ዋዜማ- በደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ህዘቦች ክልላዊ መንግሥት ሥር በሚገኙ ስድስት ዞኖች ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ እና አምስት ልዩ ወረዳዎች ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮ፣ ዲራሼ የህዝበ ውሳኔ ድምጽ ለመስጠት  የተመዘገቡ 3,028,770 ዜጎች ትናንት ጥር  29 ቀን 2015 ዓ.ም ድምጻቸውን ሲሰጡ ውለዋል፡፡ የድምፅ ቆጠራ እየተካሄደ ነው።

በምርጫው እለት የምርጫውን እንቅስቃሴና አጠቃላይ ድባብ  በጋሞ ዞን እንዲሁም ጌዲዮና ወላይታ ዞኖች ዋዜማ ተንቀሳቅሳ ለመታዘብ እንደቻለችው ከማለዳው 12 ሰዓት መራጮች ድምጽ መስጠት የጀመሩ ሲሆን እሰከ ቀኑ አጋማሽ ድረስ በአብዛኛዎቹ የምርጫ ጣቢያዎች የታየው የመራጮች ቁጥር አነስ ብሎ ታይቷል።  

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ዋና ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዲቅሳ የድምጽ መስጫ ሰአት መጠናቀቁን ተከትሎ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አጠቃላይ ድምጽ ለመስጠት የወጣው መራጭ ህዝብ ቁጥሩ በይፋ ባይታወቅም አብዛኛው ህዝብ ወጥቶ እንደመረጠና ጥሩ የሆነ ተሳትፎ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

በተመለከትናቸው አብዛኞቹ ጣቢያዎች  ምርጫ  ታዛቢዎች የነበሩ ሲሆን በተወሰኑ ጣቢያዎች በተለይም ዋዜማ በተንቀሳቀሰችበት ሰዓት ያለምንም ታዛቢ ምርጫዎች ሲካሄዱ ተመልክተናል፡፡ 

የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዲቅሳ  ከዚህ  ጋር በተገናኘ ከጋዜጠኖች ለተነሳላቸው ጥያቄ ሲመልሱ በአንዳንድ ምክንያት በአጋጣሚ በአንድ ምርጫ ጣቢያ በሆነ ሰዓት በቦታው  ታዘቢ የለም ማለት ሙሉ ቀኑን ታዛቢ የለም ማለት አለመሆኑን ነገር ግን በየመሃሉ የቦርዱ ተቆጣጣሪዎች እየተንቀሳቀሱ ሲመለከቱ እንደነበር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ በጋሞ፣ወላይታ እንዲሁም ጌዲዮ ዞኖች ምርጫውን ሲታዘቡ ተስተውሏል፡፡

የኢትዮጵያ የሲቪል ማህበራት ድርጅቶች ኅብረት ለምርጫ፤ የተሰኘ ጥምረት ህዝበ-ውሳኔ ከሚካሄድባቸው ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች 434 ተቀማጭ እና 76 ተንቀሳቃሽ ታዛቢዎችን ማሰማራቱን አስታውቋል፡፡

ህብረቱ በመግለጫው እንዳስታወቀው ከድምጽ አሰጣጡ ጋር በተገናኘ የትዝብት ሪፖርት ከላኩ 413 ታዛቢዎች መካከል 363 ታዛቢዎች (88%) የድምጽ አሰጣጥ ሂደቱ ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት እስከ ረፋዱ 3፡00 ባለው ግዜ ውስጥ መጀመሩን፤ ነገር ግን 50 (12%) የድምፅ መስጫ ጣቢያዎች ከጠዋቱ 12፡00 ሰዓት በፊት ድምፅ መሰጠት መጀመራቸውን በትዝብቱ ጠቅሷል።

በተጨማሪም ኅብረቱ ወደ 13 የሚደርሱ ከምርጫ ሕጉ እና መመሪያዎች የተቃረኑ “አሳሳቢ”ሁነቶች በአማሮ፣ ጋሞ፣ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች ሪፖርት የተደረገለት መሆኑን አስታውቋል፡፡

