• ነጋዴዎች እቃቸውን እያሸሹ ነው፡፡
  • መርካቶ በዋጋ ተመን መዋዠቅ ግራ ተጋብታለች፡፡

ዋዜማ ራዲዮ-ከትናንት በስቲያ የተደረገውን የውጭ ምንዛሬ ተመን ማስተካከያ ተከትሎ በማግስቱ የጀመረ የዕቃ አቅርቦት ችግርና የዋጋ መዋዠቅ በመዲናዋ በተለይም በመርካቶ በስፋት እየተስተዋለ ነው፡፡ በርካታ አስመጪዎች እጃቸው ላይ የሚገኙ እቃዎቻቸን እንዲሁም በችርቻሮ ሱቆች ለገበያ ያቀረቧቸውን ቁሳቁሶች መልሰው ወደ መጋዘን በማጎር ላይ እንደሚገኙ የዋዜማ ዘጋቢዎች በተዘዋወሩባቸው የገበያ ማእከላት ሸማቾችንና ቸርቻሪዎችን በመጠየቅ ለመረዳት ችለዋል፡፡
በአንጻሩ ሸማቾች ዋጋ አለቅጥ ሊንር ይችላል በሚል የዋጋ ማስተካከያው እንዳይነካቸው አላቂ እቃዎችን በገፍ ሲገዙ ተመልክተናል፡፡
‹‹አሁን እያየሁት ያለው ችግር የዋጋ መናር ብቻ ሳይሆን ግራ መጋባትም ጭምር ነው፡፡›› ያለን አንድ አስተያየት ሰጪ ‹‹ነገሩ እስኪለይለት በሚል በደፈናው እቃ ማሸሽ ተጀምሯል›› ይላል፡፡
‹‹ማተሚያ ቤቶች ለምሳሌ የኅትመት ዋጋ ተመን መስጠት አቁመዋል፤ ምክንያታቸውን ሲጠየቁ ወረቀት የለንም የሚል ነው፡፡ እውነታው ግን ስቶክ ያላቸውን ወረቀት በመደበቅ፣ አጋጣሚው የፈጠረላቸውን ሦስት እጥፍ ለማትረፍ ነው›› ይላል ብሔራዊ አካባቢ በአጋዥ መጻሕፍት ኅትመት ላይ የሚተዳደር ጎልማሳ፡፡
ዛሬ ረፋድ ላይ መገናኛ ዘፍመሽ ሞል ሥር የሚገኘውን የሸዋ ሀይፐር-ማርኬት የጎበኘቸው ዘጋቢያችን ፓስታ፣ መኮሮኒ፣ ሩዝ እና ዱቄት ማግኘት እንዳልቻለች ተናግራለች፡፡ ‹‹ሰሞኑን ገዝቻለሁ፣ ይመጣል በኋላ ተመለሺ ነው ያሉኝ›› ትላለች፡፡ የሸዋ ሱፐር ማርኬት የሽያጭ ሠራተኛ በበኩሏ ለዘጋቢያችን እንደተናገረችው ‹‹ዋጋ ለውጥ አላደረግንም››፤ ከትናንት ማታ ጀምሮ ግን ብዙ ሰዎች ብዙ ብዙ እቃ እየገዙ ነበር፡፡ መደርደሪያውን ባዶ ያደረጉት እነሱ ናቸው›› ብላለች፡፡
ዘጋቢዎቻችን በተዘዋወሩባቸው የአትክልት ተራ ገበያዎች ከዶላር ዋጋ ተመን ጋር ቀጥተኛ ተያያዥነት በሌላቸው አስቤዛዎች ላይ የዋጋ ልዩነት መስተዋሉን ለመረዳት ችለናል፡፡ ቀደም ሲል በኪሎ 15 ብር ሲሸጥ የነበረ ቲማቲም በቀናት ውስጥ 24 ብር ገብቷል፡፡ ሽንኩርት 9 ብር ከ50 በኪሎ ሲሸጥ የቆየ ቢሆንም ዛሬ በ16ብር ሲሸጥ ተስተውሏል፡፡ አንዳንድ ያነጋገርናቸው ነጋዴዎች ጭማሪው ከዶላሩ ወሬ በፊትም የነበረ ነው ብለውናል፡፡
የጥቅምት ወር የቤንዚል ዋጋ ባለበት እንደሚቀጥል በመገናኛ ብዙኃን ቀደም ብሎ የተገለጸ ቢሆንም በአዲስ አበባ ዛሬ ረፋድ ላይ እንዲሁም ትናንት አመሻሽ ላይ ዘለግ ያሉ የተሸከርካሪ ሰልፎች ታይተዋል፡፡ ይህም በዶላር ጭማሪው ምክንያት ዋጋ ሊጨምር ይችላል ከሚል መነሻ እንደሆነ ለመረዳት ችለናል፡፡ ኾኖም ለም ሆቴል በሚገኝ ማደያ ሰልፍ በመርዘሙ ነዳጅ ቀጂዎች እስከ ጥቅምት 30 ጭማሪ እንደሌለ በመንገር ሾፌሮችን ሲያረጋጉ ተመልክተናል፡፡
ከዚሁ የዋጋ መዋዠቅ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ድርጅቶች ዋጋ ማቅረቢያ ፕሮፎርማ ለመሙላት ፍቃደኛ እንዳልሆኑ ማስተዋል ችለናል፡፡ በ4ኪሎ አካባቢ የሚገኙ የስቴሽነሪ እቃ አቅራቢዎች በዶላሩ ምክንያት የዋጋ ለውጥ ስለሚኖር በሚል ‹‹ለጊዜው ዋጋ አንሰጥም›› በማለት ደንበኞቻቸውን እየመለሱ ነበር፡፡
የዋጋ ጭማሪ በቤትና የቢሮ እቃዎች ላይ የተስተዋለ ሲሆን አገር ውስጥ በሚፈበረኩ እቃዎች ላይ ነጋዴዎች የመሰላቸውን ዋጋ ጨምረው እየሸጡ ይገኛሉ፡፡ ‹‹38ሺ ብር ዋጋ ተለጥፎበት ከባለቤቴ ጋር ዘፍመሽ ላይ የተመለከትኩት ሶፋ በአንድ ጊዜ 44ሺ ብር ደርሶ ጠበቀኝ›› ያሉ ወይዘሮ ነገሩ ከዶላር ምንዛሬ ለውጥ ጋር ይገናኝ አይገናኝ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ለዘጋቢያችን ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ የግንባታ እቃዎች ዋጋ በፍጥነት እየናረ ሲሆን ብረት በዓለም ገበያ የ40 ዶላር ቅናሽ እያሳየ ባለበት በዚህ ወቅት የቱርክም ሆነ የአገር ውስጥ ብረቶች ዋጋ አስደንጋጭ ጭማሪን አስተናግደዋል፡፡ በተዘዋወርንባቸው የመገናኛና ተክለኃይማኖት የብረት ገበያ የአገር ውስጥ ባለ 8 ሚሜ ብረት አንድ ቤርጋ 150 እየተሸጠ ነው፡፡ ከቀናት በፊት ዋጋው በቤርጋ 90 ብር የነበረ ሲሆን የ60 ብር ጭማሪን አሳይቷል፡፡ በተመሳሳይ ባለ 16 ሚሜ ቤርጋ ብረት ከቀናት በፊት 430 ብር ሲሸጥ ቆይቶ በአንድ ቀን ልዩነት የ70 ብር ጭማሪን አሳይቷል፡፡ በሁሉም የአገር ውስጥ የብረት ዋጋ ላይ ከ80 እስከ 120 ብር ጭማሪ መታየቱ በአስገንቢዎችና ኮንትራክተሮች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል፡፡ ቆርቆሮ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎች አብዛኛዎቹ ምርት ያቆሙ ሲሆን የቸርቻሮ ሱቆችም ቢሆን ዋጋ ጨምሮ ከመሸጥ ይልቅ ‹‹የለንም›› ማለትን መርጠዋል፡፡
‹‹ምን መሰለህ! በቀናት ውስጥ በጣም ዋጋ ይጨምራል፤ አትጠራጠር፤ ያኔ በደንብ አትርፈህ መሸጥ እየቻልክ ለምን አሁን ከሰው ጋር ትጨቃጨቃለህ›› የሚለው ሲኒማ ራስ አቅራቢያ የሚገኝ የሕንጻ መሳሪያ መሸጫ ባለቤት፣ ‹‹ነጋዴ እስከሆንኩ ድረስ ይህን አጋጣሚ መጠቀሜ የግድ ነው›› ይላል፡፡ እንደሱ አመለካከት ከዚህ በኋላ ዋጋ በፍጹም ሊረጋጋ አይችልም፡፡ ይህን ሲያስረዳም በፍጹም እርግጠኛነት ሆኖ ነው፡፡ ‹‹ኤል-ሲ ለመክፈት የትኛውም ባንክ አንድ ዓመት ወረፋ ትጠብቃለህ፤ ፋብሪካዎች ጥሬ እቃ ስለማያገኙ ምርት ቶሎ ቶሎ አያደርሱም፤ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው ዋጋ ይቀንሳል ብለህ የምታስበው?››ሲል ይጠይቃል፡፡
ከሕንጻ መሳሪያ እቃዎች በተለምዶ አጠራሩ የአናጢ ሽቦ ከትናንት በስቲያ 30 ብር ሲሸጥ እንደነበረና በዛሬ ገበያ ከ45 እስከ 50 ብር ለውጥ ሲሸጥ እንደዋለ ያነጋገርናቸው ተጠቃሚዎች ገልጸዋል፡፡ ‹‹እቃው መጨመሩ አይደለም የሚገርመው፣ ብዙዎቹ ለመሸጥ ፍቃደኛ አይደሉም፡፡ እቃውን እያየኸው የለም ይሉሀል›› ይላል ከኮንተራክተሮች ‹‹ሰብ ኮንትራት›› በመውሰድ በአስገንቢነት የሚተዳደር ጎልማሳ፡፡
‹‹መጪው ጊዜ ለሕዝብም ለመንግሥትም ፈታኝ የሚሆን ይመስለኛል›› የሚለው በዛግዌ ቅርንጫፍ የንግድ ባንክ የተፈራ ደግፌ የሕግ አማካሪና ነገረ ፈጅ ‹‹መንግሥት ተመጣጣኝ የደመወዝ ማስተካከያ ካላደረገ አንገቱ ውስጥ የጠለቀውን ሸምቀቆ በራሱ እጅ እያጠበቀ ይመስለኛል፡፡›› ሲል የወቅቱን ነባራዊ ሁኔታ ይገልጻል፡፡