• በውዝግብ የተሞላው አዲስ አደረጃጀት ቀጣዩ የሀገሪቱ የግጭት ቀጠና እንዳይሆን ከወዲሁ ስጋት አለ

ዋዜማ- ዛሬ ነሃሴ 13፣ 2015 ዓ፣ም የነባሩ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ሕልውና በይፋ አክትሞ፣ ደቡብ ኢትዮጵያ እና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ በተሰኙ ኹለት ክልሎች ተተክቷል።

የወላይታ፣ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ጌዲዖ እና ደቡብ ኦሞ ዞኖች እንዲኹም ቡርጂ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ አሌ እና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ባለፈው የካቲትና ሰኔ ወር ላይ ባካሄዷቸው ሕዝበ ውሳኔዎች መሠረት፣ ዛሬ የአዲሱ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምስረታ ሂደት በይፋ ተጠናቋል። ክልሉ የስድስቱን ዞኖች ማዕከሎች እኩል ማዕከሎቹ እንዲኾኑ የወሰነ ሲኾን፣ የጋሞዋ አርባምንጭ የምክር ቤቱ እንዲኹም ወላይታ ሶዶ የርዕሰ መስተዳድሩ ጽሕፈት ቤት መቀመጫ እንዲኾኑ ወስኗል። ሌሎች አስፈጻሚ ቢሮዎችና ተቋማት፣ ቀሪዎቹን ከተሞች መቀመጫቸው እንዲያደርጉ ተደልድለዋል።

በዛሬው ዕለት አርባምንጭ ላይ የመጀመሪያ ጉባዔውን ያካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ብቸኛ ዕጩ ኾነው የቀረቡትን ጥላሁን ከበደን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መርጧል። ጥላሁን፣ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኾነው እስከተመረጡበት ዕለት ድረስ፣ በቀድሞው ደቡብ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ሃላፊ እና ከዚያ ቀደም ሲል ደሞ በደቡብ ክልል የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኾነው አገልግለዋል። ምክር ቤቱ በተመሳሳይ ጸሃይ ወራሳን አፈ ጉባዔው አድርጎ መርጧል። ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን በዕለቱ፣ ከፊል የክልሉ መንግሥት ካቢኔ አባላትን ለምክር ቤቱ በዕጩነት አቅርበው አጸድቀዋል።

ምክር ቤቱ፣ በአዲሱ ክልል የውስጥ አስተዳደራዊ መዋቅሮችም ላይ ለውጥ አድርጓል። ከክልሉ መስራቾች መካከል የኾኑት አምስቱ ልዩ ወረዳዎች ማለትም ቡርጂ፣ አማሮ፣ ባስኬቶ፣ ደራሼ እና አሌ እያንዳንዳቸው በዞን አስተዳደርነት እንዲዋቀሩ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል። ከክልሉ መስራቾች መካከል የኾነውና ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው ደቡብ ኦሞ ዞን ደሞ፣ በኹለት ዞኖች ተከፍሎ እንደገና እንዲዋቀር ተወስኗል።

በዚህ መሠረት፣ ማሌ፣ ሐመር፣ በና ጸማይ፣ ሰላማጎ፣ ኛንጋቶም እና ዳሰነች ወረዳዎች ከቱርሚ ከተማ አስተዳደር ጋር ባንድ ላይ አንድ የዞን አስተዳደር፤ ደቡብ አሪ፣ ወባ አሪ፣ ባካ ዳውላ እና ሰሜን አሪ ወረዳዎች ደሞ ከጂንካ እና ከገሊላ ከተማ አስተዳደሮች ጋር በጋራ ሌላ ዞን ያዋቅራሉ። ምክር ቤቱ፣ በኮንሶ ዞን ስር ኮልሜ የተባለ አዲስ ወረዳ እንዲደራጅም ወስኗል። ምክር ቤቱ የአስተዳደራዊ መዋቅር ማሻሻያ ያደረገው፣ ሲንከባለሉ የቆዩ የመዋቅርና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን በተወሰነ ደረጃ የመለሰ ኾኗል። ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለጊዜው አዲስ ልዩ ወረዳ አላዋቀረም። ሌሎቹ የክልሉ መስራች ዞኖች በያዙት መዋቅር ይቀጥላሉ።

ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ነባሩን ደቡብ ክልል መልሶ በማደራጀት፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ከምባታ ጠምባሮ፣ ሃዲያና ሃላባ ዞኖችን እንዲኹም የም ልዩ ወረዳን በማካተት ያለ ሕዝበ ውሳኔ ተቋቋሟል። አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ዛሬ ወልቂጤ ከተማ ላይ ባደረገው የመጀመሪያ ጉባዔው፣ እንደሻው ጣሰውን በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አድርጎ መርጧል። እንደሻው ቀደም ሲል የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነርና የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት ምክትል ዳይሬክተር ነበሩ። ምክር ቤቱ በተመሳሳይ የቀድሞው ደቡብ ክልል አፈ ጉባዔ የነበሩትን ፋጤ ሰርመሎን አፈ ጉባዔ አድርጎ መርጧል። አዲሱ ርዕሰ መስተዳድር ከፊል የክልሉ ካቢኔ አባላትንም ለምክር ቤቱ በዕጩነት አቅርበው አጸድቀዋል።

