዎ እና ማኰይ ጥቃቱን በተመሳሳይ ጊዜ አርብ ከንጋቱ 11 ሰዓት  ሲፈፅሙ በወታደራዊ ሬድዮ ይነጋገሩ እንደነበር ከግድያ ያመለጡ ሁለት ወንድሞቹን ጠቅሶ የአካባቢው ተወላጅ ይናገራል። ታጣቂዎቹ በስፋት እንደተነገረው ከሙርሌ ጎሳ የመጡ ብቻ ሳይሆኑ ዲንቃዎችና አኙዋችም እንደሚገኙበት ያስረዳል።

ሙርሌዎቹ የመጡት ፒቦር ከተሰኘውና የደቡብ ሱዳን ጆንግሌ ግዛት ዋና ከተማ ነው። ጆንግሌ ግዛት በአማጽያኑ ቁጥጥር ስር ያለ ቢሆንም ፒቦር ግን አሁንም በመንግስት ኃይሎች እጅ ያለች ነች። በጥቃቱ የተሳተፉት ዲንቃዎች ደግሞ ባህር ኤል ጋዝል ከሚባለው የደቡብ ሱዳን ግዛት የተመሙ ናቸው።

“የመጡት በእግራቸው ነው። እንደመጡ ያገኙትን ሰው መግደል ጀመሩ። ከብቶችንም ሰበሰቡ” ይላል የአካባቢው ተወላጅ።
የኢትዮጵያ መንግስት ትላንት አስተካክሎ ከወጣው ቁጥር ጋር ተቀራራቢ የሆኑ ሰዎች መገደላቸውን እና ህጻናትም ታግተው መወሰዳቸውም ያስረዳል። ከደቡብ ሱዳን የሚነሱት ሙርሌዎች በአካባቢው ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን እና ከብት መዝረፋቸው ያለ ቢሆንም የህጻናቱ ታፍነው መወሰድ ግን እንግዳ ነገር እንደሆነ ይገልጻል።
“ለእነሱ ይህ አዲስ ነገር ነው” ይላል ነገሩ ለአካባቢው ተወላጆች ያልተለመደ መሆኑን ሲያብራራ።
ከሳምንት በፊት በኑዌር ዞን በምትገኘው ማካክ የገጠር ቀበሌ በተደረገ የሙርሌዎች የከብት ዝርፊያ በተመሳሳይ 11 ህጻናት የተወሰዱ ሲሆን 20 ነዋሪዎች  መገደላቸውን ያስታውሳል። ከሁለት ሳምንት በፊት በማኰይ ወረዳ ወደ ምትገኘው አዱራ ቀበሌ የመጡት ሙርሌዎች ከብትም ሳይዘርፉ ህጻናትም ሳይወስዱ መመለሳቸውን ይገልጻል።

ከሙርሌዎች የከብት ዘረፋ ባህል ባሻገር በአካባቢው ተደጋጋሚ ጥቃት እንዲፈጸም ምክንያት የሆነው ነዋሪዎቹ ራሳቸውን የሚከላከሉበት መሳሪያ በማጣታቸው እንደሆነ ያስረዳል። ከሶስት ዓመት በፊት በአካባቢው የተከሰተ አንድ ሁነት በነዋሪዎቹ ዘንድ የነበረ የጦር መሳሪያ እንዲሰበሰብ ምክንያት ሆኗል።

ሁነቱ ኢትዮጵያ እና ናይጄሪያ ለዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የእግር ኳስ ጨዋታ በሚያደርጉበት ወቅት “ለናይጀሪያ ደግፏችኋል” በሚል በአካባቢው በነበሩ  የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና  ነዋሪዎች መካከል በተከሰተ አምባጓሮ የዞን አስተዳደሪ መገደሉ ነበር። በዚህ መነሾ ነዋሪዎቹ ራሳቸውን ለመጠበቅ የገዟቸው መሳሪያዎች በመንግስት እንዲሰበሰቡ መደረጉን የአካባቢው ተወላጅ ይናገራል።

