ዋዜማ ራዲዮ- ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በበጀት አመቱ የመጨረሻው የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ተገኝተው በሰጡት ማብራሪያ ላይ በተለያየ ምክንያት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለሱ ስራ እጅግ አመርቂ ነው ብለው ነበር። ተፈናቅለው ከነበሩት መካከል 95 በመቶው ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን በማውሳት ለዚህም የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚልን በምክር ቤቱ ፊት ማመስገናቸው አይረሳም።

ዋዜማ ጉዳዩን አስመልክቶ ባሰባሰበችው መረጃ ግን ዛሬም ድረስ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ ያልቻሉ ተፈናቃዮች ቁጥር መንግስት እንደሚለው አምስት በመቶ ብቻ አይደለም። ከሁሉ በላይ ተፈናቃዮቹ ያሉበት ሁኔታ ለተለያዩ እንግልቶች ዳርጓቸዋል።

      የዋዜማ ሪፖርተር በሰበታ ከተማ አስተዳደር ደረቶ የተባለ ቦታ ላይ ያሉ ተፈናቃዮችን ያሉበትን መጠለያ ሁኔታ ጎብኝቷል።ይህ ስፍራ ከአዲስ አበባ ወጣ ብላ በምትገኘው ኬንቴሪ የተወሰኑ ኪሎ ሜትሮች ገባ ብሎ ያለ ሲሆን ; በሌላ አገላለጽም ከአይካ አዲስ ቴክስታይል ፋብሪካ ጀርባ ካለው ጋራ ደሎ ስር ካለው ጫካ አቅራቢያ ያለ ነው።

     ደረቶ በተባለው ስፍራ ያሉ ተፈናቃዮች ሁለት አመት ሊሞላው ጥቂት ቀናት በቀረው የኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ ዜጎች ያሉበት ነው። ቦታው ላይ ሰባ ሰባ ካሬ ሆነው በተሰሩ በርካታ የቆርቆሮ ቤቶች ውስጥም ነው ተፈናቃዮቹ እየኖሩ ያሉት። 1380 የሚሆኑ አባወራዎች የሚኖሩበትም መጠለያ ነው።1380 የአባወራ ቁጥር ብቻ ሲሆን ሚስት እና ልጆች ሲቆጠሩ በመጠለያው ያሉ ዜጎችን ቁጥር በእጅጉ ያንረዋል።

በመጠለያው የሚኖሩ ተፈናቃዮች እስካሁን ድረስ ወደ ቀያቸው የመመለሳቸው ነገር ተስፋ ያለው አይመስልም።ህይወታቸውንም እየገፉ ያሉት ከመንግስት በየወሩ በሚያገኙት የምግብ እርዳታና መሰል ድጋፎች መሆኑን ለመታዘብ ችለናል።

     በመጠለያው የጀበና ቡና ስትሸጥ ያገኘናት ሂክማ ኡመር ; አሁን እየሸጠች ያለችው የጀበና ቡና ዝም ብላ ከመቀመጥ ብላ መሆኑንና እሷንና ልጇን ለማኖር በቂ አለመሆኑን ትገልጻለች። ባለቤቷ ወደ ድሬዳዋና ሀረርጌ እንደሚመላለስም ታነሳለች። መንግስት በመጠለያ ውስጥ ላሉ ተፈናቃዮች ከሚያደርገው የምግብና የሌሎች ቁሳቁሶች እርዳታ በተጨማሪ ስራ ፈጥረው እንዲንቀሳቀሱ ሀያ ሀያ ሺህ ብር ሰጥቷል። ለባልና ሚስት ደግሞ በድምሩ አርባ ሺህ ብር ሰጥቷቸዋል። በዚህ ገንዘብ የተወሰኑ ተፈናቃዮች አነስተኛ ንግድ ነገር የጀማመሩ ሲሆን ቀላል የማይባሉት ገንዘቡን ተጠቅመው ጨርሰውታል ስትል ሂክማ ነግራናለች። ቀድማ ትኖርበት ከነበረበት አንጻር አሁን ባለችበት የተፈናቃዮች መጠለያ የስራ እንቅስቃሴ አለ ሊባል እንደማይችል ; እንዲሁም ትኖርበት ከነበረበት የምስራቁ አየር ጸባይ አንጻር የአሁኑ እንደማይስማማ አውርታናለች።

