musevini
  • ለጋሾች ድጋፍ አቁመዋል
ዋዜማ ራዲዮ- የደቡብ ሱዳንን ተፋላሚዎች  በማደራደር ጉዳይ ዩጋንዳና ኢትዮጵያ አዲስ ፍጥጫ ውስጥ ናቸው። ዩጋንዳ በተናጠል የደቡብ ሱዳን የፖለቲካ ሀይሎችን በካምፓላ ስብስባ ማወያየት ጀምራለች። ኢትዮጵያ በበኩሏ በምስራቅ አፍሪቃ የብየነ መንግስታት ማህበር (ኢጋድ) በኩል የተቋረጠው ድርድር እንደገና እንዲጀመር እያግባባች ነው።
ባለፈው ሳምንት የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በካምፓላ የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት ሳልቫ ኪርን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ወገኖች የተካፈሉበትን የሁለት ቀናት ውይይት አድርገዋል። በውይይቱም በደቡብ ሱዳን ተቀናቃኝ ወገኖች መሀከል በጋራ መስራት የሚያስችል የጋራ ዕቅድ ወጥቶ ሀገሪቱን ወደ ስላም መንገድ መመለስ የሚቻልበትን መንገድ መክረዋል።
በሁለት ቀናት ልዩነት የምስራቅ አፍሪቃ ብየነ መንግስታት ማህበር (ኢጋድ) በጁባ ጉባዔ ጠርቷል። ኢትዮጵያ በሊቀመንበርነት የምትመራው ኢጋድ ከዚህ ቀደም የመከነው የሰላም ስምምነትን የሚተካ አዲስ የሰላም ድርድር የሚደረግበትን መንገድ ተነጋግሯል። የኢጋድ አባል የሆነችው ዩጋንዳ በተናጠል ከደቡብ ሱዳን ፖለቲከኞች ጋር ያደረገችውን ውይይት ይዛ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያና  በኬንያ አደራዳሪነት ሲካሄድ የነበረውን መረከብ ትፈልጋለች።
የዩጋንዳ እርምጃ በኢትዮጵያ ላይ እምነት እያጡ ከመጡት ከደቡብ ሱዳን መሪ ሳልቫ ኪር በኩልም ድጋፍ አለው። ዩጋንዳ የምስራቅ አፍሪቃ ቁልፍ ሀይል ሆና ለመውጣት ያላት ፍላጎት በአመዛኙ ተቀናቃኟን ኢትዮጵያን በመገዳደር ላይ ያነጣጠረ መሆኑን ለመረዳት ያለፉት አመታት ክስተቶችን ማስታወስ ይቻላል። በሶማሊያ ሁለቱ ሀገሮች በአፍሪቃ ስላም ማስከበር ተልዕኮ AMISOM ውስጥ ወሳኝ ድርሻ ለመውሰድ ያላቸው ፉክክር የአደባባይ ሀቅ ነው።
ዩጋንዳ በአባይ ውሀ ጉዳይ ከግብፅ ጋር ሽር ጉድ ማለቷም ዋና ኢላማው ኢትዮጵያ ለዩጋንዳ ጆሮ እንድትሰጥ መልዕክት ማሰተላለፍ ነበር። ይብስ ብሎም ግብፅና ደቡብ ሱዳንን በማሞዳሞድ ዩጋንዳ ምን ማድረግ እንደምትችልም ለማሳየት ስትሞክር ነበር።
በደቡብ ሱዳን የሰላም ድርድር ኢትዮጵያ ለአማፅያኑ መሪ ሪክ ማቻር ታደላለች ስትል ጁባ ትከሳለች። ዩጋንዳ በበኩሏ በስልጣን ላይ ያሉት የሳልቫ ኪር ዋና ደጋፊ ናት። ወታደሮች ልካ ፕሬዝዳንት ኪርን እስከመከላከል ደርሳለች።
የዩጋንዳና የኢትዮጵያ እያደገ የመጣ ፉክክር ለምስራቅ አፍሪቃ ውጥንቅጥ አዲስ ትኩሳት ይዞ መምጣቱ አይቀርም። ዩጋንዳ ኢትዮጵያን ሳያስቆጡ የልብን ማድረስ እንዴት እንደሚቻል እየተማመደች ይመስላል። ኢትዮጵያ በበኩሏ ለዩጋንዳ ሸብ-ረብ  “አይቶ እንዳላየ”  እውቅና መንፈጉን የመረጠች ይመስላል። የባህር በር የሌላቸውና በድንበር የማይዋሰኑት ሁለቱ ሀገሮች በየፊናቸው ከምዕራባውያን ጋር ወዳጅነት አላቸው።
በተያያዘ ዜና- የደቡብ ሱዳንን የሰላም ድርድር በገንዘብ ሲደግፉ የቆዩት አሜሪካ የአውሮፓ ህብረት እንግሊዝና ኖርዌይ ከዚህ በኋላ ድጋፍ ማድረግ እንደሚቸግራቸው በተሸኘው ሳምንት ተናግረዋል። ይህም ለሰላም ድርድሩ ሌላ ፈተና ነው። በእስካሁኑ የሰላም ድርድርም ሆነ የዛሬ ሁለት አመት በተፈረመው ስምምነት ተግባራዊነት ላይ ምንም ፈቅ ያለ ነገር ባለመኖሩ ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ገንዘብ ከማባከን ውጪ ትርጉም የለውም እንደ ለጋሾቹ አስተያየት።