NISSየሀገራችን የደህንነትና የስለላ መዋቅር የሀገር ጥቅምና ህልውና ከማስጠበቅ ይልቅ በስልጣን ላይ ያለውን ገዥ ቡድን የሚያገለግል መሳሪያ ሆኖ ቆይቷል፣ አሁንም አልተለወጠም። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ የስለላና የፀጥታ መዋቅሩን አፍርሰው ካልሰሩት በሀገሪቱ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት የመገንባት ህልም ብዙ ፈተና ይጠብቀዋል። ለመሆኑ የደህንነትና የስለላ መዋቅሩ ምን ይመስላል? [ዘርዘር ያለ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

ዋዜማ ራዲዮ- ከሰሞኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመተባበር በስለላ ሙያ በዲግሪ ፕሮግራም ሰልጣኞችን ማስመረቁን አሳውቋል፡፡ ተቋሙ በስለላ ሙያ በዲግሪ መርሃ ግብር አስተምሮ ሲያስመርቅ የመጀመሪያው ነው፡፡

የስለላ እና መረጃ ተቋምን ጨምሮ የጸጥታ ተቋማት አወቃቀርን ማሻሻል የአንድ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግር ዓይነተኛ ማሳያ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለላና መረጃ ሥራ ደሞ የማንኛውንም ሀገር ሕልውና ከቆመባቸው ቁልፍ ምሰሶዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ ጥያቄው ግን ይህንኑ ቁልፍ ሥራ የሚመራው ተቋም እና ተቋሙ የሚመራበት ፍልስፍና ባብዛኛው ከዴሞክራሲያዊ ሕገ መንግስታዊ መርሆዎች እና ከሕግ የበላይነት እሳቤ የሚቀዳ ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡

 በዚህ ረገድ ኢሕአዴግ -መራሹ መንግስት ለዐመታት በስለላ ተቋሙ ላይ የሕግ የበላይነትን እና ህብረ ብሄራዊ ስብጥርን የሚያሰፍን አወንታዊ ለውጥ አላደረገም፡፡ ተቋሙ በሀገር ውስጥ ከፖሊስ ባልተናነሰ ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን እና ጋዜጠኞችን በማዋከብና በማሳደድ ነው የደኅንነቱ ስሙ ተደጋግሞ የሚጠቀሰው፡፡ እንደ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ፌደራል ፖሊስ፣ መከላከያ ሠራዊት እና ጸረ ሙስና ያሉ ሕገ መንግሥታዊ ተቋማትን በሙሉ ቁጥጥሩ ቀፍድዶ ለያዘው ኢሕአዴግ ወደፊትም የደኅንነቱ ተቋም ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች እንዲመራ ማድረግ የመጨረሻዎች ሁሉ መጨረሻ አማራጭ ነው የሚሆነው፡፡ እናም ተቋሙን ከማዘመን አልፎ አንጻራዊ ተቋማዊ ነጻነቱን ጠብቆ ሀገራዊ ተቋም የማድረጉ ነገር በቀላሉ የሚሞከር አይደለም፡፡

 የጉለሌው ቢሮ

የሀገሪቱ ስለላ ተቋም በረጅሙ ጉዞው ጸጥታ መስሪያ ቤት፣ ሕዝብ ደኅንነት፣ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስቴር የሚሉ ስሞችን ሲቀያይር ከቆየ በኋላ በ1987ቱ ሕገ መንግስት ከጸደቀ በኋላ ደኅንነት፣ ኢምግሬሽንና ስደተኞች ባለስልጣን ተብሎ ተዋቅሮ ነበር፡፡ በምርጫ-97 ማግስት ደሞ ብሄራዊ መረጃ እና ደኅንነት አገልግሎት (National Intelligence and Security Service/NISS) ተብሎ እንደገና በአዋጅ ተቋቁሟል፡፡ ከአምስት ዐመት በፊት አዋጁ እንደገና ተሻሽሎለታል፡፡

 ተቋሙ መረጃ መሰብሰብና መተንተን፣ ኢላማዎችን በሰውና ቴክኒካዊ መሳሪያ መከታተል፣ በሽብር እና ሌሎች ወንጀሎች ላይ ስውር ኦፕሬሽናል ሥራዎችን ማከናወን፣ የበረራ እና ለከፍተኛ ባለስልጣናትና ለመንግስት የውጭ እንግዶች ጥበቃ ማድረግ፣ ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱ እንዳይፈርስ መጠበቅ፣ የበረራ ደኅንነትን ማረጋገጥ፣ የብሄራዊ ማንነት መታወቂያ ካርድ አሰጣጥን በበላይነት መቆጣጠር የመሳሰሉ ተግባራት በአዋጅ ተሰጥቶታል፡፡