“አሳሳቢ” በሚል ያወጣቸውና ከተከሰቱት ችግሮች መካካል በተወሰኑ ቦታዎች የጎደሉ የድምጽ መስጫ ቁሳቁሶች በተለይም የዕርቅ እና ውጤት ማመሳከሪያ ቅጽ አለመመልከታቸውን፣ ያልተፈቀደላቸው ግለሰቦች በድምጽ መስጫ ጣቢያዎች ገብተው መቆታቸውን እንዲሁም አንድ የድምጽ መስጫ ጣቢያ በህግ ባልተፈቀደ ቦታ ተከፍቶ መገኘቱ የሚሉት ይገኙበታል፡፡

የቦርዱ ሰብሳቢ የተከሰቱ ችግሮችን አስመልክተው ሲያብራሩ  የማህተም መርገጫ በ3 ጣቢያዎች፣ የመራጭነት ማረጋገጫ ቀለም በ3 የምርጫ ጣቢያ፤ የአሻራ መርገጫ በአንድ ጣቢያ፤ የማሸጊያ መመዝገቢያና ቃለ ጉባኤ መመዝገቢያ ቅጾች በ2 ጣቢያዎች፤ ማመሳከሪያና ውጤት ማሳወቂያ እጥረት ገጥሞ እንደነበር ተነግረዋል ፡፡  

ይሁን አንጂ እጥረት ላጋጠማቸው ጣቢያዎች የምርጫ ማስፈጸሚያ መሳሪያዎች ከማስተባበሪያ ማዕከሎች መጠባበቂያ በመውሰድ መፍታት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል  ለአካለ መጠን ያልደረሱ  ዜጎች  በመራጭነት ተመዝገበው መገኘት፣በአስተዳር አካላት የተፈጸሙ የህግ ጥሰቶች በተለይም የመታወቂያ ወረቀት ሲያድሉ የተገኙ ስለመኖራቸው ብርቱካን ገልፀዋል፡፡ 

የህዝበ ውሳኔውን በተመለከተ ዋዜማ ያነጋገራቸው የመንግስት ሰራተኛ በዛብህ በርዜ ‹‹ይህ ተስፋ የምናደርገበት አዲስ ክልል መመስረት የምንመኘውን የመልካም አስተደዳር፣የሰላምና ፍትሃዊነት ችግር መፍትሄ ያመጣልናል ብለን እናስባለን ›› ብለዋል፡፡

‹‹አርባ ምንጭ ከተማ ላይ ከዩንቨርሰቲ ተመርቀው ስራ ያጡትን ስመለከት በጣም ብዙ ናቸው፤ አሁን 12ኛ ክፍል ነኝ ፤ እኔም ዩንቨርስቲ ገብቸ ስወጣ ተመሳሳይ እድል እንዳይገጥመኝ በሚልና የሚመሰረተው ክልል የተሻለ እድል ይፈጥራል በሚል ካርድ አውጥቸ ለመምረጥ ነው የተነሳሳሁት›› ያለው የ12ኛ ክፍል ተማሪና የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪ ሚኪሎል ያለውነው፡፡ 

ይህ የህዝበ ውሳኔ የዲሞክራሲ ስርዓተን መሰረት አድርጎ በሚቀርብ ጥያቄ ጠይቆ መልስ የሚያገኝበት አሰራር መኖሩን ያሳየ ሂደት መሆኑን የገለጹት የደቡብ ክልል ብልጽግና ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ ናቸው ፡፡ 

የህዝበ ውሳኔው ውጤት በቀጣይ አምስት ቀናት ከማስተባበሪያ ማእከላት ተስብስቦ ወደ ምርጫ ቦርድ ሲገባ ውጤቱ ይፋ እንደሚደረግ የቦርዱ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዲቅሳ ተናግረዋል፡፡ [ዋዜማ]