ክልሉ የመስራች ዞኖቹን ማዕከላት እኩል ማዕከሎቹ ኾነው እንዲያገለግሉ ቀደም ሲል የወሰነ ሲኾን፣ የሃዲያዋ ሆሳዕና የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር መቀመጫ እንዲኹም የጉራጌዋ ወልቂጤ የክልሉ ምክር ቤት መቀመጫ ይኾናሉ ተብሏል። ሌሎች የክልሉ አስፈጻሚ ቢሮዎች ቀሪዎቹን ከተሞች መቀመጫቸው ያደርጋሉ። የቢሮዎች ድልድል ግን፣ ከአኹኑ የፍትሃዊነት ጥያቄ ተነስቶበታል። አንዱ የፍትሃዊ ድልድል ጥያቄ ባለፉት ቀናት ያነሳው፣ ከምባታ ጠምባሮ ዞን ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት የአስተዳደራዊ መዋቅር ለውጦችንም አድርጓል። በዚህም፣ ምሥራቅ ጉራጌ ዞን የተሰኘ አዲስ የዞን መዋቅር ከነባሩ ጉራጌ ዞን ተነጥሎ እንዲዋቀር ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ወስኗል። አኹን በምሥራቅ ጉራጌ ዞን ስር የሚደራጁት ወረዳዎች፣ ከጉራጌ ዞን ተነጥለው አዲስ የዞን አስተዳደራዊ መዋቅር ለማቋቋም እንዲፈቀድላቸው ለረጅም ጊዜያት ሲጠይቁ መቆየታቸው ይታወሳል።

የጉራጌ ዞን ምክር ቤት ጉራጌ ዞን ራሱን የቻለ ክልል ኾኖ እንዲዋቀር በሙሉ ድምጽ ሲወስን፣ የ”ምሥራቅ ጉራጌ” ዞን መዋቅር ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩት የተወሰኑ ወረዳዎችና የከተማ አስተዳደሮች ግን ያኔ ገና ባልተደራጀው “ማዕከላዊ ኢትዮጵያ” ክልል ስር ለመዋቀር በተናጥል ውሳኔ ማሳለፋቸው ይታወሳል።

ምክር ቤቱ፣ የቀድሞዎቹ የጉራጌ ዞን ወረዳዎች ቀቤና እና ማረቆ፣ ልዩ ወረዳዎች ኾነው እንዲዋቀሩም ወስኖላቸዋል። በተመሳሳይ፣ በቀድሞው ደቡብ ክልል ስር ለረጅም ዓመታት ልዩ ወረዳ ኾኖ የቆየው የም ልዩ ወረዳ፣ በዞን ደረጃ እንዲዋቀር እንዲኹም በከምባታ ጠምባሮ ዞን ስር የነበረው ጠምባሮ ወረዳ ልዩ ወረዳ ኾኖ እንዲዋቀር ተወስኗል። የልዩ ወረዳ አስተዳደራዊ መዋቅሮቹ ቀጥታ ግንኙነታቸው የሚኾነው፣ ከክልሉ ምክር ቤት ጋር ነው። እናም ይሄ መዋቅራዊ ለውጥ፣ ከምባታ ጠምባሮ ተብሎ የሚጠራው ዞን ከምባታ ዞን ብቻ እንዲኾን የሚያደርግ ነው። ማረቆ እና ቀቤና ወረዳዎች ልዩ ወረዳ ኾነው መዋቀራቸውም፣ የጉራጌ ዞን አስተዳደራዊ ወሰን እንዲጠብና የታች አስተዳደራዊ እርከኖቹም እንዲቀንሱ ያደርጋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የከተማ ማዕከላት፣ የርዕሰ መስተዳድር፣ የምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የምክር ቤት አፈ ጉባዔ፣ የምክትል አፈ ጉባዔ እና ሌሎች የካቢኔ ሹመቶች አመራረጣቸው፣ የክልሎቹን የብሄረሰብ ብዝሃነት፣ ፍትሃዊ ውክልናንና እኩል የማደግ መብትን በመስፈርትነት ለመጠቀም የሞከሩ ይመስላል።

ዋዜማ ያነጋገረቻቸውና በክልል አወቃቀሩ ጥናት ላይ የተሳተፉ ባለሙያዎችና የግጭት ጥናት ተመራማሪዎች አሁን የተደረገው የክልል አወቃቀር አንዳንድ የህዝቡን ጥያቄዎች ለመመለስ ያለመ ቢሆንም ውስብስብ የወሰን፣ የሀብትና የስልጣን ፍላጎቶች ያሉት በመሆኑ ወደግጭት የማምራቱ ጉዳይ አይቀሬ ነው ብለው ያምናሉ።አደጋውን ከወዲሁ በመንገንዘብ መንግስት የቅድመ ግጭት አፈታት ዝግጅት ማድረግ እንዳለበትም ይመክራሉ።

መንግስት ከሞላ ጎደል ሊመጣ በሚችለው አደጋ ዙሪያ ግንዛቤ እንዳለው የነገሩን ምንጫችን የአዳዲስ ክልሎች ምስረታን መከልከል የማይቻልበት ደረጃ በመደረሱ መንግስት የተሰላ ሀላፊነት ወስዷል ብለዋል። እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ ያላገኙ ከኣአስር በላይ የክልልነት እንዲሁም ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ባለሙያዎቹ ለክልሉ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት የማይቻልበት ደረጃ ተደርሷል ይላሉ።[ዋዜማ]