 ተቋሙን በቅርብ የሚያውቁ ምንጮቻችን እንደሚሉት የስለላ ተቋሙ ዋና ምሰሶ የሀገር ውስጥ ጸረ-ስለላ ዘርፍን የሚመራው ዋና መምሪያ ሲሆን ለረጅም ዓመታት ጉለሌ አካባቢ ነው የሚገኘው፡፡ ይኸው ዋና መምሪያ ዋና ትኩረቱ የሀገሪቱን ብሄራዊ ደኅንነት፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞች እና ሕገ መንግስታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉ የውስጥና የውጭ ስጋቶችን እየተከታተለ መረጃ በመሰብሰብና በመተንተን ማክሸፍ ነው፡፡ ዋና መምሪያው አብዛኛውን የተቋሙን ሰው ሃይል የያዘ ሲሆን በተለይ አዲሳባ ብዙውን ይሸፍናል፡፡ የመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን፣ ህጋዊና ህገ ወጥ ተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችን፣ የእምነት ተቋማትን እና ሲቪክ ማህበራትን መከታተልም የዚሁ መምሪያ ሃላፊነት ነው፡፡

ዋና መምሪያው በክልሎችም ቅርንጫፍ ቢሮዎች ያሉት ሲሆን ለብዙ ዐመታት በክልልና ማዕከሉ መካከል ያለው የጥሬ መረጃ ልውውጥ ከሬዲዮ መገናኛ ወይም ኦፕሬተር ሳይወጣ ነው የኖረው፡፡ በስፋት ከሚንቀሳቀስባቸውና ከአንድ በላይ ቢሮዎች ካሉባቸው ክልሎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሱማሌ፣ ጋምቤላ እና ድሬዳዋ ግንባር ቀደሞቹ ናቸው፡፡

 ስለላ ወደ ቤት

የደኅንነት ተቋሙ በውጭ ሀገር የሚያደርገው ስለላ ግን ውስን እንደሆነ ነው ውስጥ አዋቂ ምንጮች የሚጠቁሙት፡፡ ለዚህም ሁለት ምክንያቶችን ነው የሚጠቅሱት፡፡ አንደኛው በአቶ መለስ ዜናዊ ጊዜ የተነደፈው የውጭ ጉዳይና ብሄራዊ ደኅንነት ፖሊሲ በባህሪው ወደ ውስጥ እንጅ ወደ ውጭ የማያይ መሆኑ ነው፡፡ ሌላኛው ደሞ ተቋሙ ብቁ የሰው ሃይል እጥረት ያለበት መሆኑ ነው፡፡ በሬዲዮና ስልክ ጠለፋ ተወስኖ የኖረው መምሪያ አሁን አሁን ወደ ዘመናዊ ቴክኖሎጅ መሸጋገሩ ግልጽ ሆኗል፡፡ በርግጥ ተቋሙ በዲፕሎማቲክ መብት ሽፋን ሰላዮቹን እንደ ሱማሊያ፣ ሱማሌላንድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጅቡቲ እና ኬንያ ባሉ ጎረቤት ሀገራት ሲያሰማራ መቆየቱን ውስጥ አዋቂዎች ይናገራሉ፡፡

የአሁኑ ስለላ ተቋም ከቀደምቶቹ ጋር ሲነጻጸር በቀዝቃዛው ዐለም ጦርነት ማክተም ሳቢያ ከውጭ ሀገር መንገስታት በቀጥታ የሚመነጭ የብሄራዊ ደኅንነት ስጋት ቀንሶለታል፡፡ መንግስታዊ ካልሆኑ ወንጀለኛና የሽብር ድርጅቶች የሚመጣው ስጋት ግን በዐይነትም ሆነ በመጠን በጣም ነው የጨመረው፡፡ መጠነ-ሰፊ ኮንትሮባንድ፣ ሙስና፣ ገንዘብ አጠባ (money laundering)፣ ድንበር-ዘለል ሽብር፣ ሐይማኖታዊ አክራሪነት፣ ሕገ ወጥ የገንዘብ ፍሰት፣ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀል፣ የበይነ-መረብ ወይም ኮምፒውተር ወንጀል ወዘተ በአፍሪካ ቀንድ ተበራክቷል፡፡