     አሁን ላይ በኦሮሚያና ሶማሌ ክልሎች የሚጠቀስ ግጭት የለም። ባላፉት ጊዜያት ነበሩ የተባሉ ችግሮችም የሉም ; በሶማሌ ክልልም የአመራር ለውጥ ከተደረገ ሰነባብቷል።ታዲያ ወደ ቀድሞ ቀዬአችሁ አትመለሱም ወይ ? የክልሉ አስተዳደርስ በዚህ ምን እያላቹ ነው ብለን ለሂክማ ላነሳንላት ጥያቄ ; የአካባቢው አስተዳደር አካላት አሁን በቆርቆሮ ያሉ ቤቶችን ወደ ግንብ እንቀይርላቹሀለን ብለውናል ትላለች።

 ሌላኛው በዚህ መጠለያ ከጅግጅጋ መጥቶ ከሁለቱ ክልሎች ግጭት መከሰት ጀምሮ መቆየቱን የነገረን ደግሞ አደም ነው። አደም ጅግጅጋ እያለ አናጺ እንደነበር እዚህ ከመጣ ደግሞ ሁለት አመት እንደሆነው ገልጾልን ; ወደ ተፈናቃዮች መጠለያ ከመጣ ግን በሙያው ምንም እየሰራ አለመሆኑንም ይናገራል። ከባለቤቱ በተጨማሪ ዘጠኝ ልጆቹን የሚያኖረው መንግስት በሚሰጠው እርዳታ ነው።ጅግጅጋ ይኖርበት የነበረውም የግል ቤቱን አሁን ላይ በየወሩ በ1500 ብር እያከራየው ገቢ እያገኘ መሆኑን ግን ገልጾልናል። ከባለቤቱ ጋር በድምሩ አርባ ሺህ ብር ለስራ ፈጠራ ተብሎ እንደተሰጠው አውርቶናል። ቀድሞ ይኖርበት የነበረበት አካባቢ ላይ ደርሶ ከነበረው ችግን አንጻር መጥፎ ትውስታ ስላለት አሁን መመለስ እንደሚፈራ ግን አልሸሸገም።

     አሁን ላይ በኦሮሞና ሶማሌ ክልል የሚሰማ ችግር ባይኖርም የክልሉ መንግስት በዚህ በደረቶ የመጠለያ ጣብያ እና በሌሎች አስር የክልሉ ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ የመጠለያ ጣብያ ውስጥ ያሉ ከሶማሌ ክልል ጋር ተፈጥሮ በነበረ ችግር የተፈናቀሉ ዜጎችን የመመለስ ፍላጎት ያለው አይመስልም። ይህ መሆኑ በመጠለያ ጣብያዎቹ የማህበራዊ ቀውስ ምልክቶች እንዲታዩ ማድረጉ አልቀረም።

በደረቶ መጠለያ ብቻ ያሉ በርካታ ወጣቶች ያለ ስራ ሁሉንም ጊዜያቸውን ያሳልፋሉ።በመጠለያው ከተወሰኑ የሸቀጥ ሱቆችና ጸጉር ቤቶች ውጭ የሚታይ የስራ እንቅስቃሴ የለም። የልመና እና ከዚህም ያለፈ ስራ ውስጥ የገቡ ተፈናቃዮች እንዳሉም ይሰማል። የተሰጣቸውን የእርዳታ እህል ለመሸጥ ገበያ የሚወጡ ሴቶች ቁጥርም ቀላል አደይለም። ለስፍራው በማይመች ሁኔታም የአርብቶ አደር አይነት ኑሮ ለመኖር የሚጥሩ ሰዎችንም ተመልክተናል። ዝርዝር የድምፅ ዘገባውን ከታች ይመልከቱ

https://youtu.be/g6SqvZ5Rwbs