በአምባጓሮው የተቀሰቀሰውን ስሜት ለማብረድ በአካባቢው የነበረው የመከላከያ ሰራዊት በፌደራል ፖሊስ እንዲተካ ማድረጉንም ያብራራል። የአርቡ ጥቃት ከተፈጸመ በኋላ መጀመሪያ የ”ድረሱልን ጥሪ” የቀረበው ለእነዚሁ የፌደራል ፖሊስ አባላት እንደነበር እና ሁሉ ነገር ከተከናወነ በኋላ በቦታው ላይ “ዘግይተው መድረሳቸውን” ይጠቅሳል።

በህዳር ወር በጋምቤላ በተካሄደው የብሄር ብሄረሰቦች በዓል ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የተገናኙት የአካባቢው ተወላጆች በድንበር በኩል የሚያጋጥማቸውን ተደጋጋሚ የጸጥታ መድፍረስ ጉዳይ አንስተው እንደነበር በውይይቱ ላይ ተሳትፎ የነበረ ግለሰብ ለዋዜማ ተናግሯል። በስብሰባው  በአካባቢው የጸጥታ ኃይል እንዲመደብ አሊያም የአካባቢው ነዋሪዎች እንዲታጠቁ መንግስት እንዲፈቅድላቸው መጠየቃቸውን ያስረዳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ለተሰብሳቢዎቹ በሰጡት ምላሽ የጸጥታ ኃይሎች በአካባቢው እንደሚመደቡ ቃል ገብተው እንደነበር ያስታውሳል። መቼ የአካባቢውን ጸጥታ መቆጣጠር እንደሚጀምሩ ሳይጠቅሱ ማለፋቸውንም አልረሳም።

“አሁን በጣም ረፍዷል” ይላል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገቡትን ቃል ለመፈጸም የነበራቸውን ጊዜ እያሰላ።

መንግስት ወታደሮችን መመደብ ካልቻለ ነዋሪዎቹ እንዲታጠቁ መፍቀድ እንደነበረበት የሚከራከሩት የአካባቢው ተወላጆች የወረዳዎቹ ነዋሪዎች ታጥቀው ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል ጉዳት አይደርስም ነበር ሲሉ ይቆጫሉ።  የደቡብ ሱዳን ቀውስ እስካልበረደ ድረስ ተመሳሳይ ጥቃቶች ላለመድረሳቸው ምንም ማስተማመኛ እንደሌለ ያስረዳሉ።

ሬክ ማሻር እና የፕሬዝዳንትነት ስልጣኑን የጨበጡት ሳልቫ ኪር በሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጪ ንቅናቄ (SPLM) ጥላ ስር ለሰላሳ ዓመታት  ታግለው ነጻነቷን እንድትጎናጽፍ ካደረጉ ታጋዮች መካከል ቢሆኑም የፈጠሩት የስልጣን እና የጎሳ ቁርቋሶ ሀገሪቱ አሁን ለምትገኝበት ቀውስ መነሻ ሰበብ ሆኗል።

Gambela residents

አስራ ሁለት ሚሊዮን ከሚገመተው የደቡብ ሱዳን ህዝብ ውስጥ የአብላጫው የዘር ግንድ የሚመዘዘው ከዲንቃ ጎሳ ሲሆን የኑዌር ተወላጆች በሁለተኛነት ይከተላሉ። ከዲንቃ ወገን የሆኑት ኪር ስልጣኑንም ሆነ ሁሉን ነገር ጠቅልለው ለጎሳቸው ሰዎች ሰጥተዋል በሚል ከኑዌሩ ማሻር እና ከጎሳ አባላቶቻቸው ቅሬታዎች መነሳት የጀመሩት ደቡብ ሱዳን ገና ነጻነቷን ሳታገኝ በራስ ገዝ አስተዳደር ደረጃ እያለች ነበር።

ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ከመገንጠሏ በፊት ህይወታቸውን በአደጋ ያጡት እና የሀገሪቷ መስራች አባት ተደርገው የሚቆጠሩት ጆን ጋራንግ እውነተኛ ወራሽ “እኔ መሆን ይገባኛል” የሚለውም ሌላው የልዩነት ነጥብ ነው። ወራሹ እንደ ጋራንግ “charismatic” መሆን ይገባዋል የሚል እምነት በቀድሞ ታጋዮች ዘንድ አለ።

የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸው እና እሳት የላሱ ተናጋሪ ናቸው የሚባሉት ማሻር ሀሳባቸውን በቅጡ እንኳ ለመግለጽ የሚቸገሩትን እና “ያልተማሩ ናቸው” የሚሏቸውን ኪርን “ለቦታው ተገቢ አይደለም” በሚል ያጣጥሏቸዋል። የፕሬዝዳንት ስልጣን የሚገባው “ለማንም ሳይሆን ለእኔ ነው” የሚል እምነት አላቸው።

ኪር በበኩላቸው ማሻርን “መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂድብኝ ነበር” በሚል ይወነጅሏቸዋል። የሁለቱ ልዩነት ፈንድቶ በይፋ ከመውጣቱ በፊት ውስጥ ውስጡን አንዱ ሌላውን ለመጣል ሲሞክሩ ቆይተዋል።

በግልፅ ከሚታየው የሁለቱ መሪዎች የስልጣን ግብግብ ሌላ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍል ጥያቄ እና ሀገሪቱ ያላትን የነዳጅ ሀብት ለመቆጣጠር የሚደረግ ትግል ደቡብ ሱዳን በአዙሪት የፖለቲካ ቀውስ እንድትዳክር አድርጓታል። ቀውሱ መቋጫ እንዳያገኝ ያደረገው ደግሞ የደቡብ ሱዳን ጎረቤቶች እና ሌሎች ሀገራት እጃቸውን በጉዳዩ ማስገባታቸው ነው።

የደቡብ ሱዳን ጦስ በቋፍ ላይ ባለው የጋምቤላ የጸጥታ እና የኃይል አሰላለፍ ላይ የሚያመጣውን ቀጥተኛ ተፅዕኖ የሚያውቀው የኢትዮጵያ መንግስት ቀውሱን በአጭር ጊዜ ለመፍታት ሞክሮ አልተሳካለትም። የገለልተኝነት የአሸማጋይነት ሚናን በይፋ በመውሰድ ላይ ታች ቢልም በደቡብ ሱዳን የኢኮኖሚ ከፍተኛ ተጠቃሚነት እንዳላት ኡጋንዳ ያሉ የውጭ ኃይሎች ቀውሱን በማወሳሰባቸው  የተመኘውን ማግኘት አልቻለም።

የኢትዮጵያ መንግስት የገለልተኝነት ጉዳይም ቢሆን በተደጋጋሚ ጥያቄ ውስጥ ሲገባ ተስተውሏል። የአማፅያኑ መሪ ማሻር ላይ “ለዘብተኝነት ያሳያል” በሚል ይተቻል። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ የማሻርን ጎሳ የሚጋሩት ኑዌሮች በጋምቤላ በብዛት የመገኘታቸው እውነት ነው።

“ማሻር ብርድ ሲይዘው ጋምቤላ ታስነጥሳለች” ዓይነት አባባል የሚጠቀሙ የፖለቲካ ተንታኞች ብዙ ናቸው። ኢትዮጵያዊ ኑዌሮች ከማሻር ጋር አይወግኑም ቢባሉ እንኳ በጋምቤላ በስድስት የስደተኞች ካምፕ ውስጥ ተጥለለው የሚገኙ ደቡብ ሱዳናውያን ጉዳይ በቀላሉ የሚታይ እንዳልሆነ የሚያስረዱ ተንታኞች አሉ።

የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች መርጃ ድርጅት በሚያዝያ ወር መጀመሪያ ባወጣው ሪፖርት መሰረት 271,435 ደቡብ ሱዳንውያን ስደተኞች በጋምቤላ ካምፖች ይገኛሉ። ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የኑዌር ጎሳ ተወላጆች ናቸው።

አሁን ያለው የጋምቤላ የስልጣን አመዳደብ በደቡብ ሱዳን ባለው እውነታ ላይ የተመረኮዘ እንደሆነ ተንታኞች ይገልፃሉ። ለረጅም ጊዜ የጋምቤላን ክልል ሲያስተዳድሩ የቆዩት አኙዋዎች ወደ ጎን ተገፍተው የርዕሰ መስተዳድርነቱ ቦታ ለኑዌሮች ከተሰጠ ሁለት ዓመት አለፈ።