ትልቅ ሀገር ውስን አቅም

ያም ሆኖ የመንግስት ስለላ ተቋም መረጃ በመሰብሰብና መረጃን ተንትኖ ለፖሊሲ ግብዓት በማቅረብ ረገድ ውስን አቅም እንዳለው ነው በተቋሙ ያለፉ የሚገልጹት፡፡ ሃቁ ይህ ቢሆንም ላለፉት ዐመታት ሀገሪቱ በሱማሊያ አሸባሪ ድርጅቶች ጥቃት ሰለባ ባለመሆኗ ብቻ ግን ተቋሙ በጠቅላላው ገዝፎ መታየቱ አልቀረም፡፡ ዘላቂ ጆኦፖለቲካዊ አሰላለፎችን እና ብሄራዊ ጥቅሞችን ባግባቡ ተንትኖ ጠንካራ የብሄራዊ ደኅንነት እና ውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በማስወጣት ረገድ ግን እዚህ ግባ የሚባል አስተዋጽዖ እንዳላበከተ ከቅርብ ዐመታት ወዲህ በምስራቅ አፍሪካ ቀጠና ለታዩ ለውጦች ሀገሪቱን እና መንግስት ያሉበት አሳሳቢ ሁኔታ ምስክር ነው የሚሆነው፡፡

ተቋሙ በውጭ ሀገር ስለላ ረገድ ስሙ ተነሳ ከተባለ ከምዕራባዊያን ሀገራት እና እስራዔል በተገዙ የኮምፒውተር ቴክኖሎጅ ስለላ መሳሪያዎች አማካኝነት በውጭ ባሉ ተቃዋሚዎች እና መበት ተሟጋቾችን በመሰለል ወይም ከደቡብ ሱዳን እና ኬንያ አንዳንድ ተቃዋዎቹን እና መብት ተሟጋቾችን አፍኖ ይወስዳል እየተባለ በሂዩማን ራይትስ ዎች እና አምነስቲ ኢንተርናሽናል በሚቀርብበት ውንጀላ ነው፡፡

ከምዕራባዊያን ስለላ ድርጅቶች ጋር በስልጠና እና ቴክኒካዊ ድጋፍ የሚያደርገው ትብብር ግን በጣም ውስንና ጥንቃቄ የተሞላበትና ቁጥም እንደሆነ ነው የሚታመነው፡፡ የኮምፒውተር ስለላውም ቢሆን ባብዛኛው በቀጥታ ምዕራባዊያን መንግስታት ተሳትፎ የሚጸም ሳይሆን ከግል ወይም ከወታደራዊ ቴክኖሎጅ መሳሪያ አምራች ኩባንያዎች በሚገዙ መሳሪያዎች የሚከናወን እንደሆነ ነው ሲዘገብ የቆየ፡፡

 ሽኩቻና መዋቅራዊ መምታታት

ቀደም ሲል የደኅንነቱ ተቋም ከመከላከያ ሚንስቴር እና ፖሊስ ጋር ጥሩ ቅንጅት አልነበረውም፡፡ ውስጥ ለውስጥ ተቋማዊ ሽኩቻም ሰፍኖ ነበር፡፡ ይህንን በመረዳት ይመስላል የቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ ብሄራዊ ደኅንነት ምክር ቤት የተሰኘ አካል በማቋቋም ሦስቱንም የጸጥታ አካላት  ባንድ ላይ ያቀፉት፡፡ ከቅርብ ዐመታት ወዲህ ግን በተለይ መከላከያውና ደኅንነቱ ራሳቸውን የቻሉ የሥልጣን ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውን እና በህገ መንግስቱ የተቀመጠው ለሲቪል ፖለቲካ መሪዎች ተጠሪ የመሆኑ ነገር ጥያቄ ውስጥ መግባቱን እየሳሳ መምጣቱን ታዛቢዎች ሲገልጹ ይሰማሉ፡፡ ይህም ካለፉት ሁለት መንግስታት የተወረሰው ጥብቅ የሲቪሉ ሥራ አስፈጻሚ ቁጥጥር እየሳሳ እንደመጣ ሊጠቁም ይችላል፡፡ ይሄ አዝማሚያ ደሞ በመርህ ደረጃ ሲታይ ውስብስብ ተቋማዊ መጠላለፍ ብሎም ፖለቲካዊ ቀውስ ሲበረታ ለሀገር መበታተን በር ሊከፍት የሚችልበት ዕድል ዝግ አይደለም፡፡

ሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የስለላ ተቋም ያቋቋመችው በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግስት ጊዜ ሲሆን ከተቋሙ ቀደምት መስራቾችም ከ1953መፈንቅለ መንግስት መሪዎች አንዱ የነበረው ኮሎኔል ወርቅነህ ገበየሁ ይገኝበታል፡፡ የጥናት እና ምርምር ክፍል  ለመጀመሪያ ጊዜ የተቋቋመውም በወርቅነህ ዘመን እንደነበር አቶ ብርሃኑ አስረስ ባንድ ወቅት በሰጡት ቃለ ምልልስ ተቁመዋል፡፡ ባለሙያዎች ለሚንስትሮች እና ለጃንሆይ የጸጥታ እና ጅኦፖለቲካ ሁኔታዎች ማብራሪያ ይሰጡበት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ጸጥታ መስሪያ ቤት መባሉ ቀርቶ ሕዝብ ደኅንነት የተባለውም በዚሁ ጊዜ መሆኑን ጄኔራል ነጋ ተገኝ “የኢትዮጵያ ዘመናዊ ጦር አመሰራረት” በተሰኘው መጽሃፋቸው አስፍረውታል፡፡

ኢትዮጵያ ዘመናዊ፣ ጠንካራና ሕዝባዊ ወገንተኝነት ያለው የስለላና መረጃ ተቋም እንደሚያስፈልጋት አሌ የሚባል አይደለም፡፡ ዳሩ ግን የስለላ ተቋሟ በታሪኩ የሦስቱም መንግስታት ቀኝ እጅ ሆኖ ነው የኖረው፡፡ በዘመነ ኢህአዴግም በተልዕኮውና ሰው ሃይል ስብጥሩ ለሕገ መንግስቱ ብቻ ታማኝ የሆነ ሀገራዊ ተቋም ከመሆን ይልቅ ወገንተኛ ሆኖ ነው የቀጠለው፡፡ ምንም እንኳ በአዋጁ መሰረት ፓርላማው በቋሚ ኮሚቴው በኩል በተቋሙ አሰራር ላይ ቁጥጥር እንደሚያደርግ ቢጠቀስም በተግባር ግን ምንም የረባ ነገር ትንፍሽ ብሎ አያውቅም፡፡ ለዚህም ነው ከሕወሃት ወይም ብአዴን ታጋዮችና ካድሬዎች የተውጣጣው ነባሩ የሰው ሃይል እምብዛም ያልተቀየረው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደሞ ተቋሙ በሰው ሃይል ምልመላው ከብቃትና ሙያ ይልቅ ለገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ታማኝ መሆንን ዋና መመዘኛው በማድረጉ እንደሆነ ተደጋግሞ ይገለጻል፡፡ ባጭሩ ተቋሙ የአገዛዙን ወይንስ የሀገረ-መንግስቱን ህልውና በመጠበቅ ላይ ውልውል ውስጥ ሲገባ የታየበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላለ፡፡ በሕዝብ ዘንድም በጥቅሉ አፋኝ፣ ገራፊ እና ገዳይ እንጅ የሕዝብና ሀገር ደኅንነት ጠበቂ ተደርጎ አይታይም፡፡

ተቋሙ በ1990ዎቹ መጨረሻ ግድም ነባሩን አባል በስለላ ኪነ ሙያ በዲፕሎማ የሚያሰለጥንበት የትምህርትና ስልጠና ተቋም አቋቁሞ የዩኒቨርስቲ ምሩቃንን መመልመል ጀምሮ ነበር፡፡ የደኅንነቱ ሃላፊዎች ግን መልሰው ለውጡን እንዳቀዛቀዙትና ለዚህም ምክንያቱ ከገዥው ድርጅት መዋቅር ውጭ የሚመጡ ምልምሎች ታማኝነት ይጎድላቸዋል የሚል እንደነበር ዋዜማ ያነጋገረቻቸው ምንጮች ይጠቁማሉ፡፡ ባፉት ጥቂት ዐመታት ግን ተቋርጦ የነበረውን የዲፕሎማ ስልጠና ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርስቲ ጋር በመቀናጀት ወደ ዲግሪ መርሃ ግብር አሳድጎታል፡፡ ይህም ተቋሙ አደረጃጀቱን፣ የሰው ሃይሉን እና አሰራሩን ለማዘመን የወሰደው አንድ ርምጃ አድርጎ መውሰድ ይቻላል፡፡[ዘርዘር ያለ የድምፅ ዘገባ ከታች ይመልከቱ]

https://youtu.be/I7LOeG9tJQE