Pope Franciesየካቶሊኩ ዻዻስ ፖፕ ፍራንሲስ የቤተክርስቲያኒቱ አማኞች ከአቅም በላይ ከሆነ ፍቺ መፈፀም “ከፈጣሪ አያጣላም” ሲሉ መናገራቸው የሰሞኑ ትልቅ ዜና ነበር። “ድመትና ውሻ ከማሳደግ – ውለዱ ክበዱ ራስ ወዳድ አትሁኑ” ሲሉም መክረዋል። ከሁሉ በላይ የተከታዮቻቸውን ቀልብ የሳበው ግን የቀልድ ዘመቻቸው ነው። መዝገቡ ሀይሉ ዝርዝሩን ይነግራችኋል፣ አድምጡት

 

 

የካቶሊኩ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ ወደ መንበራቸው ከመጡበት መንገድ ጀምሮ የዓለምን ትኩረት የሳቡ ሰው ናቸው። ከእርሳቸው በፊት በጵጵስናው መንበር ላይ የነበሩት ፖፕ ቤነዲክት 16ኛ በድንገት “ደከመኝ፣ አረጀሁ” በማለት ባልተለመደ ኹኔታ ሥልጣናቸውን በመልቀቃቸው ነው ፖፕ ፍራንሲስ ወደ መንበሩ የመጡት። ይህ በራሱ ትልቅ ትኩረት የሳበ ጉዳይ ኾኖ ቆይቱዋል። ከርሳቸው በፊት ከነበሩት ጳጳሳት በተለየም የሚመርጡት ቀላል የሕይወት መንገድ በብዙዎች ዘንድ እንዲወደዱና እንዲከበሩ አድርጉዋቸዋል።
አሁን ደግሞ በዚህ የፈረንጆች ወር መጨረሻ በ United States of America የሚያደርጉት ጉብኝት ትልቅ ግምት እያሳደረ ይገኛል። አሜሪካም ጳጳሱን ለመቀበል የምታደርገው ሽርጉድ በግልፅ ይታያል። ፖፕ ፍራንሲስ አሜሪካ ሲደርሱ በጉጉት ከሚጠብቃቸው የአሜሪካውያን ካቶሊኮች አቀባበል ጀምሮ የምርጫ ትኩሳት ባጋለው የአሜሪካ ፖለቲካ ላይ የሚያመጡት ተጽእኖ ምን ሊኾን እንደሚችል እየተገመተ ነው። ከ ስምንት ሺህ በላይ ጋዜጠኞች የጳጳሱን ጉብኝት ለመዘገብ ዝግጅት እያደረጉ ነው። የጳጳሱን ደኅንነት ለመጠበቅም የአሜሪካው FBI ሰራተኞች የሚያደርጉት ዝግጅት እስከዛሬ ድረስ ለሌሎች የአገር መሪዎች ይደረግ ከነበረው በእጅጉ እንደሚበልጥም የፕሮግራሙ አዘጋጆች ይናገራሉ።
እስከዛሬ ድረስ ጳጳሱ ባደረጉዋቸው ንግግሮች በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ የቀኙንም የግራውንም የፖለቲካ አራማጆች አንዳንዴ ሲያስከፉ አንዳንዴ ሲያስደስቱ በመቆየታቸው በአሜሪካ ጉብኝት ወቅት የሚናገሩትን ነገር በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል። የቀኝ ዘመም ፖለቲካው የተመሰረተበትን የካፒታሊዝም ሥርዓት እንደ ስግብግብ እና ለድኾችና ለተቸገሩ የማያስብ የክፋት መንገድ አድርገው የሚናገሩት ፖፕ ፍራንሲስ፤ ከፍቅር እና ከይቅርታ መልእክታቸው ጎን ለጎን ይህንኑ የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ዐይን እንደሚነኩ ይጠበቃል። በሌላም በኩል ከክርስቲያን መልእክታቸው የተነሳ ፅንስ ማቁዋረጥንና የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን በተመለከተ የሚናገሩት መልዕክት ለግራ ዘመሙ የዲሞክራቲክ ፓርቲ አባላት እና ደጋፊዎች ብዙም የማያስደስት መኾኑ ይገመታል። ከሁሉ ይልቅ የሚጠበቀው ነገር ደግሞ የፖፕ ፍራንሲስ ድንገተኛ መልዕክት ነው። በተዘጋጀላቸው መንገድ ብቻ የማይሔዱት ፖፕ ፍራንሲስ በብዙ ተንታኞች ግምት በድንገት ሊያደርጉት የሚችሉት ሌላ ነገር ይኖር ይኾናል ተብሎም ግምት ተሰጥቱዋቸዋል።
ከዚሁ የአሜሪካ ጉብኝታቸው ጋር ተያይዞም የካቶሊክ ቤተክርትስቲያን በመላው ዓለም ለምታደርገው የረድኤት ሥራ ጌንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻም ተጀምሩዋል። “Missio” የተባለው ይኸው ዘመቻም “ከጳጳሱ ጋር ይቀልዱ” የሚል ድረገጽ ከፍቶ ቀልዶችን ማሰባሰብ ጀምሩዋል። “ቀልድ ይለግሱ” የሚለው የሚሲዮ ዘመቻ በመላው ዓለም ያሉ ሰዎች በዌብሳይቱ ላይ በሚያስተላልፉት ቀልድ አማካኝነት ለረድኤት ሥራው ያላቸውን አጋርነት ከማሳየታቸውም በተጨማሪ ገቢውን ለሚፈልጉት የረድኤት ሥራ እንዲሰጥ የመምረጥም ዕድል ይሰጣቸዋል። ቀልድ ለጋሾቹ የሚለግሱት ቀልድ በአንደኝነት ከተመረጠላቸው የፖፕ ፍራንሲስ “Comedic Adviser” (የቀልድ ጉዳዮች አማካሪ) የመኾን ማዕረግም ይሰጣቸዋል።
ለዚህ ዓላማ ብለው ባይናገሩትም ቀልዱን የጀመሩት ራሳቸው ፖፕ ፍራንሲስ እንደኾኑ የሚሲዮ ሰራተኞች ይናገራሉ። ሚሲዮ ካዘጋጃቸው የዘመቻው ማሳያ ነገሮች አንዱ የኾነው የሚሲዮ አርማ ያለበት ኮፍያ ለፖፕ ፍራንሲስ ተበርክቶላቸው ነበር። የፖፕ ፍራንሲስ ምላሽ “ጎሽ አሁን ገና ዐይኔን ከፀሐይ የሚከልል ኮፍያ አገኘሁ!” የሚል ነበር። አብረዋቸው ለሚሰሩት ይህ ከተለመደው ጨዋታ አዋቂነታቸው የመነጨ ንግግር ነበር።
“የሚለግሱት ቀልድ ከእነዚህ ነገሮች አንዱን ሊያግዝ ይችላል። በቦንስ አይረስ አርጀንቲና የሚገኙ የተቸገሩ ሕፃናትን መርዳት፣ በአዲስ አበባ ኢትዮጵያ ላሉ ጎዳና ተዳዳሪዎች ቤት መሥራት ወይም በናይሮቢ ኬንያ የሚገኙ የተራቡ ሰዎችን መመገብ” ይላል የ”ከጳጳሱ ጋር ይቀልዱ” ዓላማ።
የመጀመሪያው ቀልድ ነጋሪ “The Late Night Show” በመባል የሚታወቀው የቴሌቪዥን ፕሮግራም አዘጋጅ Conan O’Brien ነው። እንዲህ ብሉዋል፤ “የካሊፎርኒያ ድርቅ እጅግ ከመክፋቱ የተነሳ በናፓ የሚገኙ ሰዎች ጳጳሱ ወይንጠጁን ወደ ውሃ እንዲቀይሩላቸው እየተማጠኑ ነው!” (ናፓ በካሊፎርኒያ የሚገኝ በወይንጠጅ የሚታውቅ ግዛት ነው።)
ይህ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን የጀመረችው ዘመቻ ለዘመናት ሲሰነዘርባት የነበረውን ቀልድ ለቤተክርስቲያኒቱ ጥቅም የማዋል ሙከራ ይመስላል። በሳይንስና ቴክኖሎጂም ከዘመኑ ጋር ለመራመድ ጥረት እያደረገች እንደኾነም በግልጽ ይታያል። ሳይንቲስት የኾኑ ካህናቱዋ እና በልዩ ልዩ ሙያ እውቅና ያገኙ የቤተክርስቲያኒቱ አጥባቂ ተከታዮች ቤተክርስቲያኒቱ በዚህኛውም ዘመን ጠቃሚ ልትኾን እንደምትችል እያስመሰከሩ ነው።
ወደ እኛ አገር የእምነት ተቁዋማት ስንመጣ እንደሌላው የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ የእምነት ተቁዋማትም ከዘመኑ ጋር የመራመድን ነገር አስበውት የሚያውቁ አይመስሉም። ይህ የፖፕ ፍራንሲስ እና የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ርምጃ እንዴት እንደሚታይ መገመት አይከብድም። መቀለድ ቀርቶ በዓደባባይ ፈገግ ማለት ከመንፈሳዊነት እንደመራቅ በሚቆጠርበት አገር ከጳጳሱ ጋር መቀለድ ራሱ የማይታሰብ ቀልድ